ፈልግ

ብፁዕ ካርዲናል ኮንራድ ወደ ዩክሬን ግዛት ዘልቀው ገብተዋል ብፁዕ ካርዲናል ኮንራድ ወደ ዩክሬን ግዛት ዘልቀው ገብተዋል 

ብጹዕ ካርዲናል ኮንራድ፣ የዩክሬን ስደተኞችን የሚቀበሉ ጎረቤት አገራትን አመሰገኑ

“ጥርጣሬ የሌለው እምነት ተራራን ማንቀሳቀስ ይችላል” ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ኮንራድ ክራዬቭስኪ፣ በጦርነት ምክንያት የሚሰደዱ በርካታ የዩክሬን ሕዝቦችን ለሚቀበሉ ጎረቤት አገራት ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል። በሰሜን ምዕራብ ዩክሬን ጉብኝት በማድረግ ላይ የሚገኙ፣ በቫቲካን የር. ሊ. ጳ በጎ አድራጎት ተግባር ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ ብጹዕ ካርዲናል ኮንራድ ክራዬቭስኪ፣ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የዩክሬን ህዝብ በስቃይ ውስጥ እና በስደት ላይ እንደሚገኝ ያውቃሉ ብለው፣ በየቀኑ በሚያቀርቡት ጸሎት የሚያስታውሷቸው መሆኑን ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የር. ሊ. ጳ በጎ አድራጎት ሥራ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ ብጹዕ ካርዲናል ኮንራድ፣ በዩክሬን ውስጥ ለሚገኙ የጦርነት ሰለባ ለሆኑት ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የተላከላቸውን የዕርዳታ ቁሳቁሶችን በማከፋፈል ላይ እንደሚገኙ ታውቋል። በሌዎፖሊ ከተማ የሚገኙ ተፈናቃዮችን ከጎበኟቸው በኋላ በሰሜን ምዕራብ ወደምትገኝ የሪቪን ከተማ ደረሰው፣ በከተማው በሚገኙ መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ የሚገኙ ተፈናቃዮችን መጎብኘታቸው ታውቋል። በከተማው ውስጥ በተዘጋጀው የአብያተ ክርስቲያናት የሰላም ጸሎት ላይ በመገኘት፣ ተፈናቃዮችን በማገልገል ላይ ከሚገኙ በጎ ፈቃደኞች ጋርም መገናኘታቸው ታውቋል።

ብጹዕ ካርዲናሉ ከጋዜጠኞች ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለዩክሬን ሕዝብ ያላቸውን ወዳጁነት በድጋሚ በመግለጽ፣ መላውን ዓለም በማስተባበር ለዩክሬን ሰላም ጸሎት በማድረግ ላይ መሆናቸውን አስረድተዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዓርብ የካቲት 18/2014 ዓ. ም. ሮም በሚገኝ የሩሲያ ኤምባሲ ተገኝተው በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል የተቀሰቀሰውን ጦርነት አስመልክተው ከተኩል ሰዓት በላይ ውይይት ማድረጋችውን ያስታወሱት ብጹዕ ካርዲናል ኮንራድ፣ ቅዱስነታቸው በዕለቱ ባደረጉት ውይይት "ንጹሃን ሰዎች እንዳይሞቱ በማለት ምሕረትን መጠየቃቸውን አስረድተዋል። “እምነት ተራራን ማንቀሳቀስ ይችላል” የሚለውን የቅዱስ ወንጌል መርህ ቅዱስነታቸው እንደሚከተሉ የተናገሩት ብጹዕ ካርዲናል ኮንራድ፣ “መሣሪያችን እምነት ነው” ብለው፣ “ከእግዚአብሔር ዘንድ ምሕረትን እና ለዩክሬን ሕዝብ ሰላሙን ማግኘት የምንችለው በእግዚአብሔር ካመንን ብቻ ነው” በማለት አስረድተዋል።

የር. ሊ. ጳ በጎ አድራጎት ሥራ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ ብጹዕ ካርዲናል ኮንራድ፣ ቀጥለውም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለዩክሬን ሕዝብ በየዕለቱ እንደሚጸልዩ፣ ተልዕኮአቸውም ይህን ለዩክሬን ሕዝብ ለማስታወቅ እንደሆነ ገልጸዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዩክሬን እየሆነ ያለውን ነገር በሙሉ፣ የዜጎቹን ዕለታዊ ስቃይ እና ሽሽት በሚገባ የተገነዘቡት መሆናቸውን አስረድተዋል። ብጹዕ ካርዲናል ኮንራድ በመጨረሻም ስደተኞችን ተቀብለው አስቸኳይ ሰብዓዊ ዕርዳታን በማቅረብ ላይ ለሚገኙ የአውሮፓ አገራት ምስጋናቸውን አቅርበው፣ ለመላው የዩክሬን ሕዝብ ሰላምታን በማቅረብ የእግዚአብሔርን ቡራኬ ተመኝተውላቸዋል።

12 March 2022, 16:05