ፈልግ

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የመንገደኞች ጠባቂ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የመንገደኞች ጠባቂ  

ካርዲናል ሚካኤል፣ የእምነት መንገድ የወንጌል ምስክርነት ደስታ የሚገኝበት ሥፍራ መሆኑን ገለጹ

በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ ዕድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ ብጹዕ ካርዲናል ሚካኤል ቸርኒ፣ ግንቦት 16/2015 ዓ. ም. የዋለውን የመንገደኞች ጠባቂ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዓመታዊ በዓል በመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት አክብረዋል። ሮም በሚገኝ የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ባሳረጉት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ላይ ባሰሙት ቃለ ምዕዳን፣ “እምነት በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ውስጥ ልዩ የሆነውን የእግዚአብሔር ክብር እና ታላቅነት እንድንገነዘብ የሚያደርገን በመሆኑ አብረን ልንጓዘው ይገባል” ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ግንቦት 16 የሚከበረውን የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የመንገደኞች ጠባቂ ዓመታዊ በዓል ምክንያት በማድረግ የቀረበውን የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት የመሩት ብጹዕ ካርዲናል ሚካኤል ቸርኒ በዕለቱ ባሰሙት ቃለ ምዕዳን፣ የመንገደኞች ረዳት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ልጇን ኢየሱስ ክርስቶስን በሕጻንነቱ እንደመራችው በማስታወስ፣ የሮም ከተማ ሕዝብን ከበሽታ ጠብቃ ወደ መልካም የመራች በመሆኗ ለበርካታ ዘመናት ስትከበር መቆየቷን አስታውሰዋል። 

በየዕለቱ ወንጌልን ለመመስከር ተጠርተናል!

የኢየሱስ ክርስቶስ መወለድ ለእረኞቹ የተነገረበትን አጋጣሚ ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከተነገራት የብስራት ታሪክ ጋር ያዛመዱት ብፁዕ ካርዲናል ሚካኤል፣ “እግዚአብሔር ያደረገልንን ድንቅ ሥራ በጆሮአችን ሳንሰማ እምነት በውስጣችን አይወለድም" ብለው፣ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሳትዘገይ መልካም ዜናን ለማብሰር ወደ ኤልሳቤጥ በፍጥነት መሂዷን አስታውሰዋል።

መልካም ዜናን በፍጥነት ማብሰር ርቀት የማይገድበው፣ የተቸገሩትን የመቅረብ ፍላጎት የሚፈጥር እና ድንቅ ተአምራትን ለሌሎች እንድንነግር የሚያደርገን ነው ብለዋል። “እረኞችም የኢየሱስ ክርስቶስን መወለድ በሰሙ ጊዜ እንደተደነቁ ሁሉ፣  የቅዱስ ወንጌል አብሳሪ ደቀ መዛሙርት እንድንሆን፣ በዕለታዊ የሕይወት ጉዟችን ወንጌልን ለማብሰር ተጠርተናል” ብለዋል።

የእምነት መንገድን አብሮ መጓዝ

“የእምነት ጉዞን በኅብረት መጓዝ የኢየሱስ ክርስቶስ ምስክርነት ደስታን የምንጋራበት እና በሰው ልጅ ሕይወት ውስጥ የለውጥ እርምጃ የሚወሰድበት ነው” በማለት አስረድተዋል። የተነገራትን የምሥራች ቃል በልቧ መያዝ እና ማሰላሰል እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የሄደችባቸው ሁለት አመለካከቶች ናቸው” ያሉት ብፁዕ ካርዲናል ሚካኤል፣ ማርያም የሰማችውን በልቧ አስቀምጣ በማስታወሷ ሕይወቷ በእግዚአብሔር ቃል እንዲመራ በማድረግ እና ለወደፊት ሕይወቷም መመሪያ እንዲሆን የሚያስችል የእምነት ልምምድ አድርገዋለች” ብለዋል። ማሰላሰልም እንደዚሁ የዕይታችንን ጥልቀት የሚያድስ የማስተዋል ልምምድ ሲሆን፣ ይህ ደግሞ በእግዚአብሔር ዓይን በመመልከት እንደሆነ አስረድተዋል።

ክርስቶስን ከመረጥን መንገድ ሁሉ ወደ እርሱ ይመራል!

"እምነት በተለመደው የዕለት ተዕለት ሕይወት ውስጥ የእግዚአብሔርን ታላቅነት እንድናውቅ የተጋበዝንበት ጉዞ ነው" ያሉት ብፁዕ ካርዲናል ሚካኤል ቸርኒ፣ "እንደ ወንድማማቾች እና እህትማማቾች በአንድነት በምንጓዝበት የእምነት ጉዞ ላይ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አጋራችን ትሆነናለች" ብለዋል።

በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ ዕድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ ብጹዕ ካርዲናል ሚካኤል ቸርኒ ትናንት ባሳረጉት የመስዋዕተ ቅድሴ ጸሎት ላይ ያቀረቡትን ቃለ ምዕዳን ሲደመደሙ እንደተናገሩት፣ ሲኖዶሳዊነትን ወይም የኅብረት ጉዞን በመጥቀስ፣ የአንድነት ጉዞ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የተገለጸችበትን ቃል እንደሚያስታውሰን ገልጸው፣ የእምነት ልምዶቻችን እና ምርጫዎቻችን በእያንዳንዱ ምዕመናን እና በመላው ቤተ ክርስቲያን ሕይወት ውስጥ ዘወትር ወደ አንድነት ሊያመጣን እንደሚችል አስረድተዋል።

25 May 2023, 16:58