ፈልግ

በ “ፍቅር ሐሴት” ሐዋርያዊ ቅቃለ ምዕዳን ላይ የተካሄደ ሴሚናር በ “ፍቅር ሐሴት” ሐዋርያዊ ቅቃለ ምዕዳን ላይ የተካሄደ ሴሚናር  

ወ/ሮ ገብርኤላ፣ ወላጆች በወንጌል ተልዕኮ አገልግሎት የሚተባበሩ መሆናቸውን አስታወቁ

በቅድስት መንበር የምእመናንና የቤተሰብ ሕይወት መምሪያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት፣ የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ “የፍቅር ሐሴት” የተሰኘው ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን አምስተኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ፣ ሰኔ 5/2013 ዓ. ም. በተዘጋጀው የአውታረ መረብ ሴሚናር፣ ወላጆች በወንጌል ተልዕኮ አገልግሎት ከቤተክርስቲያን አገልጋዮች ጋር የሚተባበሩ መሆናቸውን ወ/ሮ ገብርኤላ ጋምቢኖ አስታውቀዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የምእመናንና የቤተሰብ ሕይወት መምሪያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ባዘጋጀው የአራት ቀናት ሴሚናር ላይ፣ በቤተሰብ ሐውርያዊ አገልግሎት ላይ የተሰማሩ 350 አባላት መካፈላቸው ታውቋል። ሴሚናሩ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ እና በቅድስት መንበር የምእመናንና የቤተሰብ ሕይወት መምሪያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ዋና ጸሐፊ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ኬቪን ፋረል ባስተላለፉት መልዕክት መጠቃለሉ ታውቋል። ሴሚናሩ በቤተሰብ ሐዋርያዊ አገልግሎት ሥራ ላይ የተሰማሩ ግለ ሰቦች የተለያዩ ሃሳባቸውን በማቅረብ የጋራ ውይይት የተደረገበት ሲሆን “የፍቅር ሐሴት” የተሰኘው የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን በተግባር የሚገለጽበትን መንገዶችን መመልከቱ ታውቋል። በቅድስት መንበር የምእመናንና የቤተሰብ ሕይወት መምሪያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ምክትል ዋና ጸሐፊ የሆኑት ወ/ሮ ገብርኤላ ጋምቢኖ ሴሚናሩን በማስመልከት ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደርጉት ቃለ ምልልስ፣ ለቤተሰብ የሚሰጥ ሐዋርያዊ አገልግሎትን በማስመልከት ከቤተሰብ በኩል የሚሰጡ ምስክርነቶች አስፈላጊ መሆናቸውን አስረድተዋል።

ወ/ሮ ገብርኤላ ጋምቢኖ በቃለ ምልልሳቸው ወቅት በቤተሰብ ሐዋርያዊ አገልግሎት ላይ የሚሰማሩ አባላትን ማዘጋጀት እና በተለይም የጋብቻ ሕይወትን በሚመለከቱ ርዕሠ ጉዳዮች ላይ ሰፋ ያሉ ውይይቶችን በማድረግ ልምዶችን መለዋወጥ አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል። አክለውም እነዚህን ጠቃሚ ልምዶች ከተቀረው ዓለም ጋር መጋራት እንደሚያስፈልግ እና ልምዶችም ከቤተሰብ ክፍሎች የሚመነጩ እና የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስን ምኞት የሚገልጹ መሆናቸውን አስረድተዋል። ከጀርመን በመነሳት በአስሩ የአውሮፓ አገሮች እና በብራዚል ውስጥም እየተዳረሰ የሚገኝ፣ የቤተሰብን ሕይወት ለማገዝ የሚሰጥ የሐዋርያዊ አገልግሎት ልምድ፣ በቤተሰብ ሕይወት ውስጥ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለማቃለል የሚያግዝ እና የቤተክርስቲያንን እናትነት እንዲገነዘቡ በማድረግ ረገድ ከፍተኛ እገዛን የሚያደርግ መሆኑን አስረድተዋል።

ለቤተሰብ የሚሰጥ ሐዋርያዊ አገልግሎት በተጠናከረ መንገድ እኒከናወን የማድረጉ ዋና ዓላማ በዛሬው ዓለም ለሚገኙ ቤተሰቦች የሚቀርብ የወንጌል አገልግሎትን ለማሳደግ የሚረዳ መሆኑን ወ/ሮ ገብርኤላ ጋምቢኖ አስረድተዋል። አክለውም ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በመልዕክታቸው ክርስቲያን ባለትዳሮች እና ካህናት ቤተክርስቲያንን በአንድነት ለማገዝ የተጠሩ ናቸው ማለታቸውን አስታውሰዋል። ከዚህም በተጨማሪ ቤተሰቦች የተክሊልን ምስጢር ለመንከባበብ ሐዋርያዊ ተልዕኮ የተጣለባቸው መሆኑን መናገራቸውን አስታውሰዋል። ይህን ልምድ ለማሳደግ የሚያስችል መንፈሳዊ ትምህርቶችን የሚያካፍሉ የቤተክርስቲያን አገልጋዮችን ማዘጋጀት እና ማሰልጠን አስፈላጊ መሆኑን ወ/ሮ ገብርኤላ ጋምቢኖ ገልጸው ቤተሰቦች በዚህ አገልግሎት እንዲሳተፉ የሚጠይቅ የምስጢረ ጥምቀት ጸጋ መኖሩንም አስታውሰዋል። የምስጢረ ተክሊል ጸጋ ቤተሰቦች በወንጌል አገልግሎት ተልዕኮ እንዲሳተፉ እና ከሌሎች ቤተሰቦች ጋር ሆነው ክርስቲያናዊ ሕይወትን አብረው እንዲጓዙ የሚጋብዝ ጥሪ ያለበት ምስጢር መሆኑንም አስረድተዋል።

በቅድስት መንበር የምእመናንና የቤተሰብ ሕይወት መምሪያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት፣ ለጋብቻ ሕይወት ስኬታማነት የሚያግዙ ልዩ ልዩ የተግባር ስልቶችን ማዘጋጀቱን የገለጹት ወ/ሮ ገብርኤላ ጋምቢኖ፣ የተግባር ስልቶቹ በተለይም አዲሱን ትውልድ ለክርስቲያናዊ ጋብቻ ሕይወት የሚያዘጋጁ፣ በጋብቻ ሕይወት ጥሪያቸው ላይ ጥልቅ አስተንትኖን እንዲያደርጉ፣ ስለ እምነታቸው እውቀት እንዲኖራቸው የሚያግዟቸው መሆኑን ገልጸዋል። ክርስቲያናዊ ጋብቻ እውነተኛ ክርስቲያናዊ ፍቅር የሚገለጽበት፣ የሕይወት ምስክርነት በተግባር የሚታይበት በመሆኑ፣ ወጣቱ ትውልድ ከኢየሱስ ክርስቶስ በሚያገኙት እርዳታ በመታገዝ በመካከላቸው መልካም ግንኙነትን በመፍጠር መልካም የጋብቻ ሕይወት መኖር የሚችሉ መሆኑን አስረድተዋል።

ማኅበረሰብ እና ቤተክርስቲያን የክርስቲያናዊ ጋብቻ ታላቅነትን በመገንዘብ፣ ከእርሱ የሚገኘውንም ከፍተኛ ጥቅም በማወቅ ተገቢውን ጥበቃ እና ክብር መስጠት እንደሚገባ ወ/ሮ ገብርኤላ ጋምቢኖ አሳስበው፣ በዓለማችን ውስጥ በቤተሰብ ዙሪያ የሚታዩ ችግሮች በቤተሰብ መካከል ሊኖር የሚገባው እውነተኛ ፍቅር በመጓደሉ መሆኑን አስታውሰው፣ ይህን እክል ለማስወገድ ሴቶች በቤተሰብ ሐዋርያዊ አገልግሎት መሳተፍ አስፈላጊ መሆኑን እና የቤተክርስቲያን ድጋፍ መኖር አስፈላጊ መሆኑን፣ በቅድስት መንበር የምእመናንና የቤተሰብ ሕይወት መምሪያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ምክትል ዋና ጸሐፊ የሆኑት ወ/ሮ ገብርኤላ ጋምቢኖ ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ አስታውቀዋል። 

14 June 2021, 14:38