ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ብጹዕ ዮሐንስ ጳውሎስ ቀዳማዊ ር. ሊ. ጳ. ብጹዕ ዮሐንስ ጳውሎስ ቀዳማዊ  

ካርዲናል ፓሮሊን፥ “ር. ሊ. ጳ. ብፁዕ ዮሐንስ ጳውሎስ ቀዳማዊ ውጤታማ ሰላም ፈጣሪ ነበሩ”

የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን፣ “የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ዮሐንስ ጳውሎስ ቀዳማዊ ሐዋርያዊ አስተምህሮች” በሚል አርዕስት የተጻፈ መጽሐፍ የምረቃ ሥነ-ሥርዓት ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር፥ ብፁዕ ዮሐንስ ጳውሎስ ቀዳማዊ ውጤታማ ሰላም ፈጣሪ እንደ ነበሩ ገለጹ። በሰላሳ አራት የሐዋርያዊ መሪነት ቀናት ውስጥ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ሰላምን ለመፍጠር ላደረጉት ጥረትም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“የቀድሞ ር. ሊ. ጳ. ዮሐንስ ጳውሎስ ቀዳማዊ የሐዋርያዊ አስተዳደር ጊዜ አጭር ቢሆንም፣ ከጉባኤው ጋር ወደ ምንጩ ተመልሳ ከስብከተ ወንጌል አጀማመርዋ በመነሳት ዓለምን ለማገልገል ዓላማ ያደረገችውን ቤተ ክርስቲያን ዕቅድ በማጠናከር፣ የሰው ልጅ ለሚገኝበት እውነታ ቅርብ በመሆን እና ለበጎ አድራጎት የነበራቸው ጥማት ዛሬም ሆነ ሁል ጊዜ የማይሻር የማመሳከሪያ ነጥብ ሆኖ ዓለምን በማገልገል ነው።”

የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ እና የብፁዕ ዮሐንስ ጳውሎስ ቀዳማዊ ፋውንዴሽን ፕሬዚደንት ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን፣ በመጽሐፉ የምረቃ ሥነ-ሥርዓት ላይ ግንቦት 15/2015 ዓ. ም. ተገኝተው ባደረጉት ንግግር፥ “የር. ሊ. ጳ. ዮሐንስ ጳውሎስ ቀዳማዊ የሐዋርያዊ አስተዳደር ጊዜ አጭር እና የሰላሳ አራት ቀናት ጊዜ ብቻ እንደነበር ገልጸዋል። “የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ዮሐንስ ጳውሎስ ቀዳማዊ ሐዋርያዊ አስተምህሮች” በሚል አርዕስት እና “ታሪካዊ እና ሥነ-መለኮታዊ ጥናት ማህደር” በሚል ንኡስ አርዕስት ተጽፎ በሰሜን ጣሊያን የቬኒስ ካ’ፎስካሪ ዩኒቨርሲቲ ለምረቃ የበቃውን መጽሐፍ ያዘጋጁት ስቴፋኒያ ፋላስካ እና ፍላቪያ ቱዲኒ ናቸው።

የ ብፁዕ ዮሐንስ ጳውሎስ ቀዳማዊ ፋውንዴሽን በቫቲካን

በቫቲካን ውስጥ የሚገኘውን የብፁዕ ዮሐንስ ጳውሎስ ቀዳማዊ ፋውንዴሽን የካቲት 9/2012 ዓ. ም. በማቋቋም ሥራውን በይፋ ያስጀመሩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሲሆኑ፣ በፋውንዴሽኑ ውስጥ የብፁዕ ዮሐንስ ጳውሎስ ቀዳማዊ ሥነ-መለኮታዊ፣ ቤተ ክርስቲያናዊ፣ ባሕላዊ እና መንፈሳዊ ትሩፋት ያላቸው ጽሑፎች ተጠብቀው ቆይተው ለጥናት እንዲረዱ አድርገዋል።

ባለፉት ሦስት ዓመታት ውስጥ በቫቲካን የሚገኘው የብፁዕ ዮሐንስ ጳውሎስ ቀዳማዊ ፋውንዴሽን በዓለም አቀፍ ደረጃ ምርምር እና ጥልቅ ጥናት ለሚያካሂዱት ማብራሪያን በመስጠት መሠረታዊ እርምጃዎችን መውሰዱን ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን አስታውሰዋል። ፋውንዴሽኑ ካታሎግ አዘጋጅቶለት በቬኒስ ፓትሪያርካዊ ቤተ መጻሕፍት የሚገኘውን የግል ቤተ መጻሕፍት ጥራዞችን በማግኘት እና እንደገና በማዘዙ አሁንም በሂደት ላይ ያሉ መሠረታዊ እርምጃዎች መወሰዳቸውን ካርዲናል ፓሮሊን ገልጸዋል።

“ቤተ ክርስቲያን የጉባኤውን አቅጣጫ መሠረት በማድረግ ወደፊት እንድትራመድ ያደረጉት ብፁዕ ዮሐንስ ጳውሎስ ቀዳማዊ፣ ቅድሚያ የሰጡባቸውን ጉዳዮች ካርዲናል ፓሮሊን ሲገልጹ፥ ወደ ቅዱስ ወንጌል ምንጮች መመለስ፣ የታደሰ የሚስዮናዊነት መንፈስ እንዲኖር ማድረግ፣ የብጹዓን ጳጳሳት ኅብረት እና አንድነት፣ የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት፣ ከዘመናዊው ዓለም ጋር የሚደረግ ውይይት፣ ከአብያተ ክርስቲያናት ጋር አንድነትን መፈለግ፣ በሃይማኖቶች መካከል የሚደረግ ውይይት እና ሰላምን መፈለግ” እንደነበሩ ካርዲናል ፓሮሊን አብራርተዋል።

የሐዋርያዊ አስተምህሮ ውርስ

ካርዲናል ፓሮሊን በቫቲካን ውስጥ የሚገኘውን የብፁዕ ዮሐንስ ጳውሎስ ቀዳማዊ ፋውንዴሽን የጥናት ማዕከል በማስመልከት በሰጡት ማብራሪያ፣ የጥናት ማዕከሉ ዓለም አቀፍ ጥናትና ምርምር ለማስፋፋት ያስቻለ መሆኑን ገልጸው፣ የብጹዕ ዮሐንስ ጳውሎስ ቀዳማዊ ሐዋርያዊ አስተምህሮ ትሩፋትን ከታሪክ ማህደር ምንጮች አንፃር ለማስተዋወቅ ያደረገውን ጥረት አድንቀዋል። ፋውንዴሽኑ ሮም በሚገኝ ጎርጎሮሳዊ ጳጳሳዊ ዩኒቨርሲቲ አማካይነት ባለፈው ዓመት በግንቦት ወር የዮሐንስ ጳውሎስ ቀዳማዊ ሐዋርያዊ አስተምህሮችን የተመለከተ የመጀመሪያ ጥናታዊ ጉባኤን አዘጋጅቶ ሙሉ የታሪክ ማህደር ሰነዶችን በማስተዋወቅ ረገድ አዲስ የጥናት አቅጣጫ መክፈቱን አስታውሰዋል።

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ስለ ቀድሞው ር. ሊ. ጳ. ዮሐንስ ጳውሎስ ቀዳማዊ ያላቸውን አስተያየት ሲገልጹ፥ ር. ሊ. ጳ. ዮሐንስ ጳውሎስ ቀዳማዊ “የቅዱስ ጴጥሮስ ተተኪ የሆኑ ጽኑ ዓለት” እንደነበሩ ገልጸው፣ ክርስቶስ ራሱ የመሠረታት ቤተ ክርስቲያን በጸጋው አንድነቷን እንድትጥብቅ ያደረጉ መሆናቸውን አመልክተው፣ “ብፁዕ ዮሐንስ ጳውሎስ ቀዳማዊ እራሳቸው አባል በሆኑበት ክርስቲያን ሕዝቦች መካከል የዓለምን ቁስሎች እና ክፋቶች በትንቢታዊ ዓይን ተመልክተው ሰላም ለቤተ ክርስቲያን ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ያመላከቱ ሐዋርያዊ መሪ ነበሩ” በማለት ገልጸዋል። “ዮሐንስ ጳውሎስ ቀዳማዊ በሕዝቦች መካከል እርቅን እና ወንድማማችነትን በመፍጠር፣ ለትብብር በመጋበዝ፣ በጭንቅ ላይ በምትገኝ ዓለማችን ውስጥ ሰላምን ለማስፈን እና ለመጨመር እንዲሁም ጥፋትን እና ሐዘንን የሚያስከትል ዓመፅን ማስወገድ እና በሃይማኖቶች መካከል ያለውን አንድነት ለማሳደግ የነበራቸው ቁርጠኝነት” ቅድሚያን የሰጡበት እንደነበር ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በማከል ገልጸዋል።

የር. ሊ. ጳ. ዮሐንስ ጳውሎስ ቀዳማዊ ጥረቶች

ር. ሊ. ጳ. ዮሐንስ ጳውሎስ ቀዳማዊ በመካከለኛው ምሥራቅ ሰላም እንዲሰፍን በርካታ ጥሪዎችን ማድረጋቸውን ያስታወሱት ካርዲናል ፓሮሊን፣ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ መስከረም 10/1978 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከተሰበሰቡት ምዕመናን ጋር ባደረሱት የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ላይ፣ ቁርኣን እና ቅዱሳት መጻሕፍትን በመጥቀስ ለልዩ ልዩ የእምነት መሪዎች ባደረጉት ንግግር ለመጀመሪያ ጊዜ የሰላም ጥሪ ማስተላለፋቸውን አስታውሰዋል። “የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝደንት ጂሚ ካርተር “ሰላም ፈጣሪዎች ብፁዓን ናቸው” የሚለውን የኢየሱስ ክርስቶስን ቃል በመጥቀስ ንግግር ባደረጉበት ወቅት የአሜሪካ ኮንግረስ በጭብጨባ መቀበሉ በሁሉም ክርስቲያኖች ልብ በተለይም በካቶሊኮች ልብ ውስጥ ገብቶ እውነተኛ የሰላም ፈጣሪ እና አስከባሪ ያደርገናል ብዬ በእውነት ተስፋ አደርጋለሁ” ብለዋል።

ከአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጂሚ ካርተር ጋር መተባበር

በዚህ የተነሳ ር. ሊ. ጳ. ዮሐንስ ጳውሎስ ቀዳማዊ ለዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ጂሚ ካርተር በቀጥታ መጻፋቸውን ያስታወሱት ካርዲናል ፓሮሊን፣ በአጭር የር. ሊ. ጳጳሳትነት ወቅት የሰላም ግንባታ ጥረታቸው በሁለት ተጨባጭ ሁኔታዎች ላይ እንደ ነበር ጠቁመው፣ የመጀመሪያው እንደ ጎርጎሮሳውያኑ መስከረም 20/1978 ዓ. ም. ለአርጀንቲና እና ቺሊ ብጹዓን ጳጳሳት በላኩት መልክት፣ በሁለቱ አገራት መካከል በተፈጠረው የድንበር ውዝግብ ምክንያት በአገራቱ መካከል የተፈጠረው የትጥቅ ግጭት ቅድስት መንበር ባደረገችው ሽምግልና ሊወገድ መቻሉን አስታውሰዋል። ከዚህም በተጨማሪ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከመስከረም 5 – 17/1978 ዓ. ም. ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጂሚ ካርተር፣ የግብፁ ፕሬዝዳንት አንዋር ኤል ሳዳት እና የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ሜናችም ሜጊን በካምፕ ዴቪድ የተሳተፉበት የሰላም ድርድር ድጋፍ መሆኑንም አስታውሰዋል።

ለጸሎት እገዛቸው ምስጋናን አቅርበዋል

የተገኘውን ውጤት በማስመልከት የአሜሪካው ፕሬዘደንት ጂሚ ካርተር እንደ ጎርጎሮሳውያኑ መስከረም 17/1978 ዓ. ም. ለር. ሊ. ጳ. ዮሐንስ ጳውሎስ ቀዳማዊ ደብዳቤ በመጻፍ ለካምፕ ዴቪድ ስብሰባ መሳካት እና በመካከለኛው ምሥራቅ ሰላም እንዲሰፍን ላደረጉት የጸሎት ድጋፍ ምስጋና ማቅረባቸውን አስታውቀዋል። ር. ሊ. ጳ. ዮሐንስ ጳውሎስ ቀዳማዊ ለፕሬዝደንት ጂሚ ካርተር የጻፉትን መልዕክት ያስታወሱት ካርዲናል ፓሮሊን፣ “ቅድስት መንበር ይህን ግብ ለማሳካት የሚደረገውን ጥረት በጥልቅ በመከታተል እንደ ቀድሞው እንደሚቀጥል እርግጠኛ መሆናቸውን፣ ከእንቅስቃሴው ጋር በሚስማማ መንገድ ለመተባበር ዝግጁ መሆናቸውን እና በተመሳሳይም ለመካከለኛው ምሥራቅ አገራት እና ለመላው ዓለም አስፈላጊ የሆነውን ሰላም ለማምጣት ጸሎት ማቅረብ እንቀጥላለን” ማለታቸውን አስታውሰዋል።

በመንበረ ጴጥሮስ የሚደረግ መላውን ዓለም ይነካል

እነዚህን ችግሮች ለመፍታት የሚረዳን መንፈስ፣ ሁለንተናዊ በጎ አድራጎት እና ለታላቅ እሴቶች ግልጽ መሆን፣ ር. ሊ. ጳ. ዮሐንስ ጳውሎስ ቀዳማዊ በሐዋርያዊ ሥልጣናቸው መጀመሪያ ላይ ማለትም እንደ ጎርጎሮሳውያኑ መስከረም 3/1978 ዓ. ም. ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ “ቤተ ክርስቲያን ትሑት የወንጌል መልዕክተኛ በመሆኗ በምድር ሁሉ ሰላምን ለመፍጠር የበኩሏን አስተዋፅዖ ታደርጋለች” ማለታቸውን አስታውሰው፣ ያለ ፍትህ፣ ያለ ወንድማማችነት እና ያለ አብሮነት ዓለም በስላም መኖር እንደማይችል እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ግንቦት 23/1973 ዓ. ም. “ሰላም በምድር” የሚል የቅዱስ ዮሐንስ 23ኛ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን አሥረኛ ዓመት በተከበረበት ወቅት የቬኒስ ከተማ ፓትሪያርክ የር. ሊ. ጳ. ዮሐንስ ጳውሎስ ቀዳማዊ የጥበብ ቃላትን መጥቀሳቸውን ካርዲናል ፓሮሊን አስታውሰዋል።

ቅድስና እና ለሰላም የሚቀርቡ ጸሎቶች

ዓለም ከቤተ ክርስቲያን የፖለቲካ አጀንዳዎችን፣ የቡድን እና የድንበር ምርጫዎችን እንደማይጠብቅ የገለጹት ካርዲናል ፓሮሊን፣ የውይይት ድፍረት፣ አስተዋይነት፣ ከኃያላን መንግሥታት ጋር በእምነት እና በቅድስና ለመወያየት በጸሎት መጠንከር እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። ጸሎት በችግር ዘመን ብቸኛው ውጤታማ ክንድ እንደሆነ የገለጹት ካርዲናል ፓሮሊን፣ ዛሬም ቢሆን የስልጣን ሽንገላ እና ግዴለሽነት፣ የፍትህ እና የሰላም ጥማትን ያለገደብ እየደበቀው እንደሚገኝ አስረድተዋል።

በእነዚህ መሣሪያዎች የር. ሊ. ጳ. ዮሐንስ ጳውሎስ ቀዳማዊ ሐዋርያዊ አስተዳደር የማይሻር ምስክርነትን እንደሰጠ ተናግረው፣ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያንን ለአጭር ጊዜ ብቻ ቢመሯትም ቤተ ክርስቲያንን እና ዓለምን በበጎ አድራጎት ሥራቸው የማይሻር የጥንካሬ ሐሳብ ማቅረባቸውን ካርዲናል ፓሮሊን ገልጸዋል።

24 May 2023, 18:13