ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ከጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ መልስ በቫቲካን ውስጥ ከወጣት ሴቶች ጋር ሰላምታ ሲለዋወጡ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ከጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ መልስ በቫቲካን ውስጥ ከወጣት ሴቶች ጋር ሰላምታ ሲለዋወጡ 

ካርዲናል ፓሮሊን - ዓለማችን የሴቶች መሪነት እና ክህሎቶች የሚያስፈልገው መሆኑን ገለጹ

የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን፣ በጣሊያን በተዘጋጀው በኤኮኖሚ የበለጸጉ 20 አገሮች ሴቶች መድረክ መልዕክት ልከዋል። በሰሜን ጣሊያን ሚላን ከተማ ከጥቅምት 8-9/2014 ዓ. ም. ድረስ ለሁለት ቀናት የተዘጋጀው የሴቶች ጉባኤ መሪ ቃል “አዲሱን እና ሁሉ አቀፍ የመሪነት ዓላማን በማስተባበር ለሁሉም ኃይል እንድትሆን” የሚል እንደነበር ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በር. ሊ. ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ስም የቪዲዮ መልዕክታቸውን ያስተላለፉት የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን፣ የዛሬውን ግዙፍ ተግዳሮቶች ለመቋቋም ዓለም የሴቶች አጋርነት ፣ አመራር እና ክህሎቶች ያስፈልጋታል ብለው፣ በኤኮኖሚ የበለጸጉ 20 አገሮች  ቡድን የሴቶች መድረክ በጣሊያን በመዘጋጀቱ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል። 

በሰሜን ጣሊያን ሚላኖ ከተማ የተዘጋጀውን ስብሰባ የተካፈሉት የስብሰባው ተሳታፊዎች ዋና ዓላማ ፣ ሴቶች በሚጫወቱት ወሳኝ ሚና እና አዎንታዊ ተፅእኖ ላይ ግንዛቤን ለማሳደግ ሲሆን “አዲሱን እና ሁሉ አቀፍ የመሪነት ዓላማን በማስተባበር ለሁሉም ኃይል እንድትሆን” በሚለው የስብሰባው ጭብጥ ላይ በማተኮር፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ማገገምን ለማምጣት በሚደረጉ ጥረቶችን ላይ ውይይት መደረጉ ታውቋል። ዓለም በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ከፍተኛ ተግዳሮቶች ያጋጠመው መሆኑን አምነው፣ ዓለማችንን ካጋጠመው እና ብዙዎችን በአሰቃቂ ሁኔታ ውስጥ ካስገባው ቀውስ ለማገገም የተጎዱትን መርዳት እና አስፈላጊ ጥረቶችን ማድረግ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን በመልዕክታቸው “ሴቶች የጋራ መኖሪያ ምድራችንን በመገንባት የማይተካ አስተዋፅኦን እንደሚያበረክቱ፣ በተለይም በሕይወት ላይ የሚደርሱ ተጨባጭ ጫናዎችን በትዕግስት መሸከምን ያውቃሉ” በማለት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ብዙውን ጊዜ አፅንዖትን ሰጥተው የተናገሩትን ጠቅሰዋል። ዓለም አቀፍ ማህበራዊ ፣ ኤኮኖሚያዊ እና የአየር ንብረት ለውጥ ተግዳሮቶች በሚታዩበት በዚህ ወቅት፣ የራስ ወዳድነትን ስሜትን በማስወገድ፣ በተለይም ፈጣን ትርፋማነትን ብቻ ከሚመለከቱ አጭር ዕይታዎች ለመውጣት ሴቶች የሚጫወቱት ሚና አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።

የሁሉም ኅብረተሰብ አባላት ተሳትፎ እና ትብብር ወሳኝ እና አስፈላጊ መሆኑን የገለጹት ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን፣ የተሻለ ዓለምን ለመገንባት ሁሉም የጋራ ጥሪን ለመቀበል ተጠርተዋል ብለዋል። አክለውም ፣ ለእነዚህ ጥረቶች አስተዋፅኦን ለማበርከት የሰው ልጅ ስሜት እና የእያንዳንዱን ሰው ሰብዓዊ ክብር መታደስ ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብለዋል።

በመልዕክታቸው ማጠቃለያ “ልጃገረዶች እና ወጣት ሴቶች ለልማት እና ለማኅበራዊ ዕድገት እንዲያዘጋጃቸው ጥራት ያለውን ትምህርት ሊያገኙ ይገባል” በማለት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ያቀረቡትን ጠንካራ የማበረታቻ መልዕክት የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን አስታውሰዋል።

19 October 2021, 16:57