ፈልግ

በሕክምና እገዛ ሕይወትን የማጥፋ ዘዴ በሕክምና እገዛ ሕይወትን የማጥፋ ዘዴ 

አቡነ ፓሊያ፣ ሕይወትን የሚጻረር አዲስ የምርምር ዘርፍ በማደግ ላይ መሆኑን አስታወቁ

በቫቲካን የስነ-ሕይወት ጥናት ጳጳሳዊ አካዳሚ ፕሬዚደንት ብጹዕ አቡነ ቪንቼንሶ ፓሊያ፣ ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ ጣሊያንን ጨምሮ በተለያዩ አገራት መሠረታዊውን የሕይወት ፅንሰ-ሀሳብ የሚጻረር የምርምር ዘርፍ ቀስ በቀስ በማደግ ላይ መሆኑን አስታውቀዋል። የምርምር ዘርፉ ከሰው ልጅ ደኅንነት እና የጤና ፅንሰ-ሀሳብ ጋር የማይዛመድ መሆኑንም አስረድተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ እ. አ. አ ነሐሴ 15/2016 ዓ. ም. በዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ጳጳሳዊ ተቋም ውስጥ የጋብቻ እና ቤተሰብ መምሪያን በፕሬዚደንትነት እንዲመሩ በማለት ብጹዕ አቡነ ቪንቼንሶ ፓሊያን በቫቲካን የስነ-ሕይወት ጥናት ጳጳሳዊ አካዳሚ ፕሬዚደንት አድርገው መሰየማቸው ይታወሳል። እንደሚታወቀው ከጥቂት ዓመታት ወዲህ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በዓለማችን ውስጥ ስጋትን በማንገስ እጅግ በርካታ የሰው ሕይወትን ለሞት መዳረጉ እና ሌሎች ማኅበራዊ እና ኤኮኖሚያዊ ችግሮችን ማስከተሉ ይታወቃል። ይህ በሆነበት ባሁኑ ወቅት ዓለማችን ከአዳዲስ ተግዳሮቶች ጋር የተቆራኘ መሆኑን በቫቲካን የስነ-ሕይወት ጥናት ጳጳሳዊ አካዳሚ ፕሬዚደንት የሆኑት ብጹዕ አቡነ ቪንቼንሶ ፓሊያ፣ ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቆይታ ገልጸዋል። ብጹዕነታቸው “በሰው ልጅ ሕይወት የጤና ጽንሰ-ሀሳብ” ላይ እየተከሰተ ያለው አሉታዊ ለውጥ ያሳሰባቸው መሆኑን ገልጸው፣ የ“ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ጳጳሳዊ የጋብቻ እና የቤተሰብ ሕይወት ሳይንስ ሥነ-መለኮታዊ ተቋም እስካሁን የወሰዳቸውን እርምጃዎች አስመልክተው ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የጋብቻ እና የቤተሰብ ሕይወት ሳይንስ ሥነ-መለኮታዊ ተቋም በሥርዓተ ትምህርት ዘርፍ ጥልቅ ተሃድሶ ሊደረግለት ያስፈልግ ነበር ያሉት ብጹዕ አቡነ ቪንቼንሶ ፓሊያ፣ ለተቋሙ የተሰጠው አዲስ ስም የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊን ዓላማን እና ምኞት መሠረት በማድረግ፣ ሥነ-መለኮት እና ሳይንስ የሚሉ ሁለት ቃላትን ያካተተ መሆኑን አስረድተዋል። በመሆኑም ለተቋሙ የተሰጠው አዲሱ ስም የጋብቻ እና የቤተሰብ ሳይንስ ሥነ -መለኮታዊ ተቋም የሚል መሆኑን ገልጸዋል። በዚህ መሠረት የተቋሙ አዲስ የጥናት ዕቅድ የቤተሰብ እና የጋብቻ ጉዳዮችን ከሰው ልጅ ማኅበራዊ እና ባሕላዊ የዕድገት ደረጃ፣ ከሕግ እና ኢኮኖሚያዊ ጭብጥ ጋር በማዛመድ ከሥነ-መለኮት እስከ ሥነ-ምግባር ያሉ ሐዋርያዊ አገልግሎቶችን ከሰብዓዊ ሳይንስ ጋር የሚዛመዱ ጉዳዮችን የሚመለከት ዕቅድ ያለው መሆኑን አስረድተዋል። የስነ-ሕይወት እና የማኅበረሰብ ጥናት የቤተክርስቲያኗ የማዕዘን ድንጋይ በመሆናቸው፣ አጠቃላይ ወጎችን ከዘመናዊው ዓለም ወቅታዊ ሁኔታዎች ጋር በማገናኘት ጥንቃቄ የተሞላባቸው አዳዲስ የጥናት ዘርፎች መታከላቸውን ብጹዕ አቡነ ቪንቼንሶ ፓሊያ አብራርተዋል።

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ባለበት ባሁኑ ወቅት ተቋሙ አስተንትኖ ማድረጉን ያስታወሱት ብጹዕ አቡነ ቪንቼንሶ ፓሊያ፣ ከሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ ሰነዶች መካከል የቀድሞ ር. ሊ. ጳ ቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ ይፋ ያደረጉትን “Gaudium et spes” ወይም “ደስታ እና ተስፋ” የሚለውን ሐዋርያዊ ሰነድ መሠረት ያደረጉ እና ከፍተኛ ፍላጎት የታዩባቸው ሴሚናሮች እና ትምህርታዊ ጥናቶች መካሄዳቸውን ገልጸዋል። በሴሚናሩ ወቅት ከወሊድ ምጣኔ ጉዳዮች ጋር የተዛመዱ ችግሮችን አስመልክተው ከቻይና የተጋበዙት የማኅበረሰብ ሳይንስ ተመራማሪ ገለጻ ማድረጋቸውን ገልጸዋል። ከዚህም በተጨማሪ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በቤተሰብ ሕይወት ላይ ያስከተለውን ቀውስ በተመለከተ ውይይት የተደረገ ሲሆን፣ በማኅበራዊ ድረ-ገጽ አማካይነት በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች በወረርሽኙ ወቅት ቁምስናዎችን እና የቤተሰብ ተቋማትን ማገዝ በሚችሉባቸው መንገዶች ሰፊ ውይይት መደረጉን ብጹዕ አቡነ ቪንቼንሶ ፓሊያ ገልጸዋል። 

በቅድስት መንበር የሥነ-ሕይወት ጥናት ጳጳሳዊ አካዳሚም በበኩሉ፣ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ይፋ ካደረጉት “የፍቅር ደስታ” ከሚለው ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን ተጨማሪ ብርታትን እና ጥንካሬን ማግኘቱን ገልጸው፣ በዚህ አጋጣሚ “ሕይወት” የሚለው ቃል ልዩ ትኩረት የተሰጠው መሆኑን አስረድተዋል። ከጊዜ ወደ ጊዜ በማደግ ላይ ያለውን የአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ግኝት ያስታወሱት አቡነ ቪንቼንሶ ፓሊያ፣ ይህን በተመለከተ “አርቲፊሻል ኢንቴሊጀንስ ፋውንዴሽን” በመባል የሚታወቅ ማዕከል መቋቋሙን ገልጸው ዓላማውም ሕይወትን ለሚመለከቱ ርዕሠ ጉዳዮች አስቸኳይ ትኩረት እንዲሰጣቸው የሚያሳሰብ መሆኑን አስረድተዋል። 

ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ የጊዜያችንን ድንገተኛ አደጋዎች በጋራ ለመቋቋም የሚያግዝ ከሃይማኖታዊ ተቋማት እና ከሳይንሱ ማኅበረሰብ የተውጣጣ የምሁራን ቡድን መቋቋሙን አቡነ ቪንቼንሶ ፓሊያ አስታውቀው፣ የምንገኝበት ዘመን፣ ቴክኖሎጂ የወደፊቱ አዲስ ሃይማኖት የመሆን አደጋ ያለበት መሆኑን አስረድተዋል። አክለውም የሥነ-ሕይወት ጳጳሳዊ አካዳሚው ሥነ-መለኮትን እና ሳይንስን በማጣመር፣ በመካከላቸው አዲስ ውይይት እና አዲስ ኅብረት መፍጠር እንዳለባቸው አሳስበዋል።  

ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ ጣሊያንን ጨምሮ በተለያዩ አገራት መሠረታዊውን የሕይወት ፅንሰ-ሀሳብ የሚጻረር የምርምር ዘርፍ ቀስ በቀስ በማደግ ላይ መሆኑ እንዳሳሰባቸው የገለጹት ብጹዕ አቡነ ቪንቼንሶ ፓሊያ፣ የምርምር ዘርፉ “በእናት ማሕጸን ውስጥ ሙሉ ጤናማ ያልሆነ ጽንስ መወለድ የለበትም” የሚል መሆኑን ገልጸዋል። ከዚህ አንፃር፣ የሰው ልጅ ደካማነት የመላው ፍጥረት አካል መሆኑን ቤተክርስቲያን ተገንዝባ አስፈላጊውን ማሳሰቢያ ልትሰጥ ይገባል ብለዋል። የሰው ልጅ ደካማነት አንዱ የሌላውን ሃላፊነት በመውሰድ አስቸኳይ ማኅበራዊ ወንድማማችነት እንዲገነባ የሚያሳስብ መሆኑን አስረድተዋል። 

በቫቲካን የሥነ-ሕይወት ጥናት ጳጳሳዊ አካዳሚ ካለፉት ቅርብ ወራት ወዲህ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ባስከተለው ቀውስ ምክንያት ክፉኛ ለተጎዱ እና ለተዘነጉ አቅመ ደካሞች፣ የአካል ጉዳተኞች እና ሕጻናት ድጋፍ ለማድረግ ጥረት እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል። ጳጳሳዊ አካዳሚው በተጨማሪም ለአቅመ ደካሞች የሚደረግ የቅድሚያ ድጋፍን በማጠናከር፣ ማንም ወደ ጎን ሳይባል ሰብዓዊነትን የተላበሰ ዓለምን ለመገንባት ጥረት እያደረገ መሆኑን፣ በቫቲካን የስነ-ሕይወት ጥናት ጳጳሳዊ አካዳሚ ፕሬዚደንት ብጹዕ አቡነ ቪንቼንሶ ፓሊያ ከቫቲካን ዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቆይታ ገልጸዋል። 

17 August 2021, 16:30