ፈልግ

በአንዲት ቤተክርስቲያን ውስጥ ያለው ኅብረት ዘወትር በማደግ ላይ መሆኑ ተገለጸ

በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት፣ መስከረም 16/2014 ዓ. ም የሚከበረውን ዓለም አቀፍ የስደተኞች እና ጥገኘት ጠያቂዎች ቀን ምክንያት በማድረግ ዝግጅት በማድረግ ላይ መሆኑ ታውቋል። ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቱ ዕለቱን በጋራ ለማክበር በማለት የተለያዩ መልዕክቶችን በማስተላለፍ እና ቅድመ ዝግጅቶችን በማካሄድ ላይ ሲሆን፣ መመሪያውም “በአንዲት ቤተክርስቲያን ውስጥ ኅብረታችን ዘወትር በማደግ ላይ ይገኛል” በሚለው የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ መሪ ቃል ላይ መሆኑ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት በልዩ ልዩ ቋንቋዎች፣ በፈረንሳይኝ፣ በእንግሊዚኛ፣ በስፔን፣ በሆላንድ፣ በፖርቱጋል እና በጀርመን ቋንቋዎች አቀነባብሮ ይፋ ባደረገው የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የቪዲዮ መልዕክት፣ የተጠመቀ ሁሉ የአንዲት ቤተክርስቲያን እና የአንድ ቤተሰብ አባል መሆኑ ሊሰማው ይገባል ብሏል። የቪዲዮ መልዕክቱ በተጨማሪም ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ “ሁላችንም የአንድ ቤተሰብ አባላት ነን” በማለት ባስተላለፉት መልዕክት፣ በቁምስናዎች በኩል አቀባበል እና እንክብካቤ የተደረገላቸው ስደተኞች የአንድ ቤተሰብ አባል እንደሆኑ የተሰማቸውን ስሜት በምስክርነት የገለጹበት መሆኑ ታውቋል።

መስከረም 16/2014 ዓ. ም የሚከበረውን ዓለም አቀፍ የስደተኞች እና ጥገኘት ጠያቂዎች ቀን በጋራ ለማክበር ዝግጅት እያደረገ የሚገኝ፣ በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት የስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ማስተባበሪያ ክፍል፣ ከተለያዩ ካቶሊካዊ ቁምስናዎች በኩል የሚላኩለትን የጽሑፍ፣ የፊልም እና ፎቶግራፍ ምስክርነቶችን media@migrants-refugees.va በሚለው የኢሜል አድራሻው  ተቀብሎ ለማስተናገድ የተዘጋጀ መሆኑን አስታውቋል። 

07 June 2021, 14:33