ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የደቡብ ኮርያ ሰማዕታትን እ. አ. አ ነሐሴ 16/2014 ዓ. ም ባስታወሱበት ወቅት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የደቡብ ኮርያ ሰማዕታትን እ. አ. አ ነሐሴ 16/2014 ዓ. ም ባስታወሱበት ወቅት  

የደቡብ ኮርያ ሰማዕታት የሕዝባቸውን ማንነት የሚገልጹ፣ የእምነት ምስክሮች መሆናቸው ተገለጸ

በደቡብ ኮርያ እ. አ. አ 1846 ዓ. ም በሰማዕትነት የተገደሉት የአገሪቱ የመጀመሪያው ካህን አባ እንድርያስ ኪም ቴጎን የልደታቸው ሁለት መቶኛ ዓመት መታሰቢያ በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ በተፈጸመው የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ሥነ-ሥርዓት መከበሩ ታውቋል። መስዋዕተ ቅዳሴውን የመሩት በቅድስት መንበር የቤተክህነት ጉባኤ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ፣ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ላዛሮ ዩ ናቸው። የመስዋዕተ ቅዳሴውን ጸሎት ካህናት፣ ደናግል፣ ምዕመናን እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተካፍለዋል። የአባ እንድርያስ ኪም ቴጎ ቅድስናን የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳስ ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ እ. አ. አ በ1984 ዓ. ም አጽድቀው በይፋ ማወጃቸው ይታወሳል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

አባ እንድርያስ ቴጎን ጠንካራ የእምነት ጽናት ካለው ቤተሰብ እ. አ. አ ነሐሴ 21/1821 ዓ. ም የተወለዱ ሲሆን አባታቸው የገዛ መኖሪያ ቤታቸውን ወደ ጸሎት ቤትነት በመቀየር ከሌሎች ምዕምናን ጋር በመሆን ጸሎታቸውን ያቀርቡ ነበር። ባሳለፏቸው የአራት ትውልድ ዘመን ከቤተሰባቸው መካከል አሥራ አንድ አባላት ለእምነታቸው ሲሉ ደማቸውን ያፈሰሱ፣ ከእነዚህም መካከል አምስቱ ለቅድስና እና ለብጽዕና ደረጃ በቅተዋል። በወቅቱ የአሥራ አንድ ዓመት ዕድሜ አዳጊ ወጣት የነበረው እንድርያስ እምነቱን እንዲክድ ተጠይቆ ባለመቀበሉ ብዙ ስቃይ ከደረሰበት በኋላ አንገቱን ተቀልሶ እንዲገደል ተደርጓል። ለእምነታቸው ያላቸውን ታማኝነት በመግለጽ ተመሳሳይ ስቃይ የደረሰባቸው በመቶ የሚቆጠሩ ሌሎች ምዕመናን በደቡብ ኮርያ ውስጥ መኖራቸው ሲታወቅ፣ የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ እ. አ. አ በ1984 ዓ. ም የአባ እንድርያስን ስም በቅዱሳን መዝገብ ውስጥ እንዲቀምጥ አድርገዋል።

ካርዲናል ፓሮሊን እ. አ. አ በ2018 ዓ. ም. ለኮርያ ሰላም ጸሎት አቅርበዋል

ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ላዛሮ ዩ ነሐሴ 15/2013 ዓ. ም በቫቲካን በሚገኘው ቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ በመሩት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ላይ በቁጥር ሰላሳ የሚደርሱ ካኅናት፣ ወደ ሰባ የሚደርሱ ገዳማዊያን እና ገዳማዊያት የተካፈሉ ሲሆን በቅድስት መንበር የደቡብ ኮርያው አምባሳደርም መገኘታቸው ታውቋል። ከዚህም በተጨማሪ ኑሮአቸውን በሮም ከተማ ያደረጉ የደቡብ ኮርያ ምዕመናንም የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎትን ተካፍለዋል። እ. አ. አ 2018 ዓ. ም ለኮርያ ሰላም ተብሎ በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ በቀረበው የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ላይ የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን ተገኝተው እንደነበር ይታወሳል።

የኮርያ ሰማዕታት ታሪክ

በኮርያ ውስጥ በነበሩ የቀድሞ ካቶሊካዊ ካህናት፣ ደናግል እና ምዕመናን ላይ ከፍተኛ ስቃይ ይደርስባቸው እንደነበር የአገሪቱ የክርስትና ታሪክ ይገልጻል። በኮርያ ውስጥ የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያን ማኅበረሰብ ለመጀመሪያ ጊዜ የታዩት እ. አ. አ በ1600 ዓ. ም እንደነበር ይታወሳል። የባሕል ልውውጥ ለማድረግ ወደ ቻይና የተጓዙት ኮርያዊያን ወደ አገራቸው ሲመለሱም የክርስትናን እምነት ተቀብለው አገራቸው እንደሚመለሱ ኢየሱሳዊ ካኅን ክቡር አባ ማቴዎ ሪቺ በመጽሐፋቸው ገልጸዋል። ይህን መጽሐፍ በማንበብ ልዩ ክርስቲያናዊ ጥሪ የተሰማው ሊ ቢዮክ የተባለ ምዕመን በአገሩ ውስጥ የመጀመሪያውን የክርስቲያን ማኅበረሰብ እንደመሠረተ ይነገራል። በግል በመረጣቸው የቤተክርስቲያን ሽማግሌዎች እና አገልጋዮች ብርታት ምስጢራትን በማዘጋጀት የጋራ ጸሎቶችን ማካሄድ ጀመሩ። ቀጥሎም መሪ ካኅን እንዲላክላቸው በማለት በቻይና ለሚገኙ ጳጳስ ጥያቄ አቅርበው አባ ቹ ሙን ሞ የተባሉ ካኅን ተልኮላቸዋል። በዚህ መሠረት በኮርያ የሚገኝ የክርስቲያን ማኅበረሰብ በአጭር ጊዜ ውስጥ በቁጥር አድጎ ተገኘ።

ጭካኔ የተሞላበት ስቃይ እና ስደት ደረሰባቸው

እ. አ. አ በ1785 ዓ. ም ገደማ በኮርያ ውስጥ በሚገኙ ክርስቲያኖች ላይ ከፍተኛ ስቃይ ይደርስባቸው ጀመር። በዚህ ምክንያት ክርስቲያኖችን ያገለግሉ የነበሩ ካኅን እ. አ. አ በ1801 ዓ. ም ተገደሉ። ይሁን እንጂ የክርስቲያን ማኅበርሰብ ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ ማደጉን አላቋረጠም። ንጉሥ ሱንጆ መንግሥታቸውን የሚያስጨንቀው የክርስቲያኖች ተጽዕኖ ነው በማለት ከአገሪቱ ውስጥ ክርስቲያኖች እንዲጠፉ አወጁ። በዚህ ምክንያት ክርስቲያኖች ላይ ከፍተኛ ስቃይ ይደርስ ጀመር። ክርስቲያኖቹ መሪ ካኅን ስለተገደለባቸው ሐዋርያዊ መሪን በማጣት ብቻቸውን ቀሩ። ካህን እንዲመደብላቸው በማለት  ወደ ር. ሊ. ጳጳሳት እና በቻይና ለሚገኙት ጳጳሳት ጥያቄአቸውን ማቅረብ አላቋረጡም ነበር። ከፈረንሳይ አገር እ. አ. አ በ1837 ዓ. ም አንድ ጳጳስ እና ሁለት ካኅናት ተደብቀው ወደ ኮርያ የገቡ ቢሆንም በተቃዋሚዎቻቸው በተሰነዘረው ጥቃት ተገደሉ። እንድርያስ ኪም የተባለ ካህን ባደረገው ሁለተኛው ጥረት አንድ ጳጳስ እና አንድ ካኅን ሐዋርያዊ አገልግሎታቸውን ለማበርከት ወደ ኮርያ መጡ። በክርስቲያኖች ላይ የሚፈጸም በደል ባይወገድም እ. አ. አ ከ1866 ጀምሮ ሐዋርያዊ አስተዳደር እንደ ምንም ሊዋቀር ቻለ። በመጨረሻም እ. አ. አ 1882 ዓ. ም በኮርያ ውስጥ የሐይማኖት ነጻነት ታወጀ።

የቀድሞ ር. ሊ. ጳ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ 103 የኮሪያ ሰማዕታትን ይፋ አደረጉ

በኮርያ ውስጥ በክርስቲያኖች ላይ ይደርስ በነበረው ስቃይ ከአሥር ሺህ በላይ ምዕመናን በሰማዕትነት መገደላቸውን ከአገሩ የሚወጡ መረጃዎች አረጋግጠዋል። ከእነዚህም መካከል እ. አ. አ ከ1925 ዓ. ም 103 ሴት እና ወንድ ኮርያዊ ምዕመናን በካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ለሰማዕትነት መብቃታቸው ይፋ የተደረገ ሲሆን እ. አ. አ በ1968 ዓ. ም በተፈጸመው የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ወቅት የቀድሞ ር. ሊ. ጳ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ቅድስናቸውን ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል። ከእነዚህ መካከል አሥር የውጭ አገር ዜጎች፣ ሦስት ጳጳሳት እና ሰባቱ ካህናት መሆናቸው ይታወሳል።

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በኮርያ ውስጥ ሌሎች 124 ሰማዕታትን ይፋ አደረጉ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ እ. አ. አ ነሐሴ 16/2014 ዓ. ም ወደ ደቡብ ኮርያ ባደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ወቅት ሌሎች 124 ሰማዕታትን ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል። ቅዱስነታቸው በሴኡል ከተማ አቅራቢያ በሚገኝ የሰማዕታቱ መታሰቢያ ቤተመቅደስ ውስጥ ተገኝተው የመሩትን የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሰዎች ማካፈላቸው ይታወሳል። በመስዋዕተ ቅዳሴው ጸሎት ሥነ-ሥርዓት ላይ ባሰሙት ስብከት፣ ክርስቶስን ማስቀደም እንደሚገባ እና በእምነት ላይ ፈጽሞ መደራደር እንደማያስፈልግ ማሳሰባቸው ይታወሳል። አክለውም የሰማዕታቱ የሕይወት ገድል አዲስ ፍሬን እንደሚያፈራ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን ምስክርነት እንድንሰጥ፣ ዘወትር እርሱን እንድንወድ እና እንድናገለግለው፣ የእኛ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን ወንድሞች እና እህቶች እንድንደግፍ ሳያቋርጥ የሚጠይቀን መሆኑን ገልጸዋል።

የኮርያ ቤተክርስቲያን እና የኢዮቤልዩ በዓል        

በደቡብ ኮርያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የመጀመሪያ ካህን የሆኑት የአባ እንድርያስ ኪም ቴጎን ልደት ሁለት መቶኛ ኢዮቤልዩ  መታሰቢያ በዓልን እ. አ. ከኅዳር 29/2020 ዓ. ም. ጀምሮ በተለያዩ ዝግጅት ሲከበር ቆይቷል። አንድ ዓመት የቆየው የጸጋ ጊዜ፣ በተባበሩት መንግስታት የትምሕርት፣ የሳይንስ እና የባሕል ተቋም "ዩኔስኮ" ተሳታፊ በሚሆንበት ታላቅ መንፈሳዊ በዓል እ. አ. አ ኅዳር 27/2021 ዓ. ም የሚደመደም መሆኑን በቅድስት መንበር የቤተክህነት ጉባኤ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ላዛሮ ዩ ገልጸዋል። በዓሉ እያንዳንዳችን የሰማዕታቱን መንፈሳዊነት በልባችን ውስጥ ለመያዝ መልካም ዕድል የሚሰጥ መሆኑን እና የኮርያ ቤተክርስቲያን የሰማዕታቶቿን ሕይወት በማስታወስ የእምነት እሴቶቿን በሚገባ ለመረዳት እጅግ ጠቃሚ መሆኑን አስረድተዋስል።

ከኮርያ ሕዝብ መካከል 11 ከመቶ የሚሆነው የካቶሊክ እምነት ተከታይ ሲሆን ከሕዝቦቿ መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆነው ሐይማኖት የሌለው መሆኑን ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ላዛሮ ገልጸው፣ ይህ እውነታ የኮርያ ካቶሊካዊ ምዕመናን በእምነታቸው ጠንክረው የሕዝባቸውን ማንነት በእምነት ምስክርነት እንዲገልጹ የሚያሳስብ መሆኑንም አስረድተዋል።     

21 August 2021, 15:31