ፈልግ

ለክርስቲያኖች አንድነት የሚውል የጸሎት ሳምንት ለክርስቲያኖች አንድነት የሚውል የጸሎት ሳምንት 

ለክርስቲያኖች አንድነት እና ሐዋርያዊ ሲኖዶስ ጸሎት እንዲደረግ ጥሪ ቀረበ

ዘንድሮ ከጥር 10-17/2014 ዓ. ም. በሚከበረው የክርስቲያኖች አንድነት ሳምንት ምዕመናን ጸሎታቸውን እንዲያቀርቡ እና የጋራ ጉዞአቸውን እንዲቀጥሉ በማለት የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ጠቅላይ ጸሐፊ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ማርዮ ግሬሽ እና በቅድስት መንበር የክርስቲያኖች ሕብረት ማጠናከሪያ ጳጳሳዊ ምክር ቤት ፕሬዚደንት፣ ብጹዕ ካርዲናል ኩርት ኮክ አሳሰቡ አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ሁለቱ የጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቶች አስተባባሪዎች ጥቅምት 18/2014 ዓ. ም. በመላው ዓለም ለሚገኙ የክርስቲያኖች አንድነት እንቅስቃሴ አስተባባሪ ብጹዕን ጳጳሳት በላኩት መልዕክት፣ በየአገራቱ በሚገኙ ካቶሊካዊ ሀገረ ስብከቶች ውስጥ ያለውን ሲኖዶሳዊ ሂደት እና የክርስቲያኖች አንድነት እንቅስቃሴ ይዘትን ተግባራዊ ለማድረግ ያለሙ ሃሳቦችን አቅርበዋል። ሁለቱ ብጹዓን ካርዲናሎች፣ ብጹዕ ካርዲናል ማርዮ ግሬሽ እና ብጹዕ ካርዲናል ኩርት ኮክ ለብጹዓን ጳጳሳቱ በላኩት መልዕክት፣ ሲኖዶሳዊነት እና የክርስቲያኖች አንድነት አብረው የሚከናወኑ ሂደቶች መሆናቸውን ገልጸው፣ የክርስቲያኖች አንድነት እንደ ስጦታ መለዋወጥ ስለሚረዳ፣ ካቶሊኮች ከሌሎቹ ክርስቲያኖች ሊቀበሉ ከሚችሏቸው ስጦታዎች መካከል አንዱ በሲኖዶሳዊነት ያላቸውን ልምድና ግንዛቤ ነው ብለዋል።   

ከዛሬ ጥር 10-17/2014 ዓ. ም. ድረስ የሚቆየው የክርስቲያኖች አንድነት የጸሎት ሳምንት፣ መሲሁን ኢየሱስ ክርስቶስ ለማመስገን ከምሥራቅ ወደ ቤተልሔም የመጡት ሰብዓ-ሰገሎች፣ በማቴ. 2:2 እንደተገልጸው፣ “ኮከቡን በምሥራቅ አይተን ለእርሱ ልንሰግድለት መጣን” የሚለው ጥቅስ፣ ሐዋርያዊ ሲኖዶሱ ክርስቲያናዊ አንድነትን እንዲያጎለብት ከመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች ጋር ለመጸለይ መልካም አጋጣሚን እንደፈጠረ ታውቋል።

ክርስቲያናዊ እሴቶቻችንን ይፋ ማድረግ

“ኮከቡን በምሥራቅ አይተን ለእርሱ ልንሰግድለት መጣን” በሚለው የዘንድሮ መሪ ሃሳብ ያስተነተኑት የሁለቱ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቶች አስተባባሪዎች በበኩላቸው፣ 

“እንደ ሰብአ ሰገል፣ ክርስቲያኖችም አብረው በአንድ ሰማያዊ ብርሃን እየተመሩ ዓለማዊ ጨለማን ለማሸነፍ  አብረው ኢየሱስን እንዲያመልኩ እና ክርስቲያናዊ ሃብታቸውን ይፋ እንዲያደርጉ መጠራታቸውን አስረድተዋል። በኢየሱስ ክርስቶስ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን የሆኑት ክርስቲያኖች አንድነታቸውን በመገንዘብ በእነዚህ ሁለት ዓመታት ውስጥ አብረውን እንዲጓዙ በማለት ጥሪያቸውን አቅርበው፣ መንፈሳዊ ሀብቶቻችንን ለሁሉ በመክፈት ስጦታዎችን መለዋወጥ እንደሚቻል ከልብ ተስፋ እናደርጋለን ብለው፣ አንድነትን ለማሳደግ የሚያስችል ኃይል እና ብርታት መንፈስ ቅዱስ ለሁሉም ክርስቲያኖች ሰጥቶናል ብለዋል።

ጸሎት ለክርስቲያን አንድነት እና የጋራ ጉዞ

የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት እና በቅድስት መንበር የክርስቲያኖች ሕብረት ማጠናከሪያ ጳጳሳዊ ምክር ቤት በኅብረት ለጸሎት ሳምንት ሃሳብ ተጨመሪ እንዲሆን የሚከተለውን ጸሎት አዘጋጅተው ይፋ አድርገዋል።

ሰማያዊ አባት ሆይ!

ሰብዓ ሰገል በኮከቡ እየተመሩ በኅብረት ወደ ቤተልሔም እንደተጓዙ፣ በዚህ የሲኖዶሳዊ ጉዞ ወቅት ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያንም ከሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ጋር በኅብረት መጓዝ እንድትችል የአንተን ሰማያዊ ብርሃን እንለምናለን። ሰብአ ሰገል አንድ ላይ ለሕጻኑ ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሰገዱለት፣ እኛም ወደ ልጅህ ቀርበን፣ መንፈሳዊ ሀብቶቻችንን ገልጠን ስጦታዎችን ለመለዋወጥ ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ምራን። በዚህም እግዚአብሔር ለቤተክርስቲያኑ እና ለፍጥረታቱ በሙሉ የሚፈልገው የአንድነት ምልክት እንሆን እርዳን። ይህን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል እንለምንሃለን። አሜን።    

18 January 2022, 16:17