ፈልግ

በስፔን ዋና ከተማ ማድሪድ የተካሄደው 15ኛ ዙር ዓለም አቀፍ ማህበራዊ ማስታወቂያ ፌስቲቫል በስፔን ዋና ከተማ ማድሪድ የተካሄደው 15ኛ ዙር ዓለም አቀፍ ማህበራዊ ማስታወቂያ ፌስቲቫል   (Copyright: Oficina de Medios de Comunicación de la Arquidiócesis de Madrid.)

በዓለም አቀፍ ሰብዓዊ ወንድማማችነት ቀን ላይ የተሠራ ፊልም ለሽልማት በቃ

ቫቲካን፣ ዓለም አቀፍ ሰብዓዊ ወንድማማችነት ቀንን አስመልክታ ያዘጋጀችው የቪዲዮ ፊልም ለሽልማት መብቃቱ ተነገረ። ቪዲዮ ፊልሙ ለአሸናፊነት እንዲበቃ ካበቁት የመመዘኛ ሥራዎች መካከል በአርማው አቀራረብ ፣ በቪዲዮ ምስል እና በግራፊክ ሥራው ላይ ያሳየው ከፍተኛ ጥራት እና ግልጽነት መሆኑ ታውቋል። የሽልማት አሰጣጡ ሥነ-ሥርዓት በማድሪድ ከተማ ማክሰኞ ሰኔ 22/2013 ዓ. ም መፈጸሙ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በስፔን ዋና ከተማ ማድሪድ የተካሄደው 15ኛ ዙር ዓለም አቀፍ ማህበራዊ ማስታወቂያ ፌስቲቫል ላይ የቀረበውን የፊልም ሥራ ለሕዝብ ይፋ ያደረጉት በጳጳሳዊ ምክር ቤት የሐይማኖት ተቋማት የጋራ ውይይት አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት ከቅድስት መንበር መገናኛ ጽሕፈት ቤት እና ከሰብአዊ ወንድማማችነት ከፍተኛ ኮሚሽን ጋር በኅብረት መሆኑን በጳጳሳዊ ምክር ቤት የሐይማኖት ተቋማት የጋራ ውይይት አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት በጋዜጣዊ መግለጫው አስታውቋል።

ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ወንድማማችነት ቀን

አሸናፊ የሆነው የቅስቀሳ ፊልሙ በውስጡ የአርማ ንድፍ እና ስዕላዊ ክፍል ያለው መሆኑ ታውቋል። የአንድ ከተኩል ደቂቃ ቪዲዮ ፊልሙ በ 22 ቋንቋዎች የተተረጎመ ሲሆን ፊልሙን በጳጳሳዊ ምክር ቤት የሐይማኖት ተቋማት የጋራ ውይይት አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት ድረ ገጽ ላይ መመልከት የሚቻል መሆኑ ታውቋል። ዓለም አቀፍ ሰብዓዊ ወንድማማችነት ቀን ለመጀመሪያ ጊዜ ጥር 27/2013 ዓ. ም ተከብሮ ማለፉ ይታወሳል።

የሰው ልጆች በሙሉ በሰላም እና በአንድነት የሚኖሩበት ቀን መታሰቢያ

የ“ሰብዓዊ ወንድማማችነት” ሰነድ ስምምነት ር. ሊ. ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከግብጹ የአል አዛር ታላቁ መስጊድ ኢማም ከሆኑት ከአህመድ አል ጣይብ ጋር በአቡ ዳቢ ከተማ ጥር 27 ቀን 2011 ዓ. ም መፈራረማቸው ይታወሳል። ስምምነቱ ከተደረገ ከሁለት ዓመት በኋላ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የ “ሰብዓዊ ወንድማማችነት” ሰነድ ስምምነት የሰው ልጆች በሙሉ በሰላም እና በአንድነት የሚኖሩበት ቀን መታሰቢያ ሆኖ ጥር 27 በየዓመቱ እንዲከበር መወሰኑ ይታወሳል። ር. ሊ. ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከግብጹ የአል አዛር ታላቁ መስጊድ ኢማም ከሆኑት ከአህመድ አል ጣይብ ጋር በአቡ ዳቢ ከተማ ጥር 27 ቀን 2011 ዓ. ም መገናኘታቸው “ሁላችንም ወንድማማቾች ነን” የሚለውን ሦስተኛ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን ለመጻፍ ያነሳሳቸው መሆኑን የሐይማኖት ተቋማት የጋራ ውይይት አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት አስታውቋል።

የማድሪድ ሽልማት ሥነ-ሥርዓት

በስፔን ማድሪድ ከተማ ማክሰኞ ሰኔ 22/2013 ዓ. ም በተካሄደው የሽልማት አሰጣጥ ሥነ-ሥርዓት ላይ ተገኝተው ሽልማቱን የተቀበሉት የማድሪድ ከተማ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ ካርዲናል ካርሎስ ኦሶሮ ሴራ፣ በጳጳሳት ጽሕፈት ቤት የሚዲያ ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ሮድሪጎ ፒኔዶ እና የላ ማቺ ኮሚኒኬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ የሆኑት አቶ ዩዋን ዴላ ቶሬ መሆናቸው ታውቋል። በቅድስት መንበር ስም ሽልማቱን የተቀበሉት ብጹዕ ካርዲናል ካርሎስ ኦሶሮ ሴራ፣ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ “ሁላችንም ወንድማማቾች ነን” በሚለው ሐዋርያዊ ቃለ  ምዕዳናቸው “በጋራ ጉዞ ወቅት ከመካከላችን በአንዳችን ጉዳት ቢደርስ በዝምታ ማለፍ አንችልም” ማለታቸውን አስታውሰው፣ ዓለም አቀፍ የ“ሰብዓዊ ወንድማማነት” ቀን እንደሚያስገነዝበን ሁሉ ማኅበራዊ ወዳጅነትን መመስረት የሚቻል መሆኑን አስረድተዋል። አክለውም ሽልማቱ ሰብዓዊ ወንድማማችነት የሚለውን የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን ለመላው ዓለም ለማሳወቅ የሚያግዝ መሆኑን ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ ካርዲናል ካርሎስ ኦሶሮ ሴራ አስረድተዋል።

በጳጳሳዊ ምክር ቤት የሐይማኖት ተቋማት የጋራ ውይይት አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት በጋዜጣዊ መግለጫው እ. አ. አ በ2018 ዓ. ም በተካሄደው የቪዲዮ ፊልም ውድድር በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት አሸናፊ እንደነበር አስታውሷል።   

01 July 2021, 16:27