ፈልግ

በቅድስት መንበር እና በጣሊያን መንግሥት መካከል የተፈረመው የላተራን ስምምነት መታሰቢያ በቅድስት መንበር እና በጣሊያን መንግሥት መካከል የተፈረመው የላተራን ስምምነት መታሰቢያ   (Vatican Media)

በዩክሬን እየተካሄደው ያለው ጦርነት ከፍተኛ ስጋትን የፈጠረ መሆኑ ተገለጸ

በቅድስት መንበር እና በጣሊያን መንግሥት መካከል የተፈረመውን የላተራን ስምምነት መታሰቢያ ዓመታዊ ክብረ በዓል ትናንት መጋቢት 6/2014 ዓ. ም. ተከብሯል። በሥነ-ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የቅድስት መንበር እና የጣሊያን መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት፣ በዚህ ወቅት በዩክሬን እየተካሄደ ያለው ጦርነት ከፍተኛ ስጋትን የፈጠረ መሆኑ ገልጸዋል። በአጋጣሚው ከተነሱት ርዕሰ ጉዳዮች መካከል እ. አ. አ በ2025 ዓ. ም. የሚከበረው የኢዮቤልዩ በዓል፣ ለቤተሰብ ስለሚሰጥ ድጋፍ እና ለስደተኞች ሊሰጥ ስለሚገባው ድጋፍ መሆኑ ታውቋል። ከዚህ በተጨማሪ በዩክሬን እየተካሄደ ያለው ጦርነት እና በሊባኖስ ያለው ሁኔታ ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶበታል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በቅድስት መንበር የጣሊያን ኤምባሲ ውስጥ ተገኝተው ከጋዜጠኞች ለተነሱት ጥያቄዎች መልስ የሰጡት የቅድስት መንበር ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍል ዳይሬክተር አቶ ማቴዮ ብሩኒ ሲሆኑ፣ በቅድስት መንበር እና በጣሊያን መንግስት መካከል የተፈረመውን የላተራን ስምምነቶች አስመልክቶ የተነሱትን ዋና ዋና መሪ ሃሳቦችን አብራርተዋል።

ክቡር አቶ ብሩኒ በማብራሪያቸው ስለ ዓለም አቀፍ ሁኔታ ልዩ ትኩረትን የሰጡ ሲሆን፣ ከሁሉም በላይ በዚህ ወቅት በዩክሬን ውስጥ እየተካሄደ ያለው ጦርነት አሳሳቢነት እና በሊባኖስ ውስጥ ያለውንም ቀውስ ጠቅሰዋል። ከዚህ አንፃር የስደተኞችን የኑሮ ሁኔታ የበለጠ ሰብዓዊነት እንዲኖረው ለማድረግ የጋራ ጥረት እንደሚያስፈልግ፣ በተለይም ጦርነቱን የሚሸሹ ሰዎችን በተመለከተ፣ አቋርጠው የሚሄዱባቸውን አገሮች ድጋፍ እና ስደተኞችን ተቀብለው የሚያስተናግዱ ግለሰቦች እና አገራት ላይ አጽንዖት ሰጥተዋል።

የቅድስት መንበር ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍል ዳይሬክተር አቶ ማቴዮ ብሩኒ ከተናገሯቸው ሌሎች ርዕሰ ጉዳዮች መካከል እ. አ. አ በ2025 ለሚከበረው የኢዮቤልዩ ክብረ በዓል በቂ ዝግጅት እንዲደረግ፣ በጣሊያን ውስጥ የሚቀርቡ አገልግሎቶችን በተመለከተ ከ ጣሊያን ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ እና ከሮም ሀገረ ስብከት ጋር በመተባበር፣ በቫቲካን ወደሚገኘው ቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ለሚመጡት ነጋዲያን ሊደረግላቸው የሚገባውን አቀባበል ያስታወሱ ሲሆን፣ በተጨማሪም ለቤተሰብ ሕይወት እና ለትምህርት ቤቶች ሊሰጥ ስለሚገባው ድጋፍም አንስተው ተናግረዋል።

16 March 2022, 15:44