ፈልግ

በቫቲካን ውስጥ የሚገኘው የሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ቤተ መቅደስ የውስጥ ገጽታ በቫቲካን ውስጥ የሚገኘው የሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ቤተ መቅደስ የውስጥ ገጽታ  (Vatican Media)

ለጸሎት ወደ ቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ለሚመጡት ምዕመናን አዲስ ዕቅድ ተዘጋጅቶላቸዋል

በቫቲካን በሚገኘው ቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ ከተለያዩ አካባቢዎች መጥተው በተለያዩ መንፈሳዊ ሥነ-ሥርዓቶች፣ በመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ለመሳተፍ ወይም ኑዛዜን መግባት ለሚፈልጉት ምዕመናን ከመጋቢት 19/2015 ዓ. ም. ጀምሮ ተግባራዊ የሚሆን አዲስ ዕቅድ ይፋ ተደርጓል። የባዚሊካው ሊቀ ካህን ብጹዕ ካርዲናል ማውሮ ጋምቤቲ በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ የሚፈጸሙ የተለያዩ መንፈሳዊ ሥነ-ሥርዓቶችን በማስመልከት ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት እንደገለጹት፥ “ቤተ መቅደሱ መንፈሳዊ ሕይወት ለመለማመድ፣ በሥርዓተ አምልኮ ሥነ-ሥርዓቶች ለመሳተፍ እና መንፈሳዊ በዓላትን ለማክበር የሚያስችል ከፍተኛ ተደራሽነት እንዲኖረው ለማድረግ እንፈልጋለን" ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ወደ ቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ደርሰው ጸሎት ማድረስ እና በመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት መሳተፍ ለሚፈልጉ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና ምዕመናን በሙሉ የተዘጋጀ አዲስ መግቢያ መንገድ መጋቢት 19/2015 ዓ. ም. ለሙከራ መከፈቱ ታውቋል።

የባዚሊካው የቀኝ መተላለፊያ አገልግሎት እንዲሰጥ ተመርቆ ተከፍቷል

ከቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ የጸጥታ አስከባሪዎች ጋር በመተባበር ክፍት እንዲሆን የተደረገው የባዚሊካው ቀኝ በኩል መግቢያ በሩ፣ በባዚሊካው ቀኝ በኩል ወደሚገኝ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ታዋቂ ሐውልት፣ ወደ ቀድሞ ር. ሊ. ጳ. ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ መካነ መቃብር፣ የቅዱስ ቁርባን ጸሎት ወደሚቀርብበት፣ ወደ ጎርጎሮሳውያን ጸሎት ቤት፣ ወደ እመቤታችን ረድኤት ቅዱስ ምስል፣ ንስሐን ወደ ሚገቡበት እና የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎትን ወደሚሳተፉበት ቅዱስ ዮሴፍ ቤተ ጸሎት መድረስ የሚያስችል እንደሆነ ተገልጿል።   

ከእንግዲህ ሰልፍ መጠበቅ አይኖርም

በባዚሊካው ውስጥ የግል ጸሎት ማቅረብ ወይም ቅዱሳት ምስጢራትን መቀበል የሚፈልጉ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና ምዕመናን ወረፋ መጠበቅ እንደ ሌለባቸው የተነገረ ሲሆን፣ ባዚሊካው ክፍት የሚሆንበት ሰዓትም በየቀኑ ከጠዋቱ 12:50 እስከ ማታ 12:40 ድረስ እንደሚሆነ ተገልጿል። በባዚሊካ ውስጥ የሚፈጸሙ የአምልኮ ሥነ-ሥርዓቶችን መካፈል የሚፈልጉ የሀገር ጎብኚዎችም በተጠቀሰው መንገድ በኩል ያለ ቲኬት በነፃ መግባት እንደሚችሉ የተገለጸ ሲሆን፣ ይህን አዲስ እና ልዩ የሙከራ መንገድ ያስተዋወቁበት ዋና ዓላማ፣ የግል ጸሎት ለማቅረብ እና በመሥዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ለመሳተፍ ወደ ቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ የሚመጡት ምእመናን፣ የጸሎት ማኅበራት እና መንፈሳዊ ነጋዲያን ረጅም ወረፋ ሳይጠብቁ በቀላሉ መግባት እንዲችሉ ለማስቻል መሆኑን የባዚሊካው ሊቀ ካህን ብጹዕ ካርዲናል ማውሮ ጋምቤቲ አስታውቀዋል።

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን ምኞት መሠረት በማድረግ በቅዱስ ጴጥሮስ ቤተ መቅደስ ውስጥ መንፈሳዊ ሕይወትን ለመለማመድ፣ የአምልኮ ሥነ-ሥርዓቶችን ለመሳተፍ እና መንፈሳዊ በዓላትን ለማክበር ከፍተኛ ተደራሽነት እንዲኖረው ለማድረግ እንደሚፈልጉ የገለጹት ብጹዕ ካርዲናል ማውሮ ጋምቤቲ፣ አዲሱ ዕቅድ በተለያዩ መንፈሳዊ ንግደቶች ላይ ለተሰማሩት ምዕመናን መልካም አቀባበልን በማድረግ፣ ንግደት የሚያደርጉበትን ምክንያት የሚገልጽ ማስረጃ የሚያሳዩ ከሆነ፣ ወደ ባዚሊካው መምጣታቸውን የሚያረጋግጥ በብራና የተዘጋጀ የምስክር ወረቀት የሚሰጣቸው መሆኑንም ገልጸዋል።

 

29 March 2023, 19:44