ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ  እና የሰላም ምልክት፣ ዕርግብ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ እና የሰላም ምልክት፣ ዕርግብ  

55ኛው ዓለም አቀፍ የሰላም ቀን ትምህርትን፣ ሥራን እና የጋራ ውይይትን እንደሚያስቀድም ተገለጸ

በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ ዕድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት፣ ዘንድሮ ታኅሳስ 23/2014 ዓ. ም. የሚከበረውን 55ኛ ዓለም አቀፍ የሰላም ቀን በማስመልከት መልዕክት አስተላልፏል። ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቱ የዘንድሮ ዓለም አቀፍ የሰላም ቀን መልዕክት ዋና ርዕሥ፣ ዘላቂ ሰላምን ለመፍጠር ይረዳሉ ያሏቸው፥ ትምህርት፣ ሥራ እና በትውልዶች መካከል የሚደረግ ውይይት የሚሉ መሆናቸውን አስታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቱ በመግለጫው፣ “ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሁሉንም ሰው ለንባብ በመጋበዝ፣ ለዛሬው እና ለወደፊቱ ፍላጎቶች ምላሽ የሚሰጡ ሦስት ሰፊ አውዶችን ለይተው ማውጣታቸውን አስታውቆ፣ የዘመኑን ምልክቶች በእምነት ዓይን በማንበብ፣ የለውጡ አቅጣጫ አዲስና አንጋፋ ጥያቄዎችን በማቅረብ ፊት ለፊት መጋፈጥ ተገቢ እና አስፈላጊ ነው” በማለት አስረድቷል።

የቀረቡት ሦስት ጥያቄዎች

በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ ዕድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት፣  ከተለዩት ሦስቱ አውዶች በመነሳት የሚከተሉ ጥያቄዎችን በዋናነት አስቀምጧል፡- በዓለም ውስጥ ሥራ ለሰው ልጆች ፍትህን እና ነጻነትን በማስከበር፣ ይብዛም ይነስ አስፈላጊውን ምላሽ ይሰጣል? ትውልዶች እርስ በርስ በእውነት ይተባበራሉ? ወደፊት መልካም ጊዜ እንደሚመጣ ያምናሉ? በዚህ አውድ ውስጥ መንግሥታት የሰላም ተስፋን በመስጠት ተሳክቶላቸዋል ወይ? የሚሉ መሆናቸውን ገልጿል።

የዓለም የሰላም ቀን በቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ መልካም ምኞት በኅዳር ወር 1959 ዓ. ም. ባስተላለፉት ሐዋርያዊ መልዕክት የተቋቋመ ሲሆን በታኅሳስ ወር 1960 ዓ. ም. ለመጀመሪያ ጊዜ መከበሩ ይታወሳል።

16 November 2021, 16:37