ፈልግ

ብጹዕ ካርዲናል ጁሰፔ ቬርሳልዲ ብጹዕ ካርዲናል ጁሰፔ ቬርሳልዲ   (ANSA)

ካርዲናል ቬርሳልዲ መቻቻል እና ወንድማማችነት በሚያሳድጉ ስልጠናዎች ላይ ማትኮር እንደሚያስፈልግ አሳሰቡ

በጳጳስዊ ምክር ቤት ካቶሊካዊ ትምህርት ማስፋፊያ ጽሕፈት ቤት እና በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ትምህርት ሚኒስቴር መካከል የትብብር ስምምነት መፈረሙ ተገለጸ። ብጹዕ ካርዲናል ጁሰፔ ቬርሳልዲ ከአቡዳቢ ተመልሰው ከቫቲካን ዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቆይታ የ "ሰብዓዊ ወንድማማችነት” ሰነድ ፍሬን ማፍራት ቀጥሏል" ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ብጹዕነታቸው በቃለ ምልልሳቸው በዓለማችን ሕዝቦች በመካከል መቻቻልን እና ሰብዓዊ ወንድማማችነትን በማሳደግ አብሮ የመኖር ባሕልን ማሳደግ የሚያስፈልግ መሆኑን ገልጸዋል። አክለውም በካቶሊካዊ ትምህርት ማስፋፊያ ጽሕፈት ቤት እና በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ትምህርት ሚኒስቴር መካከል የተፈረመው የትብብር ስምምነት ይህን ዓላማ መሠረት ያደረገ መሆኑን አስረድተው፣ ስምምነቱ በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ውስጥ የሚገኙ የካቶሊክ ትምህርት ቤቶችን እና የቤተክርስቲያኒቱን ማሰልጠኛ ተቋማትን የሚያሳትፍ መሆኑን ገልጸዋል። 

በር. ሊ. ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እና በግብጹ የአል አዛር ታላቁ መስጊድ ኢማም በሆኑት በአህመድ አል ጣይብ መካከል በአቡ ዳቢ ከተማ ጥር 27 ቀን 2011 ዓ. ም. የተፈረመው የ“ሰብዓዊ ወንድማማችነት” ሰነድ በትምህርት እና ስልጠና ተቋማትም ፍሬ ማፍራት መጀመሩን የገለጹት በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የሕዝቦች መቻቻል እና የአንድነት ሚኒስትር ሼክ ናህያን ቢን ሙባረክ አል ናህያን፣ ለተነሳሽነታቸው ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስን ማመስገናቸውን ብጹዕ ካርዲናል ጁሰፔ ቬርሳልዲ አስታውሰዋል።

ወሳኝ እርምጃ ነው

“በጳጳስዊ ምክር ቤት ካቶሊካዊ ትምህርት ማስፋፊያ ጽሕፈት ቤት እና በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ትምህርት ሚኒስቴር መካከል የተፈረመ ስምምነት ቢሆንም፣ ስምምነቱ እጅግ ወሳኝ እና ጠቃሚ እርምጃ ነው” በማለት ከብጹዕ ካርዲናል ጁሰፔ ቬርሳልዲ ጋር ወደ ተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የተጓዙት በጳጳስዊ ፋውንዴሽን የትምህርት እና ማሰልጠኛ አገልግሎት ጠቅላይ ጸሐፊ የሆኑት ብጹዕ አቡነ ጋይ ሬል ቲቪዬዥ እና የፋውንዴሽኑ አምባሳደር ጣየዲን ሰይፍ በጋራ ሆነው ከቫቲካን ዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ገልጸዋል።   

የካቶሊክ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎቻችን እና የአረብ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች በጋራ የተለያዩ ሴሚናሮችን መከታተል እንደሚችሉ ፣ አዳዲስ ትብብሮችን መጀመር ፣ የጋራ ምርምሮችን በማካሄድ፣ ልዩነቶችን ሙሉ በሙሉ በማክበር በጋራ እሴቶች ላይ በመመስረት በሁለቱም በኩል የሚገኙ የትምህርት እና የስልጠና ተቋማትን መጎብኘት የሚችሉ መሆኑን በጳጳስዊ ምክር ቤት ካቶሊካዊ ትምህርት ማስፋፊያ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ ብጹዕ ካርዲናል ጁሰፔ ቬርሳልዲ ገልጸዋል። አክለውም ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ በኋላ የትምህርት ተቋማት መምህራንን በማስተባበር የትብብር ስምምነቱን ተግባራዊ ማድረግ የጽሕፈት ቤታቸው ሃላፊነት መሆኑን ብጹዕ ካርዲናል ጁሰፔ ቬርሳልዲ ገልጸው፣ በሚቀጥሉት ጊዜያትም ተከታታይ እና ተጨባጭ የባህል ልውውጥ የሚደረግ መሆኑን አስረድተዋል።   

08 July 2021, 16:27