ፈልግ

የቀድሞ ር. ሊ. ጳ ቤነዲክቶስ 16ኛ የቀድሞ ር. ሊ. ጳ ቤነዲክቶስ 16ኛ 

የቀድሞ ር. ሊ. ጳ ቤነዲክቶስ 16ኛ፥ “የሐሰት ትምህርቶች ከእውነተኛው አስተምህሮ ሊያርቁ ይችላሉ”

የቀድሞ ር. ሊ. ጳ ቤነዲክቶስ 16ኛ በጀርመን አገር ከሚታተም ወርሃዊ ጋዜጣ ጋር እምነትን በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ቃለ ምልልስ አድርገዋል። “በዛሬው ዘመን እምነት ወደ ርዕዮተ ዓለም እየተለወጠ የመጣው ለምንድነው?” በሚሉት እና በሌሎች ተጓዳኛ ጥያቄዎች መልስ ሰጥተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በሥነ-መልኮት ጥናት ከፍተኛ ዕውቀት እንዳላቸው የሚታወቁ የቀድሞ ር. ሊ. ጳ ቤነዲክቶስ 16 ኛ (ዮሴፍ ራዚንገር) ለጀርመን ወርሃዊ ጋዜጣ በጽሑፍ በሰጡት መላሽ ሃሳባቸውን በስፋት በማብራራት ገልጸዋል። እስከ ዛሬ ድረስ በሌሎች የሥነ-መለኮት ሊቃውንት በኩል ሰፋ ያሉ አስተያየቶች ያልተሰጡባቸው ርዕሠ ጉዳዮችን በማንሳት ሃሳባቸውን አካፍለዋል።

አንድ አማኝ ስለ እምነቱ በየጊዜው ራሱን የሚጠይቅ፣ ከዕለት ተዕለት የኑሮ እውነታዎች በስተጀርባ ያለውን የእምነት ጉዞን በአዲስ መልክ ለማወቅ ሳያቋርጥ ጥረት የሚያደርግ መሆን አለበት። ይህ ከሆነ እምነት ከእውነተኛው አስተምህሮ ተለይቶ የተሳሳተ ነው የሚያስብል ምንም ዓይነት ምክንያት አይኖርም። የእምነት አስተምህሮ ከገሃዱ ዓለም ተለይቶ እንደ ተፈጥሮ ስጦታ ተደርጎ የሚታሰብ ከሆነ፣ እምነት በአንድ መንገድ ሆነ በሌላ ራሱን በራሱ መሻር ይጀምራል። መንፈሳዊ አስተምህሮ ከእምነት የሚዳብር ነገር ግን እያንዳንዱ ራሱን ችሎ የሚጓዝ መሆ አለበት።

የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በነዲክቶስ 16ኛ በቃለ ምልልሳቸው እንደገልጹት ቤተክርስቲያን በመንፈስ ቅዱስ በመመራት መልዕክቶቿን ከልብ አውጥታ እንድምትናገር ገልጸዋል። ይህ ካለሆነ ቤተክርስቲያን በአስተምህሮ ሥልጣኗ ወይም በመዋቅሮቿ ተግባራዊነት ብቻ የምትመራ ከሆነ ነፍሳትን ወደ ራሷ ከመሳብ ይልቅ እያራቀች ትሄዳለች ብለዋል።  

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በነዲክቶስ 16ኛ እ. አ. አ በ2001 ዓ. ም ገና በጳጳሳዊ ምክር ቤት ውስጥ የእምነት አስተምህሮ ጽሕፈት ቤት አስተባባሪ በነበሩበት ወቅት ያደረጉትን ቃለ ምልልስ ይዞ የወጣው “እግዚአብሔር እና ዓለም” በሚለው የደራሲ ፒተር ሲዎልድ መጽሐፍ ውስጥ እንደገለጹት፣ የእምነት ባሕሪይ “በአንዱ ልብ ውስጥ እንዳለ በሌላው ልብ ውስጥ እንደሌለ ተደረጎ የሚወሰድ ሳይሆን፣ እምነት ሳያቋርጥ በሂደት መካከል በየጊዜው በሰው ልብ ውስጥ የሚፈጠር፣ በሕይወት ዘመናችን ሁሉ መንገድ ሆኖ የሚቀር መሆኑን አስረድተዋል። በመሆኑም እምነት ሁል ጊዜ አደጋ ሊያጋጥመው ስለሚችል እራሱን ወደ ተዛባ ርዕዮተ ዓለም የመቀየር አደጋን ማስቀረቱ መልካም መሆኑን ገልጸዋል። እምነት በሁሉም የኑሮ ደረጃ ፣ በጭንቀት እና ባለማመን መካከል አልፎ ጥንካሬን የሚያገኝ፣ ሕያው እስኪሆን ድረስ በአዲስ ዘመን እንደገና በመጓዝ ጽናትን የሚያገኝ ሂደት መሆኑን አስረድተዋል።     

የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በነዲክቶስ 16ኛ እ. አ. አ በመስከረም 26/2009 ዓ. ም ወደ ፈረንሳይ ሐዋርያዊ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፣ በፈጣሪ የማያምን እና የሚያምን እርስ በእርስ እንደሚደጋገፉ ገልጸው “ካቶሊኮች እምነትን በማግኘታቸው ብቻ ሊረኩ እንደማይገባ፣ ነገር ግን እግዚአብሔርን ለማግኘት በሚያደርጉ ፍለጋ መካከል የበለጠ ከሌሎች ጋር በመነጋገር ፣ እግዚአብሔርን ጥልቀት ባለው መንገድ እንደገና ማወቅ እንዳለባቸው አሳስበዋል።

አማኝ ሁሉ ነገር የተገለጠለት ሳይሆን በዕለት ተዕለት የሕይወት እውነታ ፊት ቆሞ ራሱን የሚጠይቅ እንደሆነ፣ እምነትም ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የተገኘ ንብረት እንዳልሆነ አስረድተው፣ እምነት ወደ ርዕዮተ ዓለማዊ አስተሳሰብ እንዳወርድ አማኝ የማያምኑትን ሰዎች ጥያቄ እና ጥርጣሬ ለማወቅ የሚፈልግ መሆን አለበት ብለዋል። ይህን ሃሳብ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ብዙን ጊዜ በአስተምህሮአቸው መካከል ሲናገሩ እንሰማቸዋለን። ለምሳሌ እ. አ. አ በመጋቢት 25/2017 ዓ. ም ሚላኖ ከተማ ለካህናት፣ ለገዳማዊያን እና ገዳማዊያት ባስተላለፉት መልዕክት፣

ዛሬ ቤተክርስቲያንን በሚያጋጥሟት ፈተናዎች ሳያዝኑ ወንጌልን በነጻነት መስበክ እንደሚያስፈልግ አሳስበው፣ እምነትን ወደ ርዕዮተ ዓለም የመቀየር አደጋ ሊያጋጥም እንደሚችል አስጠንቅቀው እነዚህ ተግዳሮቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እንድናድግ ስለሚያደጉን እርሱን የሚፈልጉ ዓይኖችን እና ልቦችን እግዚአብሔር ክፍት እንዲሆኑ የሚያደርግበት የሕያው እምነት ምልክቶች ናቸው ብለዋል። አክለውም ተግዳሮቶች የሌሉበት እምነት ፣ ሙሉ በሙሉ የተጠናቀቀ እምነት አለመኖሩን ገልጸው፣ ሁሉም ነገር እንደተነገረው እና እንደተገነዘብነው ሆኗል በማለት እምነታችን ወደ ርዕዮተ ዓለማዊነት አስተሳሰብ እንዳይወስደን ምክራቸውን ለግሰዋል።

29 July 2021, 16:45