ፈልግ

ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን፣ በስሎቬኒያ የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ባሳረጉበት ዕለት ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን፣ በስሎቬኒያ የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ባሳረጉበት ዕለት 

ካርዲናል ፓሮሊን፣ “አውሮፓን በእውነት፣ በፍትህ፣ በነጻነት እና በፍቅር እንገንባት!”

የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን፣ የምሥራቅ አውሮፓ አገር በሆነች ስሎቬኒያ ውስጥ ሐዋርያዊ ጉብኝት በማድረግ ላይ መሆናቸው ታውቋል። በስሎቬኒያ፣ ብሬዜ ከተማ ውስጥ ነሐሴ 25/2013 ዓ. ም. ባሳረጉት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ሥነ-ሥርዓት ላይ ባቀረቡት ስብከት፣ አውሮፓን በእውነት፣ በፍትህ፣ በነጻነት እና በፍቅር መገንባት ያስፈልጋል ብለው፣ አውሮፓን እና መላውን ዓለም የፍቅር ምንጭ በሆነው በእግዚአብሔር ቃል በማነጽ ጠንካራ መሠረት እንዲኖራቸው ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የስሎቬኒያን ሕዝብ ጨምሮ መላው የአውሮፓ ሕዝብ በመንፈስ እና በሥጋ በሚሰቃይበት ባሁኑ ወቅት የእግዚአብሔርን ዕርዳታ መለመን እንደሚያስፈልግ፣ ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን በስብከታቸው ገልጸዋል። ብጹዕነታቸው ወደ ስሎቬኒያ ያደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ዓላማ አገሪቱ ከዩጎዝላቪያ ተለይታ የራሷን ነጻነት ያወጀችበት 30ኛ ዓመት እና የቀድሞ ር. ሊ. ጳ ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ወደ ስሎቬኒያ ሐዋርያዊ ጉብኝት ያደረጉበትን 25ኛ ዓመት ለማክበር መሆኑ ታውቋል። ር. ሊ. ጳ ቅድሱ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ወደ ስሎቬኒያ ባደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ወቅት በወቅቱ በችግር ውስጥ የምትገኝ ስሎቬኒያን “ለኢየሱስ ክርስቶስ እናት፣ ቅድስት ማርያም አደራ እሰጣለሁ” ማለታቸው ይታወሳል።

ነፃነት፣ በብሔራዊ ታሪክ ውስጥ አዲስ ምዕራፍ ነው

“ዘለዓለማዊው ቤታችን በሰማያት ነው” ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን፣ ብቸኛ እና ከሁሉ በላይ ባይሆኑም ምድራዊ ሕይወታችንን ለመገንባት የሚያግዙ እውነተኛ እሴቶች መኖራቸውን ገልጸው፣ ይህም በፍትህ፣ በእርስ በእርስ፣ በወንድማማችነት እና በጠንካራ ፍቅር የተገነባ ነጻ እና ዴሞክራሲያዊ አገር መሆኑን አስረድተዋል። አክለውም “አስተማማኝ ማኅበራዊ ሰላም እና ጸጥታን ያረጋገጠ አገር በዓለም ዓለም አቀፍ ደረጃም ቢሆን ሰላሙ የተረጋገጠ ነው” ብለዋል። በመሆኑም ሰላም እና ፍትህ ለስሎቬኒያ ነጻነት ዋና መሠረት እንደሆኑ ገልጸው፣ ስሎቬኒያ ነጻነትን አግኝታ እንደገና መወለዷ አዲስ ምዕራፍ እንደሆነ፣ የቀድሞ ር. ሊ. ጳ ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ፣ ስሎቤኒያ ነጻነቷን ካገኘች ከጥቂት ዓመታት በኋላ ባደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ጊዜ መናገራቸውን ብጹዕነታቸው አስታውሰዋል። ር. ሊ. ጳ ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ስሎቬኒያ ነጻነቷል ካገኘች በኋላ በላኩት መልዕክት፣ የሕዝቦች የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት ሲረጋገጥ፣ ጠንካራ በሆኑ በጎነት እና የክርስትና እምነት፣ የወደፊት ዕድላቸውን አብረው ለመወሰን የሚያስችላቸውን ጥንካሬ ማግኘት እንደሚችሉ መናገራቸው ይታወሳል።

የእግዚአብሔር ቃል በተግባር ላይ ከዋለ ጠንካራ ዓለታችን ነው!

ስሎቬኒያ እ. አ. አ 2004 ዓ. ም. የአውሮፓ ኅብረት አባል አገር ለመሆን መብቃቷን ያስታወሱት ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን፣ ይህም ለአገሪቱ ትልቅ ድል እና እድገት እንደሆነ ገልጸው፣ በስሎቬኒያ፣ ብሌድ ከተማ የተሰበሰበው የአውሮፓ ኅብረት ምክር ቤት፣ የአህጉሪቱን የወደ ፊት ዕጣ ፈንታን ያማረ ለማድረግ ባደረጉት የጋራ ውይይት፣ የኅብረቱ የቀድሞ ክርስቲያን መሥራቾች እንደተመኙት ሁሉ፣ ከሁሉ አስቀድመው ፍትህ ያለበት የእግዚአብሔርን መንግሥት መገንባት አስፈላጊ እንደሆነ፣ ይህም የሰው ልጅ ዛሬም ቢሆን የሚፈልገው በዓለት ላይ እንደተገነባ ቤት ጠንካራ መሠረት ያላት የተባበረች አውሮፓን እና ዋስትና የሚሰጥ እሴት እንደገና ማግኘት እንደሆነ ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን አስረድተዋል። አክለውም፣ ቤተክርስቲያን ይህ እንዲሳካ በዘመናት ሁሉ ሀሳብ ማቅረብን ያላቆመች መሆኗን ገልጸው፣ የኢየሱስ ክርስቶስ መልእክትም “መላው ኅብረተሰብ ተረጋግቶ፣ በተለያዩ አስፈላጊ በሆኑ ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች መካከል የእግዚአብሔርን ቃል በማድመጥ ተግባራዊ ማድረግ አለበት” የሚል መሆኑን አስታውሰዋል።

የቀድሞ ር. ሊ. ጳ ቅዱስ ዮሐንስ 23ኛ “ሰላም በምድራችን” በሚለው ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳናቸው፣ መኖሪያ ቤታችንን በጠንካራ መሠረቶች ላይ መገንባት እንደሚያስፈልግ እነርሱም፥ እውነት፣ ፍትህ፣ ነጻነት እና ፍቅር ናቸው ማለታቸውን አስታውሰው፣ ኢየሱስ ክርስቶስ በወንጌሉ እንደተናገረን፣ አንድነትን በማሳደግ፣ እያንዳንዱ ሰው ጥሪውን እና ሃላፊነቱን በሚገባ ተገዝቦ አገርን ለማሳደግ ጥረት እንዲያደርግ ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን አሳስበዋል። 

እውነት ፣ ፍትህና ነፃነት የፍቅር ፍሬዎች ናቸው

ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን በስብከታቸው፣ እውነትን ከተደበቀበት ገሃድ ማውጣት፣ የሰው ልጅ ክብርን ከሚጎዳ ከማንኛውም ዓይነት ጭቆና ነፃነት ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸው፣ ነጻነት የሚያገለግለው መልካምን ለማድረግ እንጂ የግል ፍላጎትን ለማስፈጸም እንዳልሆነ አስረድተው፣ በተለይም የሐይማኖት ነጻነት እያንዳንዱን ሰብዓዊ ክብር ለማረጋገጥ እጅግ አስፈላጊ እና መሠረታዊ መሆኑን አስረድተዋል። ነጻነት የፍቅር የመጀመሪያ ውጤት እንደሆነ ብጹዕነታቸው ገልጸው፣ ፍትህም የጋራ መኖሪያ ቤትን ለመገንባት የሚያግዝ መሠረታዊ የፍቅር ውጤት መሆኑን ገልጸው፣ የእያንዳንዱን ሰው መብት የሚያረጋግጥ ፍትህ ቢሆንም “በነጻ የሚሰጥ ፍቅር” ከሁሉ በላይ መሆኑን አስረድተዋል። ሕጎች የሰው ልጅ መብቶችን እና ግዴታዎችን የሚቆጣጠሩ ከሆነ ፣ “በኢየሱስ ክርስቶስ የተገለጸው ፍቅር እኛም ያለ ትርፍ በነጻ ለመስጠት እራሳችንን ማቅረብ ያስፈልጋል” ብለዋል። የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን በመጨረሻም፣ የእውነት ፣ የነፃነት እና የፍትህ ፍሬ የሆነውን ፍቅር፣ እግዚአብሔር ለሁሉም ስሎቬኒያ፣ አውሮፓ እና ዓለም እንዲሰጥ በጸሎት እንጠይቀዋለን በማለት ስብከታቸውን አጠቃልለዋል።          

02 September 2021, 16:17