ፈልግ

ብጹዕ ካርዲናል ሚገል አንገል ኣዩሶ ብጹዕ ካርዲናል ሚገል አንገል ኣዩሶ  

የካርዲናል አዩሶ ሐዋርያዊ ጉብኝት በሐይማኖቶች መካከል ውይይት መኖሩን ይገልጻል ተባለ

በጳጳሳዊ ምክር ቤት፣ የሐይማኖት ተቋማት የጋራ ውይይት አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት ፕሬዚደንት የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ሚገል አንገል ኣዩሶ በሞስኮ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን በማድረግ ላይ መሆናቸው ታውቋል። ከሩሲያ መንግሥት በኩል በቀረበላቸው ግንዣ መሠረት ማክሰኞ ኅዳር 15/2014 ዓ. ም. ወደ ሞስኮ የገቡት ብጹዕ ካርዲናል አዩሶ፣ ከሞስኮ ከተማ ሊቀ ጳጳስ ከብጹዕ አቡነ ሂላሪዮን እና ከሩሲያ ሙስሊም ማህበረሰብ ተወካዮች ጋር ተገናኝተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ብጹዕ ካርዲናል አዩሶ፣ በተዘጋጀላቸው የጉብኝት መርሃ ግብር መሠረት በዛሬው ዕለት ከመካከለኛው ምስራቅ አገራት ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፣ ከአፍሪካ ሀገራት ሚኒስትሮች እና ከእስላማዊ መንግሥታት ልዩ የትብብር ተወካዮች ጋር መገናኘታቸው ታውቋል። በጳጳሳዊ ምክር ቤት፣ የሐይማኖት ተቋማት የጋራ ውይይት አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት ፕሬዚደንት ብጹዕ ካርዲናል ሚገል አንገል ኣዩሶ፣ በሞስኮ በሚገኝ የቅድስት መንበር እንደራሴ አማካይነት ከሩሲያ ፌዴሬሽን መንግሥት በኩል በቀረበላቸው ግብዣ መሠረት ከትናንት ማክሰኞ ኅዳር 15/2014 ዓ. ም. ወደ ሞስኮ መግባታቸው ታውቋል። ከብጹዕ ካርዲናል አዩስ ጋር ሞስኮ የሚገኙት፣ የጳጳሳዊ ምክር ቤት ተወካይ ሞንሲኞር ሉሲዮ ሴምብራኖ እና በሞስኮ የቅድስት መንበር እንደራሴ ሞንሲኞር ፒዮተር ታርኖቭስኪ ሲሆኑ፣ ካርዲናሉ ሞስኮ ከደረሱ በኋላ ከልዩ ልዩ ባለስልጣናት ጋር ተገናኝተዋል። ትናንት ጠዋት በሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ሂላሪዮን የክብር አቀባበል የተደረገላቸው ሲሆን፣ ቀጥለውም ከሩሲያ ሙስሊሞች መንፈሳዊ ጉባኤ ፕሬዝዳንት ከሆኑት ሙፍቲ ራቪል ጋይንትዲን ጋር መገናኘታቸው ታውቋል።  

በሃይማኖቶች የጋራ ጥቅም ላይ ውይይት ተደርጓል

በሃይማኖቶች መካከል የሚደረግ የጋራ ውይይትን አስመልክቶ በቀረቡ የተለያዩ ንግግሮች ላይ ጨዋነትን የተላበሱ ውይይቶች የተካሂዱ ሲሆን፣ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዋና ዋና መሪ ሃሳቦች መካከል እ. አ. አ. በየካቲት ወር 2019 ዓ. ም. በአቡ ዳቢ ከተማ የተፈረመው የ “ሰብዓዊ ወንድማማችነት” ሰነድ እና “ሁላችንም ወንድማማቾች ነን” የተሰኙ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳኖችን መመልከታቸው ታውቋል። ምሽት ላይ በሞስኮ ከተማ ካቶሊካዊ ሊቀ ጳጳስ በብጹዕ አቡነ ፓውሎ ፔሲ አቀባበል የተደረገላቸው ብጹዕ ካርዲናል አዩሶ በከተማው በሚገኝ እጅግ ንጽሕት ማርያም ካቴድራል ውስጥ ተገኝተው በሥፍራው ለተገኙት ምዕመናን የመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት መርተዋል። 

በጳጳሳዊ ምክር ቤት፣ የሐይማኖት ተቋማት የጋራ ውይይት አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት ፕሬዚደንት የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ሚገል አንገል ኣዩሶ በዛሬው ውሎአቸው፣ ከመካከለኛው ምስራቅ አገራት ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፣ ከአፍሪካ ሀገራት ሚኒስትሮች እና ከእስላማዊ መንግሥታት ልዩ የትብብር ተወካዮች ጋር መገናኘታቸው ታውቋል። ብጹዕ ካርዲናል እንደዚሁም ከሩሲያ ፌዴሬሽን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ልዩ የእስልምና ግዛቶች ትብብር ተወካይ ከሆኑት አምባሳደር ኮንስታንቲን ሹቫሎቭ ተገናኝተው አናሳ ቁጥር ያላቸው ምዕመናን መብት መከበር እና በተለይም የእምነት ነፃነትን በሚመለከቱ ጉዳይ ላይ መነጋገራቸው ታውቋል.

25 November 2021, 16:40