ፈልግ

ብጹዕ አቡነ ሪኖ ፊዚኬላ ጋዜጣዊ መግለጫ በሰጡበት ወቅት ብጹዕ አቡነ ሪኖ ፊዚኬላ ጋዜጣዊ መግለጫ በሰጡበት ወቅት  

አቡነ ፊዚኬላ፣ በሴቶች ላይ የሚፈጸም ጥቃት ከድህነት አስከፊ ገጽታዎች አንዱ መሆኑን አስታወቁ

በቅድስት መንበር የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ፕሬዚዳንት፣ ብጹዕ አቡነ ሪኖ ፊዚኬላ፣ በሴቶች ላይ የሚፈጸም ጥቃት ድህነት ከሚያስከትላቸው አስከፊ ውጤቶች መካከል አንዱ መሆኑን፣ ለአምስተኛ ጊዜ የሚከበረውን ዓለም አቀፍ የድሆች ቀን በማስመልከት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቀዋል። በመጭው ኅዳር 5/2014 ዓ. ም ለአምስተኛ ጊዜ የሚከበረውን ዓለም አቀፍ የድሆች ቀን በማስመልከት በቫቲካን ጋዜጣዊ መግለጫቸው ሰጥተዋል። በዚህ መግለጫቸው የድህነት ሕይወት ለመለወጥ የሚያግዙ አንዳንድ አዳዲስ ተግባራት መኖራቸውን አስታውቀው፣ የድህነት ዋና መንስኤ፣ ስለ ሕዝብ ብዛት የሚቀርቡ ጽንሰ-ሐሳቦች እና የርዕዮተ-ዓለም ተጽዕኖዎች መሆናቸውን አስረድተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ከምግብ እጥረት፣ ከሌሎች መሠረታዊ ነገሮች እጥረት እና ከጤና መጓደል በተጨማሪ፣ የድህነትን አስከፊነት አጉልቶ የሚያሳይ፣ በሴቶች ላይ የሚፈጸም ጥቃት መኖሩን ብጹዕ አቡነ ሪኖ ፊዚኬላ አስታውቀው፣ በቫቲካን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ድህነትን አውግዘው፣ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ መጭው ዓመት ለአምስተኛ ጊዜ የሚከበረውን ዓለም አቀፍ የድሆች ቀን ምክንያት በማድረግ ያስተላለፉትን መልዕክት ይፋ አድርገዋል። በዓሉ የሚከበረው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ   በሚያቀርቡት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ሥነ-ሥርዓት መሆኑ ታውቋል።

ዛሬም የእኩልነት እና የሰብዓዊ ክብር እጦት አለ

በቅድስት መንበር የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ፕሬዚዳንት፣ ብጹዕ አቡነ ሪኖ ፊዚኬላ፣ “በሴቶች ላይ የሚፈጸም ጥቃት የድህነት ግልጽ ምልክት ነው” ብለው፣ ጽሕፈት ቤታቸው ለአምስተኛ ጊዜ የሚከበረው ዓለም አቀፍ የድሆች ቀን፣ እ. አ. አ በ2016 ዓ. ም የተጀመረው የምሕረት ዓመት ኢዮቤልዩ ማጠቃለያ በዓል ጋር የሚከበር መሆኑን አስታውቀዋል። የሴቶች እኩልነት ዳብሮ በግልጽ በሚታይበት ባሕል ውስጥ መደረሱን ያስታወቁት ብጹዕ አቡነ ፊዚኬላ፣ የሴቶችን ሕይወት ከሚፈታተን ድህነት ባሻገር እኩልነታቸውን እና ክብራቸውን የሚቀንሱ መገለጫዎችን መቃወም እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

አዲስ የድህነት መግለጫዎች

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ካስከተለው የጤና ቀውስ በተጨማሪ ግልጽ እየሆኑ የመጡ የፍትህ ማጣት እና አዳዲስ የድህነት መገለጫዎች መኖራቸውን ብጹዕ አቡነ ፊዚኬላ ገልጸዋል። አዳዲስ የድህነት መገለጫዎች መኖራቸውን ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የተረዱት መሆኑን ገልጸው፣ የዕለት ምግባቸውን በማጣት ብዙ ሰዎች በችግር ውስጥ መውደቃቸው ከእይታችን የተሰወረ አለመሆኑን ተናግረዋል። “ሰዎች ለምግብ ፍለጋ ከቦታ ቦታ መንከራተታቸው ከድህነት ገጽታዎች አንዱ ነው” ብለዋል።

የግዴለሽነት ልማዶችን መቃወም

በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በሐዋርያዊ መልዕክታቸው “ድሆችን የሚያስረሳ ማንኛውም የግድየለሽነት ልማድ እንዲያጠቃን መፍቀድ የለብንም” ማለታቸውን ያስታወሱት ብጹዕ አቡነ ፊዚኬላ፣ ድሆች ከህብረተሰቡ ውጭ ያሉ ሳይሆኑ፣ የተመቻቸ ሕይወት እንዳይኖሩ ተከልክለው ለመከራ ሕይወት የተጋለጡ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን መሆናቸውን ገልጸው ድሆች እና መከራ የበዛበት ሕይወታቸው፣ ኢየሱስ ክርስቶስ በሰዎች መካከል መኖሩን የሚገልጹ ተጨባጭ ምልክቶች መሆናቸውን አስረድተዋል። በመሆኑም ክርስቲያኖች በዓለም ውስጥ መኖራቸውን በድጋሚ የሚያረጋግጥላቸውን አሳማኝ ምስክርነት ማግኘት ይኖርባቸዋል ብለዋል።

ለመንግሥታት እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች የቀረበ ጥሪ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ለመንግሥታት እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ባስተላለፉት ጥብቅ መልዕክታቸው፣ ጠቃሚ የሆኑ ማኅበራዊ ሞዴሎችን በመከተል፣ በዓለም ላይ የተከሰቱትን አዳዲስ የድህነት ዓይነቶችን በመጪዎቹ አሥር ዓመታት ውስጥ መታገል የሚቻል እንደሆነ መናገራቸውን ብጹዕ አቡነ ፊዚኬላ አስታውሰዋል።

ለኅዳር 5/2014 ዓ. ም የተወጠኑ ዕቅዶች፣

በቅድስት መንበር የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ፕሬዚዳንት፣ ብጹዕ አቡነ ሪኖ ፊዚኬላ፣ ለአምስተኛ ጊዜ የሚከበረው ዓለም አቀፍ የድሆች ቀን ምክንያት በማድረግ በሮም በሚገኙ ቁምስናዎች ለሚኖሩ ድሃ ቤተሰቦች ለማደል የተዘጋጁ አምስት ሺህ የምግብ እሽጎች እና በሮም ከተማ ዙሪያ ለሚገኙ ትምህርት ቤት የሚታደሉ 350 የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ ጭምብሎች መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል። የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መቋቋሚያ መድኃኒት መኖሩ እስከታወቀ ድረስ፣ መድኃኒቱ በሁሉም የዓለማችን ክፍሎች፣ በተቻለ መጠን ለሁሉም ሰው በተለይም ለድሃው ማኅበረሰብ ሊዳረስ እንደሚገባ፣ ብጹዕ አቡነ ሪኖ ፊዚኬላ አደራ ብለዋል።

15 June 2021, 16:30