ፈልግ

የላቲን አሜሪካ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች አንድነት ዋና ጸሐፊ ክቡር አቶ ሮድሪጎ ጉዌራ ሎፔዝ የላቲን አሜሪካ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች አንድነት ዋና ጸሐፊ ክቡር አቶ ሮድሪጎ ጉዌራ ሎፔዝ  

የአውሮፓ ጦርነት ውጥረትን፣ ድህነትን እና የኑሮ አለመመጣጠን የሚያሳድግ መሆኑ ተገለጸ

በብጹዕ ካርዲናል ኦዌሌት የሚመራ የላቲን አሜሪካ ጳጳሳዊ ምክር ቤት “የዩክሬን ጦርነት በላቲን አሜሪካ ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ” በሚል ርዕስ ላይ የተወያየ ጉባኤ ማካሄዱ ታውቋል። ልዩ ልዩ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቶችን ያሰባብሰበ ጉባኤው፣ በአውሮፓ ውስጥ የሚካሄድ ጦርነት ውጥረትን፣ ድህነትን እና የኑሮ አለመመጣጠንን የሚያሳድግ መሆኑን ገልጿል። የላቲን አሜሪካ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች አንድነት ዋና ጸሐፊ ክቡር አቶ ሮድሪጎ ጉዌራ ሎፔዝ በጥናታዊ ጽሑፋቸው፣ “ክልላችን የውስጥ ግጭቶችን ማሸነፍ ከቻለ ለተከፋፈለ እና በግጭት ውስጥ ለሚገኝ ዓለም ጥሩ ምሳሌ ሊሆን ይችላል” ማለታቸው ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በዩክሬን ውስጥ ከሁለት ወራት በላይ ሲካሄድ የሰነበተውን ጦርነት አስመልክቶ የሚወጡ የእውነት እና የሐሰት መረጃዎች የዜናን ውበታዊ እውነታን እየተካ መምጣቱ ታውቋል። በረጅም ሞገድ አማካይነት ወደ ላቲን አሜሪካ የሚደርስ መረጃ በጥቂቶች ሀብታሞች እና ከፍተኛ ቁጥር ባለው ድሃ ማኅበረሰብ መካከል የኑሮ ልዩነት በማስፋት አዲስ ሕዝባዊ እንቅስቃሴ በፖለቲካው ላይ የበላይነትን እንዲያገኝ እና በጽንፈኞች ፖለቲካ እንዲመራ የሚያደርግ ግጭት በክርስቲያን ማኅበረሰቦች ሕይወት ጉዳት እያስከተለ መሆኑ ታውቋል። እ. አ. አ የካቲት 24/2022 ዓ. ም. ሩሲያ በዩክሬን ላይ የከፈተችው ወረራ እና የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ያስከተለው ውጤት በመካከለኛው እና ደቡብ አሜሪካ ውስጥ ዛሬ ያለውን ሁኔታ በግልጽ አያሳይም።

ር. ሊ. ጳ ብቻ በሰላማዊ መንገድ ሰላምን በመፈለግ ላይ ይገኛሉ

በጥናታዊ ጽሑፋቸው “ክልላችን የውስጥ ግጭቶችን ማሸነፍ ከቻለ ለተከፋፈለ እና በግጭት ውስጥ ለሚገኝ ዓለም ጥሩ ምሳሌ ሊሆን ይችላል” ያሉት የላቲን አሜሪካ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች አንድነት ዋና ጸሐፊ ክቡር አቶ ሮድሪጎ ጉዌራ ሎፔዝ፣ ሁሉም ሰው በየፊናው “እኔ ሰላምን እደግፋለሁ” የሚል ቢሆንም ነገር ግን “ሰላምን፣ በሰላማዊ መንገድ ማግኘት ይችላል!” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ብቻ መሆናቸውን ለቫቲካን የዜና አገልግሎት ገልጸው፣ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ አቋማቸውን በገለጹበት፣ “ሁላችንም ወንድማማቾች ነን” በሚለው ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳናቸው፣ ወንድማማችነትን እንደ የፖለቲካ እርምጃ ዘዴ እንድንጠቀም መጋበዛቸውን አስረድተዋል።  

የምንገኝበት የድህረ ዘመናዊነት ወቅት እውነትን ወደ ጎን በማለት፣ የላይ ላዩ የመረጃ ውበት እውነታውን እንደሚተካ መረዳት በጣም አስፈላጊ እንደሆነ ገለጸው፣ ተፈጥሮን እና እውቀትን ያገናዘበ እውነት፣ ለተፈጥሮ ጥሪ ምላሽ የሚሰጥ የሰውን ልጅ ሁል ጊዜ መከላከል እንዳለበት አስገንዝበዋል። የሐሰት መረጃ በሚያስከትለው ጨካኔ ውስጥ እንገኛለለን ያሉት ክቡር አቶ ሮድሪጎ ጉዌራ ሎፔዝ፣ የሐሰት መረጃ ፍልሚያም ከጦርነት አንዱ እንደሆነ ገልጸው በዚህ ምክንያት ሁሉም ወገኖች እውነትን እንደገና ለማወቅ በጋራ መሥራት እንደሚገባ እና ሰላምን ማምጣት የሚቻለው እውነተኛ ፍትህ ሲገኝ ብቻ እንደሆነ አሰምረዋል።

ሰላምን ማምጣት የሚቻለው በሰላማዊ መንገድ እንጂ በአመጽ ወይም በሐሰት መረጃ እንዳልሆነ ገልጸው፣ ጦርነትን ሰላምን ለማስፈን የሚያካሂዱ ከሆነ አዲስ ግጭት ሊፈጥር ይችላል ብለው፣ የላቲን አሜሪካ ብፁዓን ጳጳሳት ምክር ቤቶች፣ በተለይ በላቲን አሜሪካ ውስጥ የሚገኙ ቤተ ክርስቲያኖቻችን የሰላም ባሕል እንዲያዳብሩ ለመርዳት ይህን ሁኔታ መረዳት እንዳለብን እናምናለን ብለዋል። አክለውም የላቲን አሜሪካ አገሮች የውስጥ ግጭቶቻቸው ማሸነፍ ከቻሉ፣ በአውሮፓ ውስጥ እንደምናየው በግጭት እና በአመጽ ለተከፋፈለ ዓለም ጥሩ ምሳሌ ሊሆኑ እንደሚችሉ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል። ለዚህም ሃላፊነትን በመውሰድ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር በመተባበር ለሰላም መሥራት፣ ከሁሉም ሰው ጋር በትዕግስት እና በምሕረት የተሞላ ውይይትን እንደ እውነተኛ የፖለቲካ ተግባር እና ትክክለኛ የቤተ ክርስቲያን እና የሐዋርያዊ እርምጃ ዘዴ መጠቀም ያስፈልጋል ብለዋል።

በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ጦርነት ሁል ጊዜ ለአንዳንድ ኢኮኖሚያዊ ማነቃቃቶች እንደ ማበረታቻ መንገድ ሆኖ አገልግሏል ያሉት አቶ ሮድሪጎ ጉዌራ ሎፔዝ፣ ለሁለተኛው የዓለም ጦርነት ምስጋና ይግባውና፣ ዩናይትድ ስቴትስ እ. አ.አ. በ 1920 ዎቹ ውስጥ ከነበረችበት የኢኮኖሚ ድቀት እንድትወጣ አግዟታል ብለዋል። ዩናይትድ ስቴትስ በተጋፈጠችበት በዚህ የኢኮኖሚ ድቀት ወቅት ጦርነቱ ያለምንም ጥርጥር ኢኮኖሚያዊ ዳግም መነቃቃትን እንደሚፈጥርላት ያላቸውን እምነት ገልጸዋል። በላቲን አሜሪካ ሁኔታው የተለየ እንደሆነ ገልጸው፣ ክልሉ ለምሳሌ በነዳጅ፣ በተፈጥሮ ጋዝ እና በሸቀጣ ሸቀጦች በኩል መልካም ዕድሎች ሊያጋጥሙ ብችልም፣ የመሠረተ ልማት አውታሮች የንግድ ሥራ ዕድልን ለመጋፈጥ በቂ ዝግጅት አላደረጉም ብለዋል።

ክቡር አቶ ሮድሪጎ ጉዌራ ሎፔዝ
ክቡር አቶ ሮድሪጎ ጉዌራ ሎፔዝ

የአሜሪካ መንግሥት አቋም ውስብስብ እንደሆነ የገለጹት አቶ ሮድሪጎ ጉዌራ ሎፔዝ፣ በቬነዙዌላ ውስጥ ለፖለቲካ ተቃዋሚዎች የዕርዳታ እጁን ዘርግቶ መቆየቱን አስታውሰው ነገር ግን በቅርብ ሳምንታት ውስጥ ከቬነዙዌላው ፕሬዚደንት ማዱሮ ጋር ይፋ የሆነ የግንኙነት መስመር ለመፍጠር መሞከሩን ገልጸዋል። ይህ እጅግ አስፈላጊ ቢሆንም፣ ከነዳጅ ግብይት የበለጠ አስፈላጊ የሚሆነው ቬነዙዌላ ነፃ አገር እንደሆነች ዩናይትድ ስቴትስ መገንዘቧ እንጂ ሩሲያ ቅድመ ሁኔታዎች ማስቀመጥ እንደማትችል አስረድተዋል።

በላቲን አሜሪካ ውስጥ ግራ አክራሪ እና የቀኝ ጽንፈኛ ቡድኖች ከጥቂት ዓመታት በፊት የአክራሪዎችን አቋም በመቀየር እና በመቀነስ መካከለኛ ቦታን እየያዙ መምጣታቸውን የገለጹት አቶ ሮድሪጎ ጉዌራ ሎፔዝ፣ የቀኝ ጽንፈኛ እና የግራ አክራሪ ቡድኖን ማዕከላዊ ቦታ መያዛቸው በአንዳንድ የላቲን አሜሪካ ሀገሮች ውስጥ አደገኛ ሁኔታን ሊፈጥር እንደሚችል፣ ምክንያቱም አመጽ መፍጠር ለሚፈልጉ አንዳንድ ቡድኖች መልካም አማራጭ ይከፍታል ብለዋል። በዚህ ምክንያት “ሁላችንም ወንድማማቾች ነን” የሚለውን ሐዋርያዊ ሰነድ እንደ የፖለቲካ እርምጃ ዘዴ እንድንወስድ የሚጋብዘንን የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ድምጽ በትኩረት ማዳመጥ እንደሚያስፈልግ፣ የላቲን አሜሪካ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች አንድነት ዋና ጸሐፊ ክቡር አቶ ሮድሪጎ ጉዌራ ሎፔዝ ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ አስረድተዋል።

09 May 2022, 18:13