ፈልግ

በአየር ንብረት ለውጥ ላይ የተደረገ 26ኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጉባኤ በአየር ንብረት ለውጥ ላይ የተደረገ 26ኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጉባኤ 

ቅድስት መንበር፣ በአየር ንብረት ጉባኤ ላይ መሻሻል ቢታይበትም ለተግባራዊነቱ ጊዜው አጭር መሆኑን ገለጸች

በእንግሊዝ ግላስጎው ከተማ ከጥቅምት 21 - ኅዳር 3/2014 ዓ. ም. ሲካሄድ የቆየው 26ኛ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጉባኤ፣ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የሚያስችሉ ተባራትን ለማከናወን ስምምነት ላይ መድረሱ ታውቋል። ጉባኤው በአንዳንድ ስምምነቶች ላይ ቢደርስም ለተግባራዊነቱ ያለው ጊዜ አጭር መሆኑን ጉባኤውን የተካፈለው የቅድስት መንበር ልዑካን ቡድን አስታውቋል። የቅድስት መንበር ልዑካን ቡድን ጉባኤው የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም በገባው ቃል ያለውን አድናቆት ገልጾ፣ ሆኖም ግን ልዑካን ቡድኑ የተከሰቱትን ክፍተቶች ለመሙላት ግልጽ በሆነ ፍኖተ ካርታ ላይ የተቀመጠ ስምምነት እንደሚያስፈልግ በድጋሚ ገልጿል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የአየር ንብረት ለውጥን በማስመልከት ከጥቅምት 21 - ኅዳር 3/2014 ዓ. ም. በእንግሊዝ ግላስጎው ከተማ ሲካሄድ የቆየው 26ኛ የተባበሩት መንግሥታት ጉባኤ በመግለጫው፣ የዓለም ሙቀት መጨመርን ለመዋጋት የዓለም መንግሥታት ቃል መግባታቸውን ያስታወቀ ሲሆን መንግሥታቱ ለገቡትው ቃል የቅድስት መንበር ልኡካን ቡድኑ አድናቆቱን ገልጿል።

ተጨማሪ ሥራ መሰራት አለበት

የቅድስት መንበር የዓለም አማካይ የሙቀት መጠን ከኢንዱስትሪዎች መስፋፋት በፊት በነበረበት በ 1.5 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ለመገደብ መንግሥታት ያላቸውን ቁርጠኝነት መግለጻቸውን ልዑካን ቡድኑ አስታውቆ፣ ይህን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስፈልግ የገንዘብ ዕርዳታ ምንጭ ተስፋ ሰጭ መሆኑን ገልጿል። ቡድኑ አክሎም “የአየር ንብረት ለውጥን በ1.5 ድግሪ ሴንቲ ግሬድ መገደብ ለአደጋ ተጋላጭ ለሆኑ ማህበረሰቦች ህልውና እጅግ አስፈላጊ ነው" ብሏል። 

“ሊሠሩ የሚገቡ በርካታ ተጨማሪ ሥራዎች አሉ” ያለው የቅድስት መንበር ልኡካን ቡድኑ፣ "የተገቡትን ቃል ኪዳኖች ተግባራዊ ለማድረግ እና ውጤታማ መንገዶችን ለማግኘት ንቁ መሆን ያስፈልጋል" ሲል አፅንዖት ሰጥቷል። 26ኛውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጉባኤ የተካፈለው የቅድስት መንበር ልኡካን ቡድን፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ የጋራ መኖሪያ ምድራችን ደህንነት በማስመልከት የላኩትን መልዕክት ለጉባኤው በማቅረብ፣ የአየር ንብረት ቀውሱ በድሆች ላይ ያደረሰውን ተጽእኖ እና ጉዳቱ እንዲደርስ በትንሹም ቢሆን አስተዋጽዖ ያበረከቱትን አጽንዖት ሰጥተው መናገራቸውን ገልጿል።

"ክፍተቶች" ስለ መኖራቸው

ጉባኤው በተካሄደባቸው ሁለት ሳምንታት ውስጥ የታዩት ክፍተቶች፣ ጉዳዩን ቀላል አድርጎ መወሰድን፣  የአየር ንብረት ለውጥ ችግርን ለማቃለል ያለው የገንዘብ ዕርዳታ ቀንሶ መገኘት እና ለተግባራዊነቱ እንቅፋቶች መኖራቸውን አጉልቶ የሚያሳይ እንደነበር የቅድስት መንበር ልኡካን ቡድን ገልጿል። የቅድስት መንበር ልኡካን ቡድን ሪፖርት በመቀጠል "የፓሪሱን ስምምነት ዓላማዎች ለማሳካት መሠረታዊ የሆኑት እነዚህን ሦስት ገፅታዎች ለማስተካከል የሚረዱ ግብዓቶች ተጠናክረው ሊታደሱ ይገባል" በማለት አሳስቧል።

ግልጽ መመሪያ ያስፈልጋል

የቅድስት መንበር ሪፖርት በማከልም “የበለጸጉ አገሮች ግንባር ቀደም ሆነው እነዚህን ክፍተቶች ለመድፈን የሚያግዝ ግልጽ የሆነ መመሪያ ለማዘጋጀት 26ኛ የተባበሩት መንግሥታት ጉባኤ በቅርቡ ከስምምነት ላይ እንደሚደርስ ያለውን ተስፋ ገልጿል። ከዚህ በፊት፣ የሐይማኖት መሪዎች እና የሳይንስ ባለሞያዎች መስከረም 24/2014 ዓ. ም. የአየር ንብረት ለውጥን በማስመልከት ባደረጉት ስብሰባ፣ የአየር ንብረት ለውጡ በተለይም በድሃው ማኅበረሰብ ላይ የሚያስከትለው ጥፋት እና ጉዳት ከፍተኛ እንደሚሆን ማሳሰቡን የቅድስት መንበር ልኡካን ቡድኑ ጠቅሷል።  

ጊዜ መባከን የለበትም

በአየር ንብረት ለውጥ ላይ የተካሄደውን 26ኛ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጉባኤ የተካፈለው የቅድስት መንበር ልኡካን ቡድን በሪፖርቱ ማጠቃለያ ላይ፣ ጊዜ ወሳኝ መሆኑን በመግለጽ፣ የጉባኤው የመጨረሻ ውሳኔዎች "ለአሁኑ እና ለወደፊት ትውልዶች ባለው እውነተኛ የኃላፊነት ስሜት በመነሳሳት፣ ለጋራ መኖሪያ ምድራችን እንክብካቤን በማድረግ፣ ለምድሪቱ እና ለድሆችን ጩኸት መልስ እንደሚሰጥ ያለውን ተስፋ ገልጿል። 

16 November 2021, 16:28