ፈልግ

የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ፍንዳታ የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ፍንዳታ 

ቅድስት መንበር፣ ዓለም ከኒውክሌር የጦር መሣሪያ ነጻ እንድትሆን አሳሰበች

ቅድስት መንበር፣ “ዓለም ከኒውክሌር የጦር መሣሪያ ነጻ ሊሆን ይገባል” የሚለውን የቤተክርስቲያን አቋም በማደስ፣ በ65ኛ ዓለም አቀፍ አቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ጉባኤ መክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ላይ አሳስባለች።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ቅድስት መንበር፣ ዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ (IAEA) የኒውክሌር ጦር መሣሪያዎችን መስፋፋት ለመግታትና፣ የሰውን ልጅ ሰላማዊ የኑክሌር ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ለማድረግ ላደረገው ጥረት ምስጋናዋን አቅርባለች። 

የኒውክሌር የጦር መሣሪያ ባለቤትነት “ሥነ ምግባር የጎደለው” ነው

በቫቲካን የመንግሥታ ሁለገብ ግንኙነት ጉዳዮች ክፍል ምክትል ጸሐፊ፣ ወ/ሮ ፍራንችስካ ዲ ጆቫኒ፣ ሰኞ መስከረም 10/2014 ዓ. ም በተካሄደው 65ኛ ዓለም አቀፍ አቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ጉባኤን በተካፈሉበት ዕለት ባሰሙት ንግግር፣ ዓለም አቀፍ አቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ፣ ኒውክሌር መሣሪያዎች ከሰላም ዓላማ ውጭ ለጦርነት መሣርያነት አለ መዋላቸውን በማረጋገጥ ለሚጫወተው ልዩ ሚና ቅድስት መንበር እውቅናን መስጠቷን ገልጸዋል። ኤጀንሲው ይህን በማድረጉ፣ ከኒውክሌር የጦር መሣሪያዎች ነጻ የሆነ ዓለምን ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያበረክት መሆኑን ገልጸው፣ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በተደጋጋሚ ባስተላለፉት መልዕክቶች የኒውክሌር የጦር መሣሪያ ባለቤትነት “ሥነ-ምግባር የጎደለው ነው” ማለታቸውን እና “ዓለማችን ከኒውክሌር የጦር መሣሪያ ነጻ ሊሆን ይገባል” በማለት ማሳሰባቸውን ገልጸዋል።

በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት አስፈላጊ አገልግሎቶችን አቅርቧል

ወ/ሮ ፍራንችስካ ዲ ጆቫኒ፣ ዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት አንዳንድ አገልግሎቶችን ለማቋረጥ የተገደደ ቢሆንም አስፈላጊ የሆኑ አገልግሎቶቹን ለመስጠት ባደረገው ጥረት የተሳካ ውጤት ማስመዝገቡን አድንቀዋል። በተለይም አዲሱን፣ በእንስሳት እና በሰዎች መካከል የሚሰራጩ ጀርሞችን ለመቆጣጠር የሚያግዝ የተቀናጀ የድርጊት መርሃ-ግብርን ጠቅሰዋል። 

የጥረት መርሃ ግብሩ እ. አ. አ በሰኔ ወር 2020 መጀመሩን ያስታወሱት ወ/ሮ ፍራንችስካ ዲ ጆቫኒ፣ ዓላማውም ከእንስሳት ወጥተው ወደ ሰዎች ሊተላለፉ የሚችሉ ባክቴሪያዎችን ፣ ጥገኛ ተሕዋስያንን፣ ፈንገሶች፣ እና ወረርሽኝን ሊያስከትሉ የሚችሉ ቫይረሶች ለመከላከል ጥረት የሚያደርጉ አገራትን ለመርዳት መሆኑን ገልጸዋል። ወ/ሮ ፍራንችስካ ዲ ጆቫኒ አክለውም፣ ዓለም አቀፍ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲው በተጨማሪም የምርምር እና የልማት እንቅስቃሴዎቻቸውን በመርዳት፣ ባለሙያዊ መመሪያዎችን እንዲሁም የቴክኒክ ፣ የሳይንስ እና የላቦራቶሪ ድጋፍን የሚሰጥ መሆኑን አስረድተዋል።

በማደግ ላይ ያሉ አገራትን ይረዳል

የቫቲካን ተወካዩዋ፣ ዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ በማደግ ላይ ያሉ አገሮች ካንሰርን ለማከም ፣ የእህል ምርት መጠንን ለማሳደግ እና የውሃ አቅርቦትን ለማስተዳደር እና ለመጠበቅ የሚያግዝ የኒውክሌር ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ በማድረግ “ልዩ ተግባራትን” የሚያከናውን መሆኑንም አስረድተዋል። ኤጀንሲው በተጨማሪም በአየር ንብረት ለውጥ መስክ ፣ የውቅያኖሱን እና የአካባቢ ብክለትን በመከታተል ፣ አገራት የምግብ እና የውሃ እጥረትን ጨምሮ ከአዳዲስ የአየር ንብረት እውነታዎች ጋር እንዲላመዱ በመርዳት ቀጣይነት ያለው “ተገቢ አስተዋፅኦ” የሚያበረክት መሆኑን አፅንዖት ሰጥተው ገልጸዋል።

ለጦር መሣሪያ ግዥ የሚውለውን ገንዘብ ረሃብን ለማስወገድ መጠቀም

የቅድስት መንበር ቀጣይ ጥረት ሥነ-ምህዳራዊ እና ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት መሆኑን ያስታወሱት ወ/ሮ ፍራንችስካ ዲ ጆቫኒ፣ በወንድማማችነት ላይ የተመሠረተ ዘላቂ ልማትን የሚደግፉ ቴክኒካዊ እርምጃዎችን ማስተዋወቅ የቅድስት መንበር ጥረት መሆኑን አስረድተዋል። በመጨረሻም የዓለም መሪዎች “ረሃብን ለማስወገድ እና ለድሃ አገራት ልማት አስተዋፅኦ በማድረግ፣ ለጦር መሣሪያ የሚያወጡትን ገንዘብ ወደ ዓለም አቀፍ ፈንድ ለማዛወር ደፋር ውሳኔን እንዲወስዱ በማለት ር. ሊ. ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ደጋግመው ያቀረቡትን ጥሪ ወ/ሮ ፍራንችስካ ዲ ጆቫኒ በድጋሚ አቅርበዋል። በኦስትሪያ መዲና ቪየና በመካሄድ ላይ የሚገኘው 65ኛው የዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ጠቅላላ ጉባኤ እስከ መስከረም 14/2014 ዓ. ም የሚቀጥል መሆኑ ታውቋል።

23 September 2021, 17:12