ፈልግ

ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን  

ካርዲናል ፓሮሊን፣ በጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቶች ዘንድ የሚደረግ ተሃድሶ ለር. ሊ. ጳጳሳት አገልግሎት እንደሆነ ገለጹ

የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ፣ ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን በፈረንሳይ ውስጥ የሰሜን ምሥራቅ ክፍለ ሀገር ከተማ ወደ ሆነች ስትራስቡርግ ከመጓዛቸው አስቀድመው “La Croix” ከተባለ ካቶሊካዊ የፈረንሳይ ዕለታዊ ጋዜጣ ጋር ቃለ ምልልስ አድርገዋል። ቫቲካን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቶች መካከል እያካሄደች ባለችው የተሃድሶ ሂደት መልካም ውጤቶችን እንደምታመጣ፣ በርካታ ጉዳዮችም ግልጽነት እንዲኖራቸው የሚደረግ መሆኑን አስታውቀዋል። በተሃድሶ ወቅት ውይይት ከሚደረግባቸው ርዕሠ ጉዳዮች መካከል፥ ለሕይወት የሚሰጥ ሥነ-ምግባራዊ ጥበቃ እና በሃይማኖት ውስጥ የሚፈጠር መለያየት የሚሉ እንደሚገኙበት አስረድተዋል። በእነዚህ ርዕሠ ጉዳዮች ላይ ካቶሊካዊ ምዕመናን ድምጻቸውን ማሰማት እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል። የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ፣ ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን በፈረን

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

አዲስ በጸደቁት ሕጎች መካከል “ፈረንሳይ እና ማኅበረሰቧ” ፣ “ካቶሊካዊ ምዕመናን በማኅበራዊ እና ፖለቲካው ዘርፍ ያላቸው ሚና” የሚሉ ርዕሰ ጉዳዮች የሚገኙ መሆኑን ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን አስርድተዋል። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በሚቀጥሉት የሐዋርያዊ ጉብኝት መርሃ ግብራቸው መሠረት ወደ ፓሪስ ለመጓዝ ምኞት ያላቸው መሆኑን ብጹዕ ካርዲናል ፓርሊን ገልጸዋል። አክለውም የቤተክርስቲያኒቱ ሕመም የሆነው የሕጻናት ወሲባዊ ጥቃት እና በልዩ ልዩ ጳጳሳዊ ምክር ቤቶች ውስጥ በመካሄድ ላይ የሚገኘው የተሃድሶ መርሃ ግብር መኖሩንም በቃለ ምልልሳቸው አስረድተዋል።           

“እውነታው ይወጣል ብለን ተስፋ እናደርጋለን”

ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን በሰሜን ምሥራቅ የፈረንሳይ ከተማ በስትራስቡርግ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ በለንደን ከተማ ስለሚገኝ የቫቲካን ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት ሕንጻ እና በመጭው ሐምሌ 20/2013 ዓ. ም. በቫቲካን ፍርድ ቤት እንደሚቀርብ በሚጠበቀው የክስ ሂደት በማስመልከት ማብራሪያ ሰጥተዋል። በዚህ የክስ ሂደት እውነቱ እንደሚወጣ ተስፋ እንዳላቸው ገልጸው፣ ውጤቱ ለሁለቱ ወገን መልካም እንደሚሆን ገልጸዋል። ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን በመግለጫቸው “ትክክለኛ እውነት በእግዚአብሔር ዘንድ ያለች ናት” ብለው “ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን አጣርቶ የሚሰጠው የፍርድ ውሳኔ ከሰው ልጅ አንደበት የምትወጣ እውነት ናት” ብለዋል።       

በሕጻናት ላይ የተፈጸሙ ወሲባዊ ጥቃት በተመለከተ

በቤተክህነት በኩል በሕጻናት ላይ የተፈጸሙ ወሲባዊ ጥቃቶችን የሚያጣራ ነፃ ኮሚሽን በፈረንሳይ መቋቋሙን ያስታወሱት ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን በአጭር ጊዜ ውስጥ ይፋ ሊደረግ ይገባል ነበር ብለው፣ ነጻ ኮሚሽኑ እውነቱን ይፋ በሚያደርግበት ጊዜ በቤተክርስቲያኒቱ ከፈተኛ ሕመምን የሚያስከትል መሆኑን ተናግረዋል። ቢሆንም ለእውነት መፍራት እንደማይገባ አሳስበዋል። ከብዙሃን መገናኛ በኩል በሚደርሳቸው ዜና በርካታ ካቶሊካዊ ምዕመናን የሚያፍሩበት ጉዳይ እንደሚሆን የገለጹት ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን ሆኖም ይህን ሕመም በጸጋ መቀበል እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። ከዚህ ሕመም በኋላ ይህን የመሰለ ስህተት ሁለተኛ እንዳይደገም ትምህርትን እና ተግሳጽ የምንወስድበት ይሆናል ብለዋል።

የቤተክርስቲያኗን ስም ከሚያጠፉ ድርጊቶች መቆጠብ

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በጳጳስዊ ምክር ቤቶች በመካሄድ ላይ ያለ የተሃድሶ መርሃ ግብርን ያስታወሱት ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን፣ በካርዲናሎች መማክርት ውስጥ እርሳቸውም በአባልነት መሳተፋቸውን ገልጸው፣ የተሃድሶ መንገዱ “መልካም እረኛ” በሚለው በቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ሰንድ ላይ መሠረት በማድረግ የሚሰጡ ፍርዶች በሙሉ የቤተክርስቲያኒቱን ሕገ ቀኖና የሚከተሉ መሆኑን አስረድተዋል። ሰንዱን ይፋ ለማድረግ የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስን ሙሉ ፈቃድ ማግኘት የሚያስፈልግ መሆኑን ገልጸው፣ ይህን በመሰለ ሰፊ የካርዲናሎች መማክርት ውስጥ የሚደረግ የተሃድሶ ውጤት መስዋዕትን ሊያስከፍል የሚችል መሆኑን አስረድተዋል። ሆኖም በጳጳስዊ ጽሕፈት ቤቶች የሚደረጉ የተሃድሶ እንቅስቃሴዎች የር. ሊ. ጳጳጳሳት ሐዋርያዊ አገልግሎት ፍሬያማ ለማድረግ መሆኑ በእውነተኛ እና ቅን ፍላጎት በመመስረት የሚደረግ ተሃድሶ መሆኑን አስረድተው፣ ከዚህ በኋላ የቤተክርስቲያኗን ያለፉ ድካሞቿን ከንቱ ከሚያስቀሩ፣ ገጽታዋንም ከሚያበላሹ ተግባራት መቆጠብ እንድሚያስፈልግ አሳስበዋል።

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በቅርብ ጊዜ ውስጥ በፈረንሳይ ሐዋርያዊ ጉብኝት የማድረግ ዕቅድ የላቸውም

ር. ሊ. ጳ ጳጳስት ፍራንችስኮስ ወደ ልዩ ልዩ አገራት የሚያደርጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት በማስታወስ ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን እንደተናገሩት፣ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በፈረንሳይ ሐዋርያዊ ጉብኝት ለማድረግ ምኞት ቢኖራቸውም ነገር ግን በቅርብ ጊዜ ውስጥ የሚከናወን ዕቅድ የሌላቸው መሆኑን ገልጸዋል። ቅዱስነታቸው የፈረንሳዩን ፕሬዚደንት ክቡር አቶ አማኑኤል ማክሮንን በቫቲካን ተቀብለው ባነጋገሯቸው ጊዜ፣ ምንም እንኳን ጊዜውን እና ዕለቱን ባይገልጹትም በፈረንሳይ ሐዋርያዊ ጉብኝት ለማድረግ ምኞት እንዳላቸው መግለጻቸውን ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን አስታውሰዋል። ይህ ምኞታቸው አንድ ቀን እውን እንደሚሆን ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን  ገልጸው፣ ፈረንሳይ በር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ልትጎበኝ የሚገባት አገር መሆኗን አስረተዋል። ቫቲካን ከፈረንሳይ ጋር የመቶ ዓመታት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ያላት አገር መሆኗን አስረድተው በጋራ የሚካፈሏቸው ስጋቶች፣ ከእነዚህም መካከል ሥነ-ምሕዳርን የሚመለከት፣ ቅድስት መንበር የቆመችለት ግንባር ቀደም ዓለም አቀፍ ርዕሠ ጉዳይ መኖሩን ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን ገልጸዋል። ቀጥሎም የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለማስወገድ የተጀመሩ ተግባራት መኖራቸውን ገልጸው በቅድስት መንበር እና በፈረንሳይ መንግሥት መካከል ለምሳሌ ኒውክሌር የጦር መሣሪያ ቅነሳን በተመለከተ አንዳንድ ልዩነቶች መኖራቸውን አስታውሰዋል።

በፈረንሳይ ዓለማዊነት የተፈራ የመወያያ ርዕሥ ነው

በፈረንሳይ ፓርላማ ዓለማዊነት ከፍተኛ የመወያያ ርዕሥ መሆኑን የገለጹት የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ፣ ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን፣ በሃይማኖት ውስጥ የሚፈጠር መለያየት የሚል ርዕሠ ጉዳይ የአገሪቱ መወያያ ርዕሥ መሆኑን ገልጸው ርዕሡ እና የክርስቲያናዊ ድርጅቶች እና የአምልኮ ሥፍራዎች በመንግሥት ቁጥጥር ሥር የሚገኙ መሆኑን አስታውቀዋል። ካርዲናል ፓሮሊን በቃለ ምልልሳቸው በፈረንሳይ ውስጥ የሚታየው ዓለማዊነት ከአገሪቱ ታሪክ ጋር የተዛመደ መሆኑን አስረድተው በተለይ ከፈረንሳይ አብዮት ጋር የተያያዘ መሆኑን አስረድተው፣ በተወሰነ ደረጃ በቤተክርስቲያን እና በመንግሥት መካከል ለተፈጠረው መለያየት ምክንያት መሆኑንም አስታውሰዋል። ቤተክርስቲያን እና መንግሥት የጋራ ዓላማ ያላቸው መሆኑን የገለጹት ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን፣ የጋራ ዓላማቸው ለሰው ልጅ ጥቅም በጋራ መቆም ነው ብለዋል። በአገሪቱ በሚካሄዱ የምርጫ ቅስቀሳዎች መደናገጥ እንደማያስፈልግ ገልጸው የያዙትን ዓላማ እስኪፈጸም ድረስ ወደ ፊት መጓዝ ያስፈልጋል ብለው፣ አለመግባባቶች አመጽን ቀስቅሰው ሰዎችን በግል ደርጃ ወደ ማጥቃትና ጥፋትን ሊያስከትል የሚችሉ መሆኑን የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ፣ ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን “La Croix” ከተሰኘ ካቶሊካዊ የፈረንሳይ ዕለታዊ ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ አስረድተዋል።   

13 July 2021, 16:47