ፈልግ

በቅድስት መንበር ለሕዝቦች የወንጌል አገልግሎት ማስፋፊያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ታሪክ በአጭሩ

በቅድስት መንበር ለሕዝቦች የወንጌል አገልግሎት ማስፋፊያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት የር. ሊ. ጳጳሳትን ሐዋርያዊ አገልግሎት ከሚደግፉ ጽሕፈት ቤቶች መካከል አንዱ ነው። ይህን ጳጳሳዊ ጽሕፈት የሚመሩት ብጹዕ ካርዲናል ሉዊስ አንቶኒዮ ታግለ ናቸው።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ለሕዝቦች የወንጌል አገልግሎት ማስፋፊያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት በወንጌል አገልግሎት እና በቤተክርስቲያን ታሪክ ውስጥ አራት መቶ ዓመታትን ያስቆጠረ ነው። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ብዙ ጊዜ በንግግራቸው ከማኅበረሰብ መካከል የተገለሉ ሰዎች እና አካባቢዎችን እንደሚያስታውሱ ሁሉ በቅድስት መንበር ለሕዝቦች የወንጌል አገልግሎት ማስፋፊያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት የአገልግሎት አድማስም ለሰዎች የወንጌል አገልግሎትን ማዳረስ በመሆኑ ተግባሩን በውጤታማነት ለመፈጸም እውነተኛ ጥሪ፣ ኃይል፣ ጥበብ ያላቸው ሰዎች እና ተቋማት እንዲኖረው ይፈልጋል። አገልግሎቱ የበርካታ ሰዎች ተሳትፎን የሚጠይቅ እና በዓመት ሃያ አምስት ሚሊዮን ዩሮ ወጭን የሚጠይቅ መሆኑን ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቱ የሚመሩት ብጹዕ ካርዲናል ሉዊስ አንቶኒዮ ታግለ ገልጸዋል። የጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቱ ሃላፊ ብጹዕ ካርዲናል አንቶኒዮ ታግለ የጽሕፈት ቤቱን አገልግሎት፣ የሥራ እቅዶችን እና የተቋቋመበትን ዋና ዓላማ በዝርዝር ገልጸዋል።

በቅድስት መንበር ለሕዝቦች የወንጌል አገልግሎት ማስፋፊያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት በቀዳሚነት ለሕዝቦች የወንጌል ተልዕኮ አገልግሎትን ማቅረብ እና አዳዲስ ቤተክርስቲያኖችን ማነጽ ነው። የእምነት ማስፋፊያ ጽሕፈት ቤት ከተቋቋመበት እ. አ. አ ከ1622 ዓ. ም. ጀምሮ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ዋና ዓላማውን ሳይዘነጉ ትክክለኛ አቅጣጫን ሲያሳዩ እና ሲመሩ ቆይተዋል። ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቱ ለሰዎች በሚያቀርበው ፍሬያማ የወንጌል አገልግሎት በኩል ብቃቱን ሲያስመሰክር ቆይቷል። ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቱ ከዚህም በተጨማሪ የሮም ሀገረስ ስብከት ጳጳስን ወይም ር. ሊ. ጳጳሳትን በወንጌል ተልዕኮ አገልግሎታቸው ሲያግዝ፣ የጸሎት ሥነ-ሥርዓቶችን ሲያዘጋጅ፣ የክርስቲያናዊ ሕይወት ምስክርነቶችን ሲያበረታታ እና የገንዘብ ድጋፍም ማድረጉ ይታወቃል። በዚህም ለሕዝቦች የወንጌል አገልግሎት ማስፋፊያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት አገልግሎት በማደግ ላይ ያለች ወጣት ቤተክርስቲያንን ማገልገል ነው።

በቅድስት መንበር ለሕዝቦች የወንጌል አገልግሎት ማስፋፊያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት የወንጌል ተልዕኮ አገልግሎቱን የሚያቀርበው በየአገራቱ የሚገኙ አገልጋዮችን በተለያዩ የአገልግሎት ዘርፎች በማሰማራት ከሌሎች እያንዳንዱ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቶች ጋር በመተባበር የቤተክርስቲያን አንቀጾችን መሠረት በማድረግ የቤተክርስቲያን ሕገ ቀኖናዎችን ሲያጸድቅ ፣ ሲያሻሻል እና ከተግባራዊነት ሲያስቀር ቆይቷል። በወንጌል አገልግሎት ክልል ጳጳሳዊ አገልግሎቶችን ለማበርከት አዳዲስ ጳጳሳትን መሰየም እና የአገልግሎት አቅማቸውን ማሳደግ ተጨማሪ የጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቱ ሃላፊነት ነው። ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቱ በተጨማሪ በእያንዳንዱ ሐዋርያዊ ክልል የሚገኙ ሀገረ ስብከቶችን የሚያገለግሉ ካህናትን ለማፍራት የዘርዓ ክህነት ትምህርት ቤቶችን ማነጽ፣ መሪ ካኅናትን መመደብ፣ ብጹዓን ጳጳሳትን መንከባበብ፣ የገዳማዊያን እና ገዳማዊያት ሕይወትን መንከባከብ፣ ሐዋርያዊ የትምህርተ ክርስቶስ አገልግሎትን መከታተል እና የምዕመናንን መንፈሳዊ ሕይወት መከታተል የሚሉ ይገኝበታል። በዚህም በቅድስት መንበር ለሕዝቦች የወንጌል አገልግሎት ማስፋፊያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ተግባር በሌሎች ጳጳስዊ ጽሕፈት ቤቶች ውስጥ ከሚገኙ መምሪያዎች ጋር በመተባበር የሰፋ ይሆናል።

ለሕዝቦች የወንጌል አገልግሎት ማስፋፊያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት በሚያቀርበው የወንጌል ተልዕኮ ሐዋርያዊ አገልግሎት አዳኙ ኢየሱስ ክርስቶስ ለቤተክርስቲያን የሰጣትን የወንጌል ምስክርነት አገልግሎት ወደ ዓለም ሁሉ ለማድረስ አሁንም ብዙ ይቀረዋል። በእያንዳንዱ ሐዋርያዊ ክልል ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ የቤተክርስቲያን ተቋማት ሐዋርያዊ አገልግሎቶችን በበቂ መልኩ ለሕዝብ የማድረስ ጥሪ አለባቸው። በቅድስት መንበር ለሕዝቦች የወንጌል አገልግሎት ማስፋፊያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ሃላፊነትን እነዚህን የተለያዩ የቤተክርስቲያን መንፈሳዊ ተቋማትን በሰው እና በማቴሪያል አቅም ማደራጀት ነው።

ክቡራት እና ክቡራን አድማጮቻችን፣ በቅድስት መንበር ለሕዝቦች የወንጌል አገልግሎት ማስፋፊያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት የአገልግሎት ድርሻ ሰፊ ቢሆንም በዛሬ ዕለት ያቀረብንላችሁን ጽሑፍ በዚህ እናጠቃልላለን።

29 June 2021, 16:34