ፈልግ

ብጹዕ ካርዲናል አንጄሎ ሶዳኖ እኚህ ነበሩ። ብጹዕ ካርዲናል አንጄሎ ሶዳኖ እኚህ ነበሩ። 

የቀድሞ የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ፣ ብጹዕ ካርዲናል አንጄሎ ሶዳኖ አረፉ

የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ በመሆን ከ1983 – 1996 ዓ. ም. ያገለገሉት ብጹዕ ካርዲናል አንጄሎ ሶዳኖ፣ ዓርብ ምሽት ግንቦት 19/2014 ዓ. ም. ማረፋቸው ታውቋል። ብጹዕ ካርዲናል አንጄሎ ሶዳኖ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ተጠቅተው በሮም የሕክምና ዕርዳታ ሲደረግላቸው ቆይቷል። ብጹዕ ካርዲናል አንጄሎ ሶዳኖ በ15 የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ዓመታት የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ሆነው ቫቲካን በዓለም አቀፍ ደረጃ የምታካሂዳቸውን የሰላም ጥረቶች መርተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ከተወለዱ በ94 ዓመት ዕድሜአቸው ያረፉት ብጹዕ ካርዲናል አንጄሎ ሶዳኖ፣ በሁለቱ የቀድሞ ርዕሳነ ሊቃነ ጳጳሳት ማለትም በር. ሊ. ጳ ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ እና በር. ሊ. ጳ ቤነዲክቶስ 16ኛ ሐዋርያዊ የአገልግሎት ዓመታት የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ሆነው፣ ከ1997 – 2019 ዓ. ም. የካርዲናሎች መማክርት ጉባኤ ሰብሳቢ በመሆን ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያንን ማገልገላቸው ይታወሳል። ብጹዕ ካርዲናል አንጄሎ ሶዳኖ ለሳንባ ምች በመጋለጣቸው ምክንያት ከግንቦት 1/2014 ዓ. ም. ጀምሮ ሮም በሚገኝ ጄሜሊ ሆስፒታል የሕክምና ዕርዳታ ሲደረግላቸው የቀየ ሲሆን በኋላም በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ተይዘው የሕክምና ዕርዳታን ሲያገኙ መቆየታቸው ታውቋል።

በሰሜን ጣሊያን ፒዬሞንተ ክፍለ ሀገር በምትገኝ በአስቲ ደሴት፣ ዓርብ ታኅሳስ 13/1920 ዓ. ም. የተወለዱት ብጹዕ ካርዲናል አንጄሎ ሶዳኖ፣ ወላጆቻቸው ካፈሯቸው ስድስት ልጆች መካከል ሁለተኛ እንደነበሩ ሲነገር ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን እና ለቫቲካን መንግሥት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከታቸው ታውቋል። በተወለዱበት አካባቢ ባለው ጳጳሳዊ ዘርዓ ክህነት ትምህርት ቤት በመግባት የፍልስፍና እና ነገረ መለኮት ትምህርታቸውን ተከታትለው ካጠናቀቁ በኋላ ለከፍተኛ መንፈሳዊ ትምህርት ወደ ሮም በመምጣት በግሬጎሪያን ጳጳሳዊ ዩኒቨርሲቲ እና በላቴራን ጳጳሳዊ ዩኒቨርሲቲዎች የነገረ መለኮት እና የሕገ ቀኖና ትምህርታቸውን ተከታትለው ሁለት ድግሪዎችን ተቀብለዋል። 

በተወለዱበት በአስቲ ደሴት በሚገኝ ካቴድራል ውስጥ እሑድ መስከረም 13/1943 ዓ. ም. የክኅነት ማዕረጋቸውን የተቀበሉት ብጹዕ ካርዲናል አንጄሎ ሶዳኖ፣ በመጀመሪያዎቹ የክኅነት አገልግሎት ዓመታት ወጣቶችን እምነተ አንቀጻዊ ሥነ መለኮት ትምህርት ለማስተማር ተሰማርተው እንደነበት ታውቋል። በ 1951 ዓ. ም. ቅድስት መንበርን ለማገልገል፣ በወቅቱ የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ በነበሩት በብጹዕ ካርዲናል አንጀሎ ዴላአኩዋ ወደ ቫቲካን መጠራታቸው ይታወሳል።  ወደ ሮም ከመጡ በኋላም በጳጳሳዊ ቤተ ክህነት አካዳሚ ገብተው የተለያዩ ኮርሶችን ከተከታተሉ በኋላ በላቲን አሜሪካ በሚገኙ ሦስት አገራት እነርሱም በኢኳዶር፣ በኡራጓይ እና በቺሊ በሚገኙ ሐዋርያዊ እንደራሴ ውስጥ በጸሐፊነት ተመድበው ማገልገላቸው ይታወሳል። በ 1960 ዓ. ም. ወደ ሮም ተመልሰው በቤተ ክርስቲያኒቱ የሕዝብ ጉዳይ ምክር ቤት ለአሥር ዓመታት ያገለገሉ ሲሆን የቅድስት መንበር የልኡካን አባል በመሆን ሩማንያንን፣ ሃንጋሪን እና ምስራቅ ጀርመንን መጎብኘታቸው ይታወሳል።

የቀድሞ ር. ሊ. ጳ ቅዱስ ጳውሎስ ስድስተኛ፣ ኅዳር 21/1970 ዓ. ም. በጣሊያን የኖቫ ዲ ሴሳር ሊቀ ጳጳስ አድርገው በመሰየም፣ በላቲን አሜሪካ የቺሊ ሐዋርያዊ እንደራሴ አድርገው መሾማቸው ይታወሳል። ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ጥር 7/1970 ዓ. ም. በትውልድ አካባቢያቸው በሚገኝ ቅዱስ ሴኮንዶ ቤተ ክርስቲያን ከብፁዕ ካርዲናል አንቶኒዮ ሳሞሬ የጵጵስና ማዕረግ ተቀብለዋል። የላቲን አሜሪካ አገር በሆነች ቺሊ ውስጥ በሳለፏቸው አሥር የሐዋርያዊ አገልግሎት ዓመታት፣ ሁሉንም ሀገረ ስብከቶች ማለት በሚያስችል ደረጃ ሐዋርያዊ ጉብኝት ማድረጋቸው ሲታወስ፣ በቺሊ እና በአርጀንቲና መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት ለማስወገድ የተደረገው ጳጳሳዊ ሽምግልና በተሳካ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ ተባብረዋል። በ 1980 ዓ. ም. የቀድሞ ር. ሊ. ጳ ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ፣ በወቅቱ በቅድስት መንበር የሕዝብ ጉዳዮች ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ የነበሩትን ብፁዕ ካርዲናል አኪሌ ስልቬስቲኒ ለመተካት ወደ ሮም መጥራታቸው ይታወሳል። ከአንድ ዓመት በኋላ፣ “የመልካም እረኛ” ሐዋርያዊ ሕግ ተግባራዊ በሆነ ጊዜ፣ ብጹዕ ካርዲናል አንጄሎ ሶዳኖ የመንግሥታት ግንኙነት ዋና ጸሐፊ ሆነው በመሾም፣ በተለይም የሩሲያ ጳጳሳዊ ኮሚሽን ፕሬዚዳንት ሆነው ማገልገላቸው ይታወሳል።

ብጹዕ ካርዲናል አንጄሎ ሶዳኖ፣ በአውሮፓ የደኅንነት እና የትብብር ጉባኤዎች፣ በአውሮፓ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባዎች እና በሌሎች የተለያዩ ዓለም አቀፍ ስብሰባዎች ቅድስት መንበርን ወክለው መካፈላቸው ይታወሳል። በ1983 ዓ. ም. በቅድስት መንበር የውጭ ጉዳይ ጽሕፈት ቤት ረዳት ጸሐፊ የነበሩት ብጹዕ ካርዲናል አንጄሎ ሶዳኖ፣ ሰኔ 22/1983 ዓ. ም. የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ሆነው የተሾሙ ሲሆን ይህን ሐዋርያዊ ሥልጣን በተቀበሉበት ማግሥት እሑድ ሰኔ 23/1983 ዓ. ም. የካርዲናልነትን ማዕረግ መቀበላቸው ይታወሳል። ቀጥለውም በ1994 ዓ. ም. የካርዲናሎች መማክርት ምክትል ሰብሳሚ ሆነው መመረጣቸው ይታወሳል።

የቀድሞ ር. ሊ. ጳ ቤኔዲክቶስ 16ኛ መላዋ ቤተ ክርስቲያንን በበላይነት እንዲመሩ የተመረጡበትን የ 1997 ዓ. ም. ዝግ ጉባኤን የተካፈሉት ብጹዕ ካርዲናል አንጄሎ ሶዳኖ፣ ር. ሊ. ጳ ቤኔዲክቶስ 16ኛ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነታቸውን በድጋሚ በማረጋገጥ የካርዲናሎች መማክርት ሰብሳቢነት ሥልጣናቸውን ማጽደቃቸው ይታወሳል። እስከዚያ ጊዜ ድረስ የካርዲናሎች መማክርት ሰብሳቢነት በቀድሞ ስማቸው ብፁዕ ካርዲናል ዮሴፍ ራትዚንገር በመባል በሚታወቁ በኋላም ር. ሊ. ጳ ቤነዲክቶስ 16ኛ ተይዞ መቆየቱ ይታወሳል። ከጥቂት ወራት በኋላ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክቶስ 16ኛ ከብጹዕ ካርዲናል አንጀሎ ሶዳኖ የቀረበላቸውን የአገልግሎት መልቀቂያ ጥያቄአቸውን ተቀብለው፣ ብፁዕ ካርዲናል ታርሲስዮ በርቶኔን የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ አድርገው መሰየማቸው ይታወሳል። ብጹዕ ካርዲናል አንጄሎ ሶዳኖ በ2011 ዓ. ም. የካርዲናሎች መማክርት ሰብሳቢነት የሥራ መልቀቂያ ጥያቄን ለር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ አቅርበው ተቀባይነትን ማግኘታቸው ይታወሳል። ብጹዕ ካርዲናል አንጄሎ ሶዳኖ "በስብከተ ወንጌል አውድ የቤተሰብ ሐዋርያዊ አገልግሎት ተግዳሮቶች" በሚል ርዕሥ በ2006 ዓ. ም. የተካደውን የብጹዓን ጳጳሳት ሦስተኛ ጠቅላላ መደበኛ ሲኖዶስን እና ከአንድ ዓመት በኋላ "የቤተሰብ ጥሪ እና ተልዕኮ በቤተክርስቲያን እና በዘመናዊው ዓለም" በሚል መሪ ሃሳብ የተዘጋጀውን 14ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤን መካፈላቸው ይታወሳል።

ከብፁዕ ካርዲናል አንጀሎ ሶዳኖ ዕረፍት በኋላ የካርዲናሎች ጉባኤ 208 ካርዲናሎችን ያቀፈ ሲሆን ከነዚህም መካከል 117ቱ በዕድሜ ገደብ መሠረት ቀጣይ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትን መምረጥ እና መመረጥ የሚችሉ ሲሆን የተቀሩት 91 በዕድሜ ገደብ መሠረት መምረጥም ሆነ መመረጥ የማይችሉ መሆናቸው ታውቋል።

28 May 2022, 17:00