ፈልግ

ቅዱስነታቸው በሮም ከተማ ውስጥ ከሚገኙ ችግረኞች መካከል ከአንዷ ጋር ሰላምታ ሲለዋወጡ  ቅዱስነታቸው በሮም ከተማ ውስጥ ከሚገኙ ችግረኞች መካከል ከአንዷ ጋር ሰላምታ ሲለዋወጡ  

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በሮም የሚገኙ 2500 ችግረኞችን ከድህነት ማውጣታቸው ተነገረ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ኮቪድ-19 ወረርሽኝ ባስከተለው ቀውስ ችግር ውስጥ የወደቁ 2500 የሮም ከተማ ነዋሪዎችን በመደገፍ ከድህነት እና ከብቸኝነት ሕይወት እንዲወጡ ማድረጋቸውን “ኢየሱስ መለኮታዊ ሠራተኛ” በመባል የሚታወቅ የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የዕርዳታ መስጫ ድርጅት በሮም ሀገረ ስብከት ከሚገኝ ዋና ጽሕፈት ቤቱ አስታውቋል። “ሮምን ለማገዝ እንተባበር” በሚል ዕቅድ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን እና ልዩ ልዩ ተቋማት መሳተፋቸው ታውቋል። የሮም ሀገረ ስብከት ምክትል ሥራ አስኪያጅ ብጹዕ አቡነ ጃንፔሮ ፓልሚዬሪ በከተማው ሕገወጥ ሥራዎችን ማስፋፋት እንደማያስፈልግ፣ የሮም ከተማ ከንቲባ ወ/ሮ ቬርጂኒያ ራጂ በከተማው የሚታዩ ወንጀሎችን መከላከል እንደሚያስፈልግ፣ የላሲዮ ክልል ፕሬዚደንት አቶ ኒኮላ ዚንጋሬቲ የሮም ከተማ ችግሮች እያሉበት የኢዮቤልዩ በዓልን ማስተናገድ አይችልም ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የድጋፍ መስጫ ማኅበርን የመሠረቱት በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ከሥራ ገበታቸው ተወግደው በከፍተኛ ችግር ውስጥ ለወደቁ የሮም ከተማ ነዋሪዎች ድጎማዎችን ፣ የገቢ ድጋፍን እና ወደ ሥራው ዓለም ተመልሰው እንዲገቡ ለማድረግ መሆኑን የዕርዳታ ድርጅቱ አስታውቋል። የቤተክርስቲያኒቱ ዕርዳታ አቅርቦት ዓላማ፣ ችግር ላይ ከሚገኙ ቤተሰቦች እና ግለሰቦች ጎን ሆኖ ብሶታቸውን በርኅራሄ ልብ ከማዳመጥ በተጨማሪ በከተማዉ የሚገኙ ሌሎች ተቋማትን በማስተባበር በቁጥር በርካታ የሆኑ ቤተሰቦችን ካጋጠማቸው ችግር እና የብቸኝነት ሕይወት ለማውጣት የሚያስችል በቂ ኃይል ለማሰባሰብ መሆኑ ታውቋል።

የዕርዳታ ድርጅቱ ከተቋቋመ ከአንድ ዓመት በኋላ የተገኙ መልካም ውጤችን በሮም ሀገረ ስብከት በሚገኝ ዋና ጽ/ቤቱ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል። በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ የሮም ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ የሆኑት ብጹዕ አቡነ ጃንፔሮ ፓልሚዬሪ፣ የሮም ከተማ ከንቲባ ወ/ሮ ቬርጂኒያ ራጂ እና የላሲዮ ክልል ፕሬዚደንት አቶ ኒኮላ ዚንጋሬቲ መገኘታቸው ታውቋል። በጋዜጣዊ መግለጫው ሥፍራ የተገኙት የሀገረ ስብከቱ ዕርዳታ ማስተባበሪያ የቀደሞ ዳይሬክተር የነበሩ ብጹዕ አቡነ ቤኖኒ አምባሩስ የዕርዳታ ድርጅቱ ስኬቶችን፣ “ትንቢታዊ” እና “የምስክርነት” ምልክቶችን አብራርተዋል።  

ራስ ወዳድነትን በኅብረት ማሸነፍ ያስፈልጋል

“ሮምን ለማገዝ እንተባበር” በሚል ዕቅድ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በመሠረቱት የዕርዳታ መስጫ ድርጅት ውስጥ የላዚዮ ክልል እና የሮም ከታማ ማዘጋጃ መተባበሩ ታውቋል። የዕርዳታ ድርጅታቸውን አቅም ለማሳደግ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የመጀመሪያውን አንድ ሚሊዮን ዩሮ የለገሱ ሲሆን የላሲዮ ክልል እና የሮም ከተማ ማዘጋጃ በአንድነት አምስት መቶ ሺህ ዩሮ መለገሳቸው ሲነገር በከተማው የሚገኙ የግል ንግድ ድርጅቶች እና ግለሰቦች በጋራ ሁለት መቶ አንድ ሺህ ዩሮ መለገሳቸው ታውቋል። የዕርዳታ ድርጅቱ እነዚህን ዕርዳታዎች በማሰባሰብ በሮም ከተማ የሚገኙ በቁጥር ከ 2500 በላይ ለሚሆኑ ቤተሰቦች እና ግለሰቦች ዕርዳታን ማከፋፈሉ ታውቋል።

ለአራጣ እና ለወንጀል ተግባር ዕድል መስጠት አያስፈልግም

የሮም ከተማ ከንቲባ ወ/ሮ ቬርጂኒያ ራጂ፣ በከተማው እየተስፋፉ የመጡ ወንጀሎችን መከላከል እንዲቻል ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ባቋቋሙት የዕርዳታ ድርጅት ሥር መሰባሰቡ እንዳገዛቸው ገልጸው፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ባስከተለው ማኅበራዊ ቀውስ ችግር ውስጥ የወደቀውን የሮም ከተማ ሕዝብን መርዳት መቻሉን ገልጸዋል። የከታማውን የረጅም ዓመታት ታሪክ ያስታወሱት ወ/ሮ ቬርጂኒያ ራጂ፣ መተባበር እና የቸርነት ሥራ የከተማው የቆየ ባሕል መሆኑን አስታውሰው፣ ዛሬም ቢሆን ይህን ባሕል በመከተል በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ቀውስ ምክንያት የተጠቃውን የከተማው ነዋሪ ሕዝብን በመርዳት ላይ መሆናቸው አስረድተዋል። የቤት ኪራይን መክፈል ያልቻሉትን እና በአነስተኛ የንግድ ሥራ ላይ የተሰርማሩትን ለመደጎም የሮም ማዘጋጃ ሦስት ሚሊዮን ዩሮ በመመደብ የማይክሮ ክሬዲት የብድር አገልግሎትን ማመቻቸቱን አስረድተዋል። ይህም የከተማው ነዋሪዎች ለአራጣ እና ለወንጀል ተግባር እንዳይጋለጡ ይከላከላል ብለዋል።

ብቸኝነት ገዳይ ነው

በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ሰዎች ቤታቸውን ዘግተው፣ ከማኅበራዊ ግንኙነት ታቅበው መቆየታቸውን ያስታወሱት የላሲዮ ክልል ፕሬዚደንት አቶ ኒኮላ ዚንጋሬቲ፣ ወደየቤቱ በመሄድ ዕርዳታን የሚያዳርሱ ከ 400 በላይ በጎ ፈቃደኞች በሮም ከተማ ውስጥ መመደባቸውን አስታውሰዋል። በወረርሽኙ ምን ያህል እንደተያዙ፣ ምን ያህሉ የሕክምና ዕርዳታ እንዳገኙ፣ ምን ያህሉ በከፍተኛ የሕክምና እንክብካቤ ውስጥ እንደሚገኙ የሚታወቅ ቢሆንም፣ ቤት ተቆልፎባቸው እና ከማኅበረሰብ ተለይተው በስውር የሚሰቃዩ በርካቶች መሆናቸውን አስታውሰው፣ ወረርሽኙ በእርግጥ ሰውን እንደሚገድል ቢታወቅም ብቸኝነትም እንደዚሁ የሚገድ መሆኑን መዘነጋት የለብንም ብለዋል።

በእግር መቆም መቻል ያስፈልጋል

የሮም ሀገረ ስብከት ምክትል ሥራ አስኪያጅ የሆኑት ብጹዕ አቡነ ጃንፔሮ ፓልሚዬሪ፣ በከተማው የታየው ከፍተኛ ችግር ከሥራ ጋር የተያያዘ መሆኑን ሲያስታውሱ፥ እጅግ ብዙ ሰዎች በሥራ ገበታቸው የተበዘበዙ መሆናቸውን እና ለእንጀራቸው ሲሉ መጠነኛ ጥቅማ ጥቅሞችን ተቀብለው ያለ ክፍያ ሲሠሩ መቆየታቸውን አስታውሰዋል። በመሆኑም ብጹዕ አቡነ ጃንፔሮ ፓልሚዬሪ በከተማው ሕገወጥ ሥራዎችን ማስፋፋት እንደማያስፈልግ ገልጸው፣ እንደ ህብረተሰብ እና እንደ ቤተክርስቲያን ትንሽ የተስፋ ምልክቶችን ማሳካት እንችላለን ብለዋል። ዕርዳታ ከምጽዋት ጋር አንድ ተደርጎ መወሰድ የለበትም ብለው፣ ድሆች እንዲሰማቸው የማይፈልጉት የኅብረተሰቡ ሸክም መሆንን ነው ብለዋል።

የሴቶች ጥንካሬን ሊወደስ ይገባል

የሮም ሀገረ ስብከት ዕርዳታ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት የቀደሞ ዳይሬክተር የነበሩ ብጹዕ አቡነ ቤኖኒ አምባሩስ በጋዜጣዊ መግለጫ ማጠቃለያው ላይ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በጣም አስከፊ በሆነበት ጊዜ ቤተሰቦችን ለመርዳት ግንባር ቀደም ተዋናይ የነበሩ ሴቶችን ሁሉ ለጥንካሬአቸው አመስግነዋል። እናቶች ልጆቻቸውን ለመንከባከብ በየመንግሥት መሥሪያ ቤቶች መሰለፋቸውን፣ ይህን ሲያደርጉ የነበሩትም ቤተሰብን ከመበታተን ለመታደግ መሆኑን አስረድተው፣ ሴቶችን ለጥንካሬያቸው እናደንቃቸዋለን ብለው ምስጋናቸውንም አቅርበውላቸዋል።

04 August 2021, 14:12