የካቶሊክ ምዕመናን ቁጥር በአራቱ አህጉራት ውስጥ ጨምሮ መገኘቱ ተነገረ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ከዓለም ሕዝብ መካከል ከአንድ ሰባተኛው በላይ የካቶሊክ እምነት ተከታይና ምስጢረ ጥምቀትን የተቀበለ መሆኑን የመረጃ ተቋሙ ገልጾ፣ ከ7 ቢሊዮን 667 ሚሊዮን የዓለም ሕዝብ መካከል 360 ሚሊዮን ሕዝብ የካቶሊክ እምነት ተከታይ መሆኑን ሪፖርቱ ገልጿል። የጳጳሳዊ ተልዕኮ አገልግሎት መረጃ ማዕከሉ ዘንድሮ ይፋ ያደረገው መረጃ፣ ዓለም አቀፍ የተልዕኮ ቀንን ምክንያት በማድረግ ከሚያወጧቸው የቤተ ክርስቲያን ዓመታዊ መረጃዎች አንዱ መሆኑ ታውቋል።
በታህሳስ 22/2013 ዓ. ም. የወጣውን የቤተ ክርስቲያኒቱን የስታቲስቲክስ መረጃን መሠረት ያደረገው ሪፖርቱ፣ በተለያዩ የቤተ ክርስቲያን ክፍሎች ባደረገው ጥናት መሠረት ዛሬ በዓለማችን ውስጥ 5,300 ብጹዓን ጳጳሳት መኖራቸውን አስታውቆ፣ ቁጥሩ ከሀገረ ስብከት ጳጳሳት ይልቅ በገዳማውያ ጳጳሳት ዘንድ ዕድገት ማሳየቱን ገልጿል። በጠቅላላው ሲታይ የካኅናት ቁጥር በተለይም በአውሮፓ፣ በአሜሪካ እና አውስትራሊያን ጨምሮ በደቡብ ውቅያኖስ አካባቢ አገራት ቀንሶ የታየ ቢሆንም በአፍሪካ እና በእስያ የካኅናት ቁጥር መጨመሩ ተመልክቷል። የቋሚ ዲያቆናት ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ያስታወቀው ሪፖርቱ፣ በሌላ ወገን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በዓለም ዙሪያ የገዳማውያት ቁጥር ቢቀንስም ነገር ግን በእስያ እና በአፍሪካ ውስጥ ዕድገት ማሳየቱን ሪፖርቱ አመልክቷል።
የክኅነት ጥሪን በተመለከተ፣ በያዝነው የፈረንጆቹ ዓመት፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚገኙ ወደ 112,000 ገደማ በሚጠጉ የሀገረ ስብከት እና የገዳማውያን የዘርዓ ክህነት ትምህርት ቤቶች ውስጥ የ 2,200 ተማሪዎች መቀነስ ቢታይም በአፍሪካ አህጉር ብቻ ጭማሪ ማሳየቱ ተመልክቷል። የዝቅተኛ የሀገረ ስብከት እና የገዳማውያን ዘርዓ ክኅነት ተማሪዎች ቁጥርም የቀነሰ ሲሆን፣ በጠቅላላ ድምሩ በ95,300 ተማሪዎች መቀነሱ ተመልክቷል።
ትምህርት ቤቶች እና የጤና ተቋማት
በመላዋ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚገኙ የትምህርት እና የስልጠና ማዕከላትን የተመለከተው ሪፖርቱ፣ ቤተ ክርስቲያኒቱ በዓለም ዙሪያ 7.5 ሺህ የመዋለ ሕፃናት ትምህርት ቤቶች እንዳላት እና በእነዚህ ትምህርት ቤቶች ተመዝግበው የሚማሩ ወደ 73,000 የሚጠጉ ህፃናት መኖራቸውን ገልጿል። በ100,000 የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ሌሎች 34 ሚሊዮን ተማሪዎች እንደሚማሩ እና ከ19 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች በ50,000 2ኛ ደረጃ ት/ቤቶች ተመዝግበው ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ እንደሚገኙ ሪፖርቱ ገልጿል። ወደ 2 ሚሊዮን ተኩል የሚጠጉ ተማሪዎች የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የሚከታተሉ እና ወደ 3 ሚሊዮን 800 ሺህ የሚጠጉ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መሆናቸውን አመልክቷል።
በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የካቶሊካዊ ቤተ ክርስቲያን የጤና፣ የበጎ አድራጎት እና የዕርዳታ መስጫ ተቋማትንም የተመለከተው ሪፖርቱ፣ 5,322 ሆስፒታሎች፣ 14,415 የመጀመሪያ ሕክምና ዕርዳታ መስጫ ማዕከላት፣ 534 ላቦራቶሪዎች፣ 15,204 የአረጋውያን፣ የሕሙማን እና የአካል ጉዳተኞች ማዕከላት፣ 9,230 የወላጅ አልባ ሕፃናት ማሳደጊያዎች፣ 10,441 መዋለ ህፃናት፣ 10,362 የምክር አገልግሎት መስጫ ማዕከላት፣ 3,137 የማኅበራዊ ኑሮ ስልጠና ማዕከላት እና 34,291 ሌሎች ልዩ ልዩ ስልጠና መስጫ ማዕከላን መኖራቸውን የጳጳሳዊ ተልዕኮ አገልግሎት መረጃ ማዕከል በዓመታዊ ሪፖርቱ አስታውቋል።