ፈልግ

የእንግሊዝ እግር ኳስ የእንግሊዝ እግር ኳስ 

የስፖርት ዘርፍ ማኅበራዊ ሕይወትን ዳግም ለመጀመር የሚያግዝ መሆኑ ተገለጸ

ኮቪድ-19 ወረሽኝ ካስከተለው ቀውስ በኋላ ማኅበራዊ ሕይወትን ዳግም ለመጀመር የስፖርት ዘርፍ ከፍተኛ እገዛ እንዳለው በጳጳሳዊ ምክር ቤት የባሕል አገልግሎት ፕሬዚደንት የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ጃንፍራንኮ ራቫዚ አስታውቀዋል። በሮም ከተማ በሚገኝ ካቶሊካዊ ዩኒቨሲቲ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት ብጹዕ ካርዲናል ጃንፍራንኮ ራቫዚ ስፖርት እና ቤተክርስቲያን በአንድነት ተባብረው የጋራ ዓላማን የሚያስፈጽሙ ሊሆኑ ይገባል ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ባለፈው ግንቦት ወር ለቫቲካን አትሌቲክ ቡድን አባላት ባስተላለፉት መልዕክታቸው ክርስቲያኖች በስፖርት ዘርፍ በሚሰማሩበት ወቅት፣ ዘርፉ እንደ መንፈሳዊ የሕይወት ልምድ ሁሉ ከሌሎች ጋር መቀራረብን እና ውስጣዊ አንድነትን ለማሳደግ ጥረት የሚደረግበት ዘርፍ እንደሆነ መናገራቸው ይታወሳል። የስፖርት ዘርፍ ሕዝብን ታሳቢ በማድረግ ወደ ሕዝብ ዘንድ የሚቀርብ ተግባር መሆኑን አስረድተው፣ ቤተክርስቲያንም በበኩሏ የሰውን ልጅ ሕይወት የሚቀይሩ እና የሚያበረታትቱ አገልግሎቶችን ለማበርከት እንደምትሠራ ማስረዳታቸውን ብጹዕ ካርዲናል ጃንፍራንኮ ራቫዚ አስታውሰዋል።      

በሮም ከተማ በሚገኝ የቅድስት ማርያም ዕርገት ወይም በመህጻረ ቃሉ “ሉምሳ” ተብሎ  በሚጠራ ካቶሊካዊ ዩኒቨሲቲ ውስጥ በተካሄደው ስብሰባ ላይ በጣሊያን ብሔራዊ ስፖርት ኮሚሽን በተለያዩ ጽሕፈት ቤቶች ተሰማርተው የሚሰሩ አባላት መገኘታቸው ታውቋል። የስብሰባው ተካፋዮች በውይይታቸው በአገሪቱ የስፖርት ዘርፉን ለማሳደግ እና የተሻለ ማኅበረሰብን ለመገንባት ይበልጥ በሕጻናት ላይ ብዙ መሥራት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል። የስብሰባው ተካፋዮች በተጨማሪም በአገሪቱ የበርካታ አቅመ ደካማ ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በስፖርት ዘርፉ የሚካሄዱ እንቅስቃሴዎች እንዲገቱ ማድረጉን አስታውሰዋል። የስፖርት ዘርፉን ለማሳደግ በሰዎች መካከል ሁሉ አቀፍ አንደነትን ማሳደግ እንደሚያስፈልግ ጠቁመው፣ ስፖርት የአንድን ሰው የሕይወት አቅጣጫን እና አመለካከት ለመቀየር የሚችል ማኅበራዊ መድኃኒት መሆኑ ተነግሯል።

በስብሰባው ላይ “ስፖርት እና ደካማ ጎኖች” በሚል ርዕሥ የውይይት መድረክ በማዘጋጀት ላይ የሚገኙት፣ በቅድስት መንበር የምዕመናን፣ የቤተሰብ እና የሕይወት መምሪያ ጳጳሳዊ ምክር ቤት ተወካይ ክቡር አቶ ሳንቲያጎ ፔሬዝ ዴ ካሚኖ ተገኝተዋል። በተጨማሪም ትናንሽ የአውሮፓ መንግሥታት የተሳተፉበትን የሳን ማሪኖ አትሌቲክ ውድድር ያስታወሱት የቫቲካን አትሌቲክ ቡድን ተጠሪ ክቡር አቶ ፖል ገብርኤል ዌይስተን መገኘታቸው ታውቋል። በጣሊያን ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ የመዝናኛ እና የቱሪዝም ሐዋርያዊ አገልግሎት መምሪያ እና የቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ፋውንዴሽን ስፖርት ክፍል በጋራ ባስተላለፉት መልዕክት፣ በጣሊያን በሚገኙት ቁምስናዎች ውስጥ ከስፖርት ለሚገኙ እሴቶች እውቅና የተሰጣቸው እና ስፖርት በማኅበረሰቡ መካከል የሚያበረክተው አገልግሎትም ከፍተኛ መሆኑ ታውቋል።

በስብሰባው መካከል የኦሊምፒክ ውድድሮችን ያስታወሱት ብጹዕ ካርዲናል ጃንፍራንኮ ራቫዚ፣ ስፖርት እና ባሕል የማይነጣጠሉ መሆናቸውን ገልጸው፣ እነዚህን ሁለቱን ነጥሎ ከማየት ይልቅ በቀድሞ ይዘታቸው አንድ ለማድረግ ጥረት ማድረግ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ስፖርትን አስመልከተው ያስተላለፉትን መልዕክቶች በማስታወስ “ስፖርት መሠረታዊ የመኖር ሕልውና የሚገለጽበት” እና “ውስጣዊ ነጻ ስሜት የሚገለጽበት መድረክ ነው” በማለት ብጹዕ ካርዲናል ራቫዚ አስረድተዋል።                

ዓለም አቀፍ የኦሊምፒክ ኮሚቴ ያቀረበው አራተኛ የመፈክር ቃል መኖሩን የገለጹት ብጹዕ ካርዲናል ራቫዚ የኦሎምፒክ ውድድሮች “ፈጣን” ፣ “ከፍተኛ” እና “ጠንካራ” ከሚለው መፈክት በተጨማሪ “አብሮነት” የሚል መታከሉን ገልጸዋል። በጳጳሳዊ ምክር ቤት የባሕል አገልግሎት ፕሬዚደንት የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ጃንፍራንኮ ራቫዚ በመጨረሻም የኦሊምፒክ ውድድሮች በሕዝቦች መካከል የሚደረጉ የስጦታ ልውውጦች ናቸው በማለት አስረድተዋል።

12 July 2021, 16:27