ፈልግ

በተባበሩት መንግሥታት የምግብ እና እርሻ ድርጅት በተባበሩት መንግሥታት የምግብ እና እርሻ ድርጅት 

አቶ አንድሬያ ሞንዳ፣ “የክርስትና ግብ ፍሬን የሚያፈራ መሆን አለበት” አሉ

“ሎዘርቫቶረ ሮማኖ” በሚል ስም የሚታወቅ የቅድስት መንበር ዕለታዊ ጋዜጣ ዳይሬክተር ክቡር አቶ አንድሬያ ሞንዳ ከብጹዕ ካርዲናል ሄራንዝ ጋር ጾታዊ ጥቃትን በማስመልከት ውይይት ማድረጋቸው ታውቋል። በውይይታቸው፣ አንዳንድ ጊዜ ምዕመናን የዓለም ብርሃን ከመሆን ይልቅ የዓለም ጨለማ ሆነው መገኘታቸውን ገልጸው፣ ይህን ሁኔታ ይፋ ማድረግ ድፍረትን የሚጠይቅ መሆኑን አስረድተዋል። አክለውም ለድክመቶቻችን ምሕረትን ማግኘት የምንችለው ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር በመተባበር ብቻ እንደሆነ አስረድተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የቅድስት መንበር ዕለታዊ ጋዜጣ “ሎዘርቫቶረ ሮማኖ” አገልግሎቱን የጀመረበት 160ኛ ዓመት በመከበር ላይ መሆኑን የጋዜጣው ዳይሬክተር ክቡር አቶ አንድሬያ ሞንዳ ገልጸው፣ ጋዜጣው አገልግሎቱን በጀመረበት ጊዜ “የእውነት ወዳጅ” የሚል ስያሜ ሊሰጠው መታሰቡን አስታውሰው፣ አሁንም ቢሆን አገልግሎቱን በእውነት ላይ በመመስረት እያቀረበ መሆኑን ገልጸው፣ ከጀርመን ውስጥ ጀምሮ የተለያዩ የቤተክርስቲያን ዜናዎችን በማቅረብ ላይ መሆኑን አስረድተዋል።

ባሁኑ ጊዜ አነጋጋሪ ጉዳይ የሆነው እና በጀርመን ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ብቻ ሳይሆን በሌሎች አገራትም በምትገኝ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ውስጥ የሚፈጸሙ ወሲባዊ ጥቃቶችን ከብጹዕ ካርዲናል ጁሊያን ሄራንዝ ከተላከላቸው መልዕክት ጋር በማጣመር በጋዜጣው አምድ ላይ ለማስፈር መወሰናቸውን ክቡር አቶ አንድሬያ ሞንዳ ገልጸዋል። የስፔኑ ጳጳስ እንደገለጹት፣ ለእውነት ባላቸው ፍቅር በመታገዝ፣ ከሁሉም በላይ ቤተክርስቲያን የክርስቶስ አካል መሆኗን በመገንዘብ በ (1ኛ ቆሮ. 12፤27) ላይ የተገለጸውን በማስታወስ፣ ነገር ግን ይህች የክርስቶስ አካል የሆነች ቤተክርስቲያን ስጋ ለባሽ በሆነው ሰው ኃጢአት ምክንያት አስቸጋሪ ጊዜን በማሳለፍ ላይ መሆኗን ክቡር አቶ አንድሬያ ሞንዳ ገልጸዋል። አንዳንድ ሰዎች የዓለም ብርሃን ከመሆን ይልቅ የዓለም ጨለማ መሆንን መምረጣቸውን ያስታወሱት የጋዜጣው ዳይሬክተር፣ በ (ማቴ. 5:16) ላይ “ሰዎች መልካም ሥራችሁን አይተው የሰማይ አባታችሁን እንዲያመሰግኑ የእናንተም ብርሃን በሰው ፊት ይብራ” የሚለውን የቅዱስ ወንጌል ቃል፣ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በወጣቶች ጉዳይ ላይ በተወያየው የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ወቅት በመጥቀስ መልዕክት ማስተላለፉቸውን አስታውሰዋል። ብጹዕ ካርዲናል ጁሊያን ሄራንዝ ለጋዜጣው ክፍል በጻፉት መልዕክት ዛሬ ቤተክርስቲያን የልጆቿን ኃጢአቶች ይፋ ለማውጣት ወደ ኋላ የማትል መሆኗን ተናግረው፣ አንዳንዶች ግን የሠሩትን ኃጢአት ለመሰወር መሞከራቸውን ገልጸዋል።

ቤተክርስቲያን የልጆቿን ኃጢአት ይፋ ለማድረግ ጠንካራ እምነት፣ ድፍረት እና ትህትናን እንደሚጠይቅ አቶ አንድሬያ ሞንዳ ገልጸው፣ የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክቶስ 16ኛ እ. አ. አ ሚያዝያ 24/2005 ዓ. ም ባቀረቡት የመጀመሪያ ስብከታቸው፣ በዮሐ. 21:11 ላይ “ስለዚህ ስምዖን ጴጥሮስ ወደ ጀልባው ገብቶ መቶ ሃምሳ ሦስት ትልልቅ ዓሳዎች የሞላበትን መረብ ወደ ምድር ጎተተ፤ ይህን ያህል ብዙ ዓሣ ቢይዝም መረቡ አልተቀደደም” የሚለውን የቅዱስ ወንጌል ክፍል መጥቀሳቸውን አስታውሰዋል። ቤተክርስቲያን በልጆቿ ስህተት ምክንያት ሐዘን የተሰማት ቢሆንም ኢየሱስ ክርስቶስ ክርስቲያኖች አንድ እንዲሆኑ በማለት ወደ አባቱ ዘንድ ባቀረበው ጸሎቱ ተጽናንተን፣ በእርሱ በኩል ወደሚገኝ አንድነት ለመድረስ ወደ ፈጣሪያችን ዘንድ ጸሎታችንን ማቅረብ እንደሚገባ ተናግረዋል። መሪው አንድ ነው፤ መንጋውም አንድ ነው በማለት የተናገሩት አቶ አንድሬያ ሞንዳ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ የዓሣ ማጥመጃ መረብ እንዲቀደድ የማይፈቅድ መሆኑን ገልጸው “ወደ አንድነት ጎዳና መመለስ እንድንችል የኢየሱስ ክርስቶስን ድጋፍ በጸሎት መጠየቅ ያስፈልጋል” ብለዋል።

ከጀርመን ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በኩል እየተሰማ ያለው ጉዳይ ትህትናን የሚጠይቅ መሆኑን አቶ አንድሬያ ገልጸው፣ በዚህ ጊዜ ትህትና ማለት እውነትን ሳይደብቁ መናገር ማለት እንደሆነ አስረድተዋል። የቀድሞ ር. ሊ. ጳ ቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ በአንድ ወቅት መልዕክታቸው “እኛ ሰዎች ደካሞች ነን”! ማለታቸውን አቶ አንድሬያ አስታውሰው፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስም እንደዚሁ እሁድ ግንቦት 29/2013 ዓ. ም የክርስቶስ ሥጋ እና ደም ማስታወሻ ዓመታዊ በዓል በተከበረበት ዕለት ባቀረቡት ጸሎት “የእግዚአብሔርን ታላቅነት እና ሃያልነት በእጃችን በቀላሉ በምንቆርሰው ዳቦ እንገነዘበዋለን ብለው፣ ይህም እውነተኛ ፍቅርን እና አንድነትን የምናገኝበት ነው” ማለታቸውን ክቡር አቶ አንድሬያ አስታውሰዋል።

ሐዋርያው ጳውሎስ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች በላከው 2ኛ መልዕክቱ ም. 12:10 ላይ “ኃይል የማገኘው ደካማ በምሆንበት ጊዜ ስለሆነ . . .” ማለቱን ክቡር አቶ አንድሬያ ጠቅሰው፣ የክርስትና ግባችን ከሞትን በኋላ ኃይልን በማግኘት ወደ ዘለዓለማዊ ሕይወት መብቃት መሆኑ ክቡር አቶ አንድሬያ ገልጸዋል።

ኢየሱስ ራሱን በቀላሉ በሚቆረስ ዳቦ ማስመሰሉን የገለጹት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ኃይልን እና ጥንካሬን የምናገኘው ከቅዱስ ስጋው እና ደሙ መሆኑን አስረድተው “በፍቅር የተሞላ ኃይሉን በመጋራት ሕይወትን እናገኛለን” ብለዋል። ኢየሱስ ክርስቶስ የካዱትን እና ያሰቃዩት ሳይቀር ይቅር የሚል፣ ኃጢአተኞችንም የሚቀጣ ሳይሆን በስጋው እና በደሙ አዲስ ሕይወትን የሚሰጥ አምላክ መሆኑን ቅዱስነታቸው አስረድተዋል። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በጀርመን ለሚገኙት ካቶሊካዊ ምዕመናን ብቻ ሳይሆን በመላው ዓለም ለሚገኙት ካቶሊካዊ ምዕመናን መልዕክት ማስተላለፋቸውን የገለጹት አቶ አንድሬያ፣ በክርስቶስ ስጋ እና ደም አንድነታችንን በማረጋገጥ፣ ስጋውን እና ደሙን በመቀበል ኃይልን እንደምናገኝ ማሳሰባቸውን ገልጸው “የኢየሱስ ክርስቶስ ምሕረት ሐጢአተኞች እና ደካሞች በመሆናችን ምክንያት የሚፈራን አይደለም” ማለታቸውንም ተናግረዋል።

09 June 2021, 17:40