ፈልግ

የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ በእንግሊዝ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ በእንግሊዝ 

ሥነ-ምሕዳራዊ ለውጥ የጋራ ጥቅምን መሠረት ያደረገ እንዲሆን ጥሪ ቀረበ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በእንግሊዝ ግላስጎው ከተማ ከጥቅምት 21 - ኅዳር 3/2014 ዓ. ም. የዓለም መንግሥታት መሪዎች በአየር ንብረት ለውጥ ላይ ለሚያካሂዱት ጉባኤ መልዕክት ማስተላለፋቸው ታውቋል። ቅዱስነታቸው ለጉባኤው ባስተላለፉት መልዕክት፣ ሥነ-ምሕዳራዊ ለውጥ የጋራ ጥቅምን ያገናዘበ እንዲሆን በማለት ጥሪ ማቅረባቸውን በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት አባል የሆኑት ክቡር አቶ ኒኮላስ ፊትዝፓትሪክ ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን 

ሦስት ዋና ዋና ነጥቦች

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከሌሎች የሐይማኖት መሪዎች ጋር በመተባበር ይፋ ያደረጉት ሰነድ እና ጥሪ በርካታ ርዕሠ ጉዳዮችን እንደያዘ የገለጹት አቶ ኒኮላስ፣ ሰነዱ ሦስት ዋና ዋና ርዕሠ ጉዳዮችን እንደያዘ፣ የመጀመሪያው በፓሪሱ ስምምነት በአንቀጽ 2.2 ላይ የተገለጸው እና የምድርን ሙቀት በ1.5 ድግሪ መገደብ የሚለው ስምምነት ተግባራዊ እንዲሆን የሚጠይቅ መሆኑን ገልጸዋል። በፓሪሱ ስምምነት የተገለጸው ሁለተኛ ርዕሠ ጉዳይ ሃብታም አገሮች በማደግ ላይ ለሚገኙ መካከለኛ ገቢ ላላቸው አገሮች የገንዘብ ድጋፍ እንዲያደርጉ የሚጠይቅ መሆኑን አቶ ኒኮላስ አስታውሰው፣ ይህም የቴክኖሎጂ ተደራሽነትን፣ እውቀትን ወይም ባለሞያን በአገር እና በዓለም አቀፍ ደረጃ መጋራትን የሚያካትት መሆኑን ጠቁመዋል።

በአየር ንብረት ውድቀት ታሪካዊ ሃላፊነት ትልቅ ሚናን እንደሚጫወት የገለጹት አቶ ኒኮላስ፣ እ. አ. አ ከ1850 ዓ. ም. ጀምሮ 92 ከመቶ የዓለማችን የጋዝ ልቀቶች የሚመነጨው በኤኮኖሚ ከበለጸጉ አገሮች እንደሆነ፣ ከዚህ መካከል 40 ከመቶ የሚሆነው ከሰሜን አሜሪካ፣ 29 ከመቶ ከአውሮፓ ኅብረት አገሮች፣ 10 ከመቶ የሚሆነው ከሌሎች የአውሮፓ አገሮች እና የተቀረው ጃፓን እና አውስትራሊያ ከመሳሰሉ ያደጉ አገሮች የሚመነጭ መሆኑን አስረድተው፣ በመሆኑም እውነት ስለ ፍትህ እና ዘላቂ ዕድገት የምንነጋገር ከሆነ “የበለጸጉ አገሮች ላስከተሉት የሥነ-ምህዳር ጉዳት ማካካሻ ማቅረብ አለባቸው” ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የሥነ-ምህዳር ዕዳን መክፈል አስፈላጊ እንደሆነ ብዙ ጊዜ መናገራቸውን ያስታወሱት አቶ ኒኮላስ፣ ቅዱስነታቸው የካርቦን ልቀቶች ዕዳን በከፊል ይጥቀሱ እንጂ የተፈጥሮ ሃብት እና የአየር ንብረት ዕዳዎች እንዳሉ መናገራቸውን አስረድተዋል። እነዚህ ሁለቱን ከተናገሩ በኋላ በመጨረሻ የገለጹት ርዕሠ ጉዳይ ፍትሃዊ የስነ-ምህዳር ሽግግርን ማረጋገጥ እንደሆነ እና ይህንን ለማድረግ የብዙ ሰዎች የዕለት ሥራ ከነዳጅ ኃይል ጋር ተያያዥነት ባላቸው ኢንዱስትሪዎች እንደሚመካ የሚታወቅ ቢሆንም ከቅሪተ አካል ነዳጅ አጠቃቀም ወደ ንጹሕ ኃይል አጠቃቀም መሸጋገር እንደሚያስፈልግ መዘንጋት የለብንም ብለዋል።

መፍትሄው ከንግድ ጋር መያያዝ የለበትም

ለችግሩ መፍትሄን ማግኘት የሚቻለው እንዴት ነው ተብለው ለተጠየቁት መልስ የሰጡት አቶ ኒኮላስ፣ መፍትሔው እንደተለመደው ከንግድ ጋር የተያያዘ እንደሆነ ገልጸው፣ አሁን ያለው የኢንዱስትሪ አዝማሚያ በአገሮች ውስጥ ያለውን ልዩነት እንዳባባሰው እና በተቋም ደረጃ ያለው ግንዛቤ እየጨመረ ቢመጣም የጎጂ ጋዝ ልቀት መጠን ከጊዜ ወደ ጊዜ መጨመሩን አስረድተዋል። የአየር ንብረት ለውጥን በማስመልከት እ. አ. አ 1990 ዓ. ም. የታተመው የተባበሩት መንግሥታት ሪፖርት እንደሚያሳየው ሪፖርቱ ይፋ ከተደረገበት ጊዜ ወዲህ የታየው የጋዝ ልቀት መጠን 60 ከመቶ መጨመሩን ገልጸዋል። ይህ የሚያሳየው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች “ዓለም አቀፍ ዕቅዶች እና የልቀት መጠን መቀነስ ስኬታማ” የሆኑበት ሳይሆን “የሃያላን አገሮች ውሳኔ የመስጠት አቅም እና ፖሊሲዎች የሚጋጩበት” መሆኑን አስረድተዋል።

የተቀናጀ ሥነ-ምህዳር

የዓለም መንግሥታት መሪዎች በአየር ንብረት ለውጥ ላይ በእንግሊዝ ግላስጎው ከተማ ከጥቅምት 21 - ኅዳር 3/2014 ዓ. ም. ድረስ ከሚካሄደው ጉባኤ የሚጠበቀው፣ እ. አ. አ. በፈረንሳይ ፓሪስ ከተማ የተደረሰው ስምምነት ተግባራዊነት እንደሆነ አቶ ኒኮላስ ገልጸዋል። በፓሪሱ ጉባኤ ላይ የጋራ መኖሪያ ምድራችንን ከጥፋት መከላከልን አስመልክተው ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ “ውዳሴ ላንተ ይሁን” በማለት ባቀረቡት ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን በኩል ለሰው ልጅ አስተሳሰብ እና ለሥነ ምግባር ጠቃሚ መመሪያዎችን ማቅረባቸውን አቶ ኒሎካስ አስታውሰዋል።

ሥነ-ምሕዳርን አስመልክቶ የሚደረግ እያንዳንዱ ውይይት ህዝብን እና ማህበራዊ ፍትህን ያማከለ መሆን አለበት ብለው፣ “ሥነ-ምህዳራዊ ለውጥ” ሊመጣ የሚችለው “ውዳሴ ላንተ ይሁን” በሚለው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን እና በሌሎች ተመሳሳይ መርሃ ግብሮች ላይ ሰዎች ተገናኝተው መወያየት ሲችሉ ነው ብለዋል።

ማኅበራዊ ለውጥ የሚመጣው ከስር እንደሆነ የገለጹት አቶ ኒኮላስ፣ ሌሎች ሰዎችን በማነሳሳት መፍትሄዎችን በማኅበር ማዘጋጀት እንደሚያስፈልግ ተናግረው፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የአየር ንብረት ቀውስን ስለመቅረፍ ሲናገሩ በጎ ፈቃድ ያላቸውን ሁሉ የጋበዙት በዚህ ምክንያት መሆኑን በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ ዕድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት አባል የሆኑት ክቡር አቶ ኒኮላስ ፊትዝፓትሪክ ገልጸዋል።

02 November 2021, 16:08