ፈልግ

በጣሊያን ውስጥ ከፔሩጃ ክፍለ ሀገር ወደ አሲሲ ከተማ የተደረገ የእግር ጉዞ በጣሊያን ውስጥ ከፔሩጃ ክፍለ ሀገር ወደ አሲሲ ከተማ የተደረገ የእግር ጉዞ  

ካርዲናል ሚካኤል፣ ጥላቻ በበዛበት ዓለም ማኅበራዊ ግንኙነትን ማሳደግ እንደሚያስፈልግ አሳሰቡ

በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ ዕድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ፣ ብጹዕ ካርዲናል ሚካኤል ቼርኒ፣ ጥላቻ በበዛበት ዓለም ውስጥ ማኅበራዊ ግንኙነትን መገንባት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። በጣሊያን ውስጥ ከፔሩጃ ክፍለ ሀገር ወደ አሲሲ ከተማ የሚደረገውን የእግር ጉዞ ምክንያት በማድረግ፣ ሚያዝያ 15/2014 ዓ. ም. በተካሄደው የጸሎት ሥነ-ሥርዓት ላይ የተገኙት ብጹዕ ካርዲናል ሚካኤል፣ በተለይ በዚህ የጦርነት ጊዜ ወንድማማችነትን እና እርቅ ሊያስገኙ በሚችሉ እና የቅዱስ ከወንጌል መርሆችን በሚከተሉ ሁለት ሃሳቦች ላይ አስተንትኖአቸውን አቅርበዋል። አስተንትኖን ያደረጉባቸው ሁለቱ ሃሳቦችም፣ በእርስ በእርስ ጥላቻ ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው እና በስልጣን ለሚመኩት በሙሉ በርኅራሄ የተሞላ ልብ ሊኖረን ይገባል የሚሉ መሆናቸው ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ከፔሩጃ ወደ አሲሲ የሚደረገውን የሰላም የእግር ጉዞ ቅድመ ዝግጅት ምክንያት በማድረግ ቅዳሜ ሚያዝያ 15/2014 ዓ. ም. በአሲሲ ከተማ የቀረበውን የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት፣ በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ ዕድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ፣ ብጹዕ ካርዲናል ሚካኤል ቼርኒ የመሩት ሲሆን፣ በመስዋዕተ ቅዳሴው ወቅት ባሰሙት ስብከትም፣ ጦርነት፣ ጥላቻ እና ጨለማ በነገሠበት ዓለም ውስጥ ወንድማማችነትን ማሳደግ እንደሚያስፈልግ ጥሪ አቅርበዋል።

ጦርነት የሚያስከትለውን ግፍ ማስታወስ ያስፈልጋል

ብጹዕ ካርዲናል ሚካኤል በመጀመሪያው አስተንትኖአቸው፣ በደቀ መዛሙርቱ መካከል የነበረውን ፉክክር በሚያጎላ በቅዱስ ወንጌል ክፍል ላይ በማትኮር፣ በጦርነት ድልን ለማግኘት የሚደረገው ሩጫ መቆም እንደሚያስፈልግ ምክንያቱም ውጤቱ እራስ ከማጥፋት አልፎ ሁሉንም ማኅበራዊ ግንኙነቶችን እንደሚያበላሽ አስረድተዋል።

በየጊዜው የሚደርሱንን የጦርነት አሰቃቂ ዜናዎችን ያስታወሱት ብጹዕ ካርዲናል ሚካኤል፣ የተጠራነው ከጦነት ይልቅ የሰላምን መንገድ ለመከተል እንደሆነ ገልጸው፣ ለሰላም ብለን በምናደርጋቸው ጥቃቅን ሥራዎች ወደ ስብዕናችን መመለስ ያስፈልጋል ብለዋል። በጥላቻ እና በዓመፅ በተበከለው ዓለም ውስጥ፣ በጋራ ፍቅር ላይ የተመሠረተ ሰብዓዊ ግንኙነትን ለመገንባት ተጠርተናል ብለዋል። ስልጣን የብዙዎችን ልብ ያደነደነ ቢሆንም፣ እኛ ግን ሌሎች ለማስደሰት እና አንዳችን ለሌላው አገልጋይ እንድንሆን የሚጋብዘንን የኢየሱስ ክርስቶስ ቃል ለማድመጥ ተጠርተናል ብለዋል። እራሳችንን ከፍ በማድረግ ሌሎችን ከመጨቆን ይልቅ በትህትና እንድናገለግል፣ የኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌነትም ይህ መሆኑን አስረድተዋል።  ሌሎችን ማገልገል የእኛን ፍትህ እንደማያጠፋ፣ ነገር ግን ፍቅር እና ወንድማማችነት የሚያመጣውን መልካም ፍሬ እንድንመለከት ይጋብዘናል ብለዋል። ሁልጊዜ ለእርቅ የሚጋብዝ፣ የጦርነትን አስከፊነት የሚገልጽ ትውስታ በልባችን ውስጥ እንዲቀመጥ በማለት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ያቀረቡትን መልዕክት ጠቅሰዋል።

እግዚአብሔር ቁስላችንን ያያል

ብጹዕ ካርዲናል ሚካኤል፣ በቅዱስ ወንጌል የተጠቀሰውን የደጉ ሳምራዊ ታሪክ በሚያስታወሰው ሁለተኛው አስተንትኖአቸው፣ እግዚአብሔር ስቃያችንን ተመልክቶ እንባችንን እንደሚያብስ፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም የቁስላችንን ሕመም ለማስታገስ መምጣቱን አስረድተዋል። ወደ ገደል የሚወሰደንን የጨለማ ጉዞ አስታወሰው፣ አንዳንድ ጊዜ መረዳት ወደማይቻል የሕይወት ገደል ስንወርድ፣ የኃጢአት ጭቆና ሲበዛብን፣ የክስተቶችን ትርጉም ማወቅ ሲቸግረን፣ ደካማ ሕይወታችን በጦርነት ሲቆስል፣ ማግለል፣ ጥላቻ እና ቂም በዓለማችን ውስጥ ግጭቶችን እና ጦርነቶችን ሲቀሰቀስ፣ በዚህም ሁል ጊዜ በመንፈስ እና በስጋ ስንቆስል፣ የቆሰለው የሰው ልጅ ብቻ ሳይሆን ኢየሱስ ክርስቶስም እራሱን ከሌሎች ዝቅ በማድረግ መቁሰሉን አስታውሰዋል።

በስልጣን ለሚመኩት የርኅራሄ ልብ ሊኖረን ይገባል

በመንፈስ ጠንካሮች እንድንሆን የሚያደርገንን የኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ መከተል ያስፈልጋል ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ሚካኤል፣ ማናችንም ብንሆን በዙሪያችን ለሚሆነው ነገር እና በወንድሞቻችን ላይ ለሚፈጠሩ ቁስሎች ደንታ ቢሶች መሆን የለብንም ብለዋል። በእግዚአብሔር ቃል ላይ ያለንን አመለካከት ከግምት ውስጥ ማስገባት እንደሚያስፈልግ አሳስበው፣ ለሃይማኖታዊ ተግባራት ብቻ በመጨነቅ የወንድሞቻችንን ጩኸት አለማዳመጥ አደጋ ውስጥ ሊጥለን እንደሚችል አስጠንቅቀዋል። “ለባልንጀራ ከሚገለጽ ፍቅር እና መተሳሰብ የሚበልጥ ሃይማኖት የለም” ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ሚካኤል፣ ባልንጀራችን እኛ የምንመርጠው፣ መርጠን የምንወደው ወይም የምናዝንለት ሳይሆን በሕይወት ጉዞአችን የሚያጋጥመን ማንኛውም ሰው ባልንጀራችን እንደሆነ አስረድተዋል።

በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ ዕድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ፣ ብጹዕ ካርዲናል ሚካኤል ቼርኒ፣ አስተንትኖአቸውን ሲያጠቃልሉ፣ በበርካታ ንጹሐን ሰዎች ላይ እየደረሰ ያለውን ስቃይ በማስታወስ፣ ትንሽም ቢሆን በዕለት ተዕለት ሕይወታችን የሰላም ባሕልን ማሳደግ እንደሚያስፈልግ ገልጸው፣ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ “በወንድሞቻችን እና በእህቶቻችን ሕይወት ሁላችንም ተጠያቂዎች ነን” ማለታቸውን ጠቅሰው፣ በእርስ በእርስ ጥላቻ ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው እና በስልጣን ለሚመኩት በሙሉ በርኅራሄ የተሞላ ልብ ሊኖረን እንደሚገባ በማሳሰብ አስተንትኖአቸውን ደምድመዋል።

25 April 2022, 17:41