ፈልግ

በሶሪያ የቅስድት መንበር እንደራሴ ብጹዕ ካርዲናል ማርዮ ዘናሪ በሶሪያ የቅስድት መንበር እንደራሴ ብጹዕ ካርዲናል ማርዮ ዘናሪ   (Vatican Media)

ብጹዕ ካርዲናል ዘናሪ፣ የሶርያ ሕዝብ ከጦርነት ወደ ድህነት መግባቱን ገለጹ

በሮም ከተማ የተካሄደውን የምሥራቅ አብያተ-ክርስቲያናት የዕርዳታ ማስተባበሪያ ጉባኤን የተካፈሉት፣ በሶሪያ የቅስድት መንበር እንደራሴ ብጹዕ ካርዲናል ማርዮ ዘናሪ ለዓለሙ ማኅበረሰብ የዕርዳታ ጥሪያቸውን አቅርበዋል። ብጹዕነታቸው ለዓለሙ ማኅበረሰብ ባቀረቡት ጥሪ ከአሥር ዓመታት በላይ ጦርነት ባስከተለው መከራ ሲሰቃይ የቆየውን የሶርያ ሕዝብ ድህነት እያስጨነቀው መሆኑን ገልጸው፣ በችግር ውስጥ የምትገኘውን ሊባኖስ በጸሎት ማስታወስ እንደዚሁም ሰብዓዊ ዕርዳታን ማቅረብ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸው፣ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በተመሳሳይ መንገድ ለሶርያም የዕርዳታ እጁን ቢዘረጋላት መልካም ነው ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ከ2000 ዓ. ም ጀምሮ በሶርያ የቅድስት መንበር እንደራሴ ሆነው በማገልገል ላይ የሚገኙት ብጹዕ ካርዲናል ማርዮ ዘናሪ ዓመታዊውን የቅዱሳን ጴጥሮስ እና ጳውሎስ በዓል ለማክበር ወደ ሮም መምጣታቸው ታውቋል። የክብረ በዓሉን መስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ከር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ እና ከሌሎች ብጹዓን ካርዲናሎች እና ጳጳሳት ጋር ሆነው ያቀረቡት ካርዲናል ዘናሪ ከመስዋዕተ ቅዳሴው ጸሎት በኋላ በቅዱስ ጴጥሮስ መካነ መቃብር ፊት ቀርበው በድህነት፣ በኤኮኖሚ ማዕቀብ እና በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት በከፍተኛ ጉዳት ውስጥ የምትገኝ ሶርያን በጸሎታቸው አስታውሰዋታል። የቅዱሳን ጴጥሮስ እና ጳውሎስ መንፈሳዊነት ጠንካራ ነው ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ዘናሪ፣ ከአርባ ዓመታት በላይ ቅድስት ቤተክርስቲያንን እያገለገሉ መቆየታቸውን እና ከእነዚህ ዓመታት ውስጥ አሥራ ሁለቱን በቅዱስ ጳውሎስ ከተማ በሆነች ደማስቆስ የቅድስት መንበር እንደራሴ ሆነው ማገልገላቸውን አስታውሰዋል። ብጹዕ ካርዲናል ዘናሪ በሮም ቆይታቸው በምሥራቅ አብያተ-ክርስቲያናት የዕርዳታ ማስተባበሪያ ጉባኤን የተካፈሉ ሲሆን፣ በዚህ ወቅት እንዳስታወቁት ሶርያ ባሁኑ ጊዜ በአምስት የተለያዩ አካባቢዎች በሠፈሩ እና የራሳቸውን የመገበያያ ገንዘብ በሚጠቀሙ የአምስት አገራት ሠራዊት የተያዘች መሆኗን ገልጸው፣ “ቅድስት መንበር እና ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሶርያ ራሷን የቻለች፣ ብሔራዊ አንድነቷንም ያስጠበቀች አገር እንድትሆን ተስፋ የሚያደርጉ ቢሆንም እውነታው ግን የተለየ ነው” ብለዋል።

የክርስቲያኖች መሰደድ ያስከተለው ህመም

ብጹዕ ካርዲናል ማርዮ ዘናሪ ከቫቲካን ዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ዛሬም ቢሆን የሶርያ ሕዝብ የሚገኝበት ሁኔታ የመከራ ሕይወት መሆኑን ገልጸው፣ ላለፉት አሥር ዓመታት በአገሪቱ ውስጥ የተካሄደው ጦርነት ሕዝቡን ወደ ድህነት እና ረሃብ የከተተው መሆኑን አስረድተዋል። ብጹዕነታቸው አክለውም ከጦርነቱ በኋላ በሶርያ ውስጥ የክርስቲያን ማኅበረሰብ ቁጥር መቀነሱንም ገልጸው፣ በሶርያ ውስጥ ከሁለት ሽህ ዓመታት በላይ የኖረው ክርስቲያን ማኅበረሰብ ለባሕል ዕድገት፣ ለትምህርት እና ለጤና አገልግሎት እንዲሁም ለፖለቲካ ዕድገት ትልቅ አስተዋጽዖ ማበርከቱን አስታውሰዋል። በሶርያ ጦርነት ከመጀመሩ በፊት የካቶሊክ፣ ኦርቶዶክስ እና ወንጌላዊያንን ጨምሮ የክርስቲያኖች ቁጥር ወደ አንድ ሚሊዮን ከግማሽ እንደሚሆን አስረድተው ዛሬ ግን በሶርያ ውስጥ የሚገኝ የክርስቲያን ማኅበረሰብ ቁጥር ከአምስት መቶ ሺህ አይበልጥም ብለዋል።

በአገሪቱ የሚታየው የጸጥታ ሁኔታ ምን እንደሚመስል የገለጹት ብጹዕ ካርዲናል ዘናሪ፣ በሶርያ ውስጥ በአንዳንድ ሥፍራዎች የከባድ ጦር መሣሪያ ድምጽ እንደሚሰማ ገልጸው በተለይም በሰሜን ምዕራብ የአገሪቱ ክፍል በኢድሊብ አውራጃ ግጭቶች መኖራቸውን ገልጸዋል። በሶርያ ውስጥ ከጦርነቱ ማግስት ጎልቶ የሚታየው ረሃብ መሆኑን ያስታወቁት ብጹዕ ካርዲናል ዘናሪ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንዳስታወቀው ከሶርያ ሕዝብ መካከል 90 ከመቶ የሚሆነው በከፍተኛ የድህነት ሕይወት ውስጥ የሚገኝ መሆኑን ገልጸው፣ ከአሥር ዓመታት ጦርነት በኋላ ጥፋት እንጂ የመሠረተ ልማት ግንባታ ሊታይ አይችልም ብለዋል።

በአገሪቱ የተጣለው የኤኮኖሚ ማዕቀብ ከፍተኛ ጉዳት ማስከተሉን የገለጹት ብጹዕ ካርዲናል ዘናሪ፣ ከዚህም በተጨማሪ በአገሪቱ የሙስና መስፋፋት እና ብልሹ አስተዳደር ችግሩን የከፋ አድርጎታል ብለዋል። በፋይናንስ ዘርፍ ሊባኖስን ያጋጠማት ኤኮኖሚያዊ ቀውስ ለሶርያም ተርፏል ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ዘናሪ በሶርያ ውስጥ በሚገኙት ሀገረ ስብከቶች የተጀመሩ ፕሮጄክቶች እንቅፋት ያጋጠማቸው መሆኑን አስረድተዋል።

ብጹዕ ካርዲናል ዘናሪ በሮም ከተማ በተካሄደውን የምሥራቅ አብያተ-ክርስቲያናት የዕርዳታ ማስተባበሪያ ጉባኤ መካፈላቸውን ገልጸው፣ በጉባኤው ወቅት ባገኙት ዕድል የሶርያ ሕዝብ የሚገኝበትን ከፍተኛ የድህነት ሕይወት ማስረዳታቸውን ገልጸዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ለሶርያ ሰላም ያጸደቀው ድንጋጌ አንቀጽ 2254 ተግባራዊ እንዲያደርግ አሳስበዋል። አክለውም በሰላሙ ሂደት የሚሳተፉት በሙሉ ለሰላም ያላቸውን መልካም ፈቃድ እንዲገልጹ ጠይቀው በተለይም አሜሪካ እና የአውሮፓ ኅብረት ለሚያቀርበው ሰብዓዊ ዕርዳታን ደማስቆም የበኩሉን አስተዋጽዖን እንዲያደርግ ጠይቀው እነዚህ ሦስቱ ወገኖች የበኩላቸውን ጥረት ካላሳዩ በስተቀር የረባ ውጤት ማምጣት የማይቻል መሆኑን አስረድተዋል። ሊባኖስን ያጋጠማት ኤኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ  ቀውስ በሶርያ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖን እንዳስከተለ የተናገሩት ብጹዕ ካርዲናል ዘናሪ፣ የምሥራቅ አብያተ-ክርስቲያናት የዕርዳታ ማስተባበሪያ ጉባኤ በሌሎች የመካከለኛው ምሥራቅ አገሮችም መልካም ውጤቶችን እንደሚያስገኝ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል። አክለውም የመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ካቶሊካዊ ብጹዓን ፓትሪያርኮች ከር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ጋር ተገናኝተው መወያየታቸው ልዩ ተስፋን የሚያበረክት መሆኑን በሶርያ የቅድስት መንበር እንደራሴ ሆነው በማገልገል ላይ የሚገኙት ብጹዕ ካርዲናል ማርዮ ዘናሪ ከቫቲካን ዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ገልጸዋል።          

01 July 2021, 16:21