ፈልግ

ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ኢቫን ዩርኮቪች ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ኢቫን ዩርኮቪች  

ሊቀ ጳጳስ ኢቫን፣ “ቅድስት መንበር በዓለም ጤና ድርጅት በታዛቢነት መመረጧ ለጋራ ውይይትን ያሳድጋል”

በተባበሩት መንግሥታት እና በተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅት የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ የሆኑት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ኢቫን ዩርኮቪች፣ ቫቲካን በጀኔቭ በሚገኝ የዓለም ጤና ድርጅት ውስጥ በታዛቢነት መመረጧ ለጋራ ውይይትን የሚያሳድግ መሆኑን አስታወቁ። ሊቀ ጳጳሱ በማከልም ቅድስት መንበር የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል የምታደርገው ጥረት መሠረታዊ እና እጅግ አስፈላጊ መሆኑንም ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ኢቫን ዩርኮቪች ቅድስት መንበር በተባበሩት መንግሥታት የዓለም ጤና ድርጅት ውስጥ በታዛቢነት እንድትመረጥ የጣሊያን መንግሥት ላደረገው ጥረት ምስጋናቸውን አቅርበው፣ ቅድስት መንበር በዓለም ጤና ድርጅት ውስጥ በታዛቢነት መመርጧ ድርጅቱ ለ74ኛ ጊዜ ባካሄደው መደበኛ ጉባኤ ላይ መሆኑ ታውቋል። ቅድስት መንበር በዓለም ጤና ድርጅት ውስጥ በታዛቢነት መመረጧ ለሁሉም ታላቅ መነሳሳት እንደሚፈጥር የጣሊያኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ዲ ማርዮ ገልጸዋል። ቅድስት መንበር ለዚህ ደረጃ እንድትበቃ የረዳት ሁለት ነገሮች መሆናቸውን ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ኢቫን ዩርኮቪች ከቫቲካን ዜና አገልጎሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ገለጸዋል።

የመጀመሪያው ቅድስት መንበር በጤናው ዘርፍ ስትሠራ በቆየችባቸው ዓመታት ያስመዘገበችው ከፍተኛ እና አመርቂ ውጤት እና ወደ ፊትም ልታበረክት አቅዳ የተነሳችው ተግባራት መሆኑን ሊቀ ጳጳሱ ገልጸዋል። መላዋ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን በጉልህ ከምታቀርባቸው ማኅበራዊ ሥራዎች መካከል አንዱ የትምህርት ዘርፍ ሲሆን፣ ቤተክርስቲያኗ በዓለማችን ውስጥ 300,000 ትምህርት ቤቶች እና 1000 ዩኒቨርሲቲዎችን በግል ማስተዳደሯ እና በጤናውም ዘርፍ ቢሆን የማኅበረሰቡን ጤና በመንከባከብ ላይ የሚገኙ 110,000 የጤና ተቋማት ያላት መሆኑን ሊቀ ጳጳስ አቡነ ኢቫን ዩርኮቪች አስረድተዋል። ቅድስት መንበር በዓለም ጤና ድርጅት የታወቀችባቸው ሁለት ርዕሠ ጉዳዮች፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ለመከላከል እና ለመቆጣጥር ያደረገችው ከፍተኛ ጥረት እና ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ወረርሽኙን ለመከላከል የተጓዙበት መንገድ፣ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የጤና ተቋማት እና ድርጅቶች ጋር በመተባበር ያደረጉት ከፍተኛ ጥረት መሆኑን አስረድተዋል። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ዓለም አቀፍ ችግሮች በዓለም አቀፍ ደረጃ መፈታት እንዳለባቸው በጽኑ የሚያምኑ መሆኑን ሊቀ ጳጳስ አቡነ ኢቫን ዩርኮቪች ገልጸዋል።

በቁጥር በርካታ የሆኑ ካቶሊካዊ የማኅበራዊ ጤና ተቋማት ባደጉት አገሮች፣ በአሜሪካ እና በአውሮጳ ውስጥ መኖራቸውን ሊቀ ጳጳስ አቡነ ኢቫን አስታውሰው፣ በጀርመን እና በስፔን የሚገኙ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ማኅበራዊ የጤና ተቋማት ቁጥር ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል። ቤተክርስቲያኗ የጤና አገልግሎቶችን የምታበረክተው በማደግ ላይ ባሉት አገሮች ብቻ ሳይሆን ባደጉት አገሮችም ጭምር መሆኑን አስገንዝበዋል።

በተባበሩት መንግሥታት እና በተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅት የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ የሆኑት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ኢቫን ዩርኮቪች ከቫቲካን ዜና አገልግሎት ጋር ባደርጉት ቃለ ምልልስ እንደገለጹት፣ ቅድስት መንበር በዓለም ጤና ድርጅት ውስጥ በታዛቢነት መመረጧ እንደ መንግሥት ሆና ሳይሆን ራስ-ገዝ አገር በመሆኗ ነው ብለው፣ ሌሎች አባል አገሮች ግን እንደ መንግሥት መሳተፋቸውን ገልጸው፣ መንግሥታት በዓለም ጤና ድርጅት ውስጥ አባል በሚሆኑበት ጊዜ የሕዝባቸውን የጤና አገልግሎት ለማሳደግ ቢሆንም በጎኑ የራሳቸውን ጥቅም እና ፍላጎት ለማስከበር መሆኑን ሊቀ ጳጳስ ኢቫን ገልጸው፣ ቅድስት መንበር ከዚህ በተለየ መልኩ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውስጥ ታዛቢ ስትሆን የራሷን ጥቅም እና ፍላጎት ለማስጠበቅ ሳይሆን የመላውን ሰው ፍላጎት እና ክብር ለማስጠበቅ እና ከፈጣሪ ዘንድ የተቀበለችውን የአገልግሎት ተልዕኮዋን ለመፈጸም መሆኑን አስረድተዋል።
 

02 June 2021, 15:16