ፈልግ

በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት የተስፋፋው የድህነት ሕይወት በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት የተስፋፋው የድህነት ሕይወት  

ካርዲናል ታግለ፣ ድሆችን ማገልገል በእግዚአብሔር የማዳን ሥራ መተባበር መሆኑን ገለጹ

በቅድስት መንበር ለሕዝቦች የወንጌል አገልግሎት ማስፋፊያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት አስተባባሪ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ሉዊስ አንቶኒዮ ታግለ፣ የጣሊያን ካቶሊካዊ የቸርነት ሥራ ድርጅት የተቋቋመበት 50ኛ ዓመት መታሰቢያን ምክንያት በማድረግ ባስተላልፉት መልዕክት የተቸገረን መርዳት ሥራ ሳይሆን በእግዚአብሔር የማዳን ሥራ መተባበርን የሚሳይ የፍቅር አገልግሎት መሆኑን አስረድተው ድሆችን በፍቅር ማገልገል እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“የቸርነት መንገድ” በሚል ርዕሥ ሰኔ 18/2013 ዓ. ም ሮም ከተማ በሚገኝ በቅዱስ ጳውሎስ ባዚሊካ ውስጥ በተዘጋጀው የጸሎት ሥነ-ሥርዓት ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት ብጹዕ ካርዲናል ሉዊስ አንቶኒዮ ታግለ፣ ፍቅር በክርስቲያናዊ ትርጉሙ በሃሳብ ወይም በስሜት የሚገልጽ ሳይሆን ከመንፈስ ቅዱስ የተቀበልነው ጸጋ በተግባር የሚገለጽበት መንገድ ነው ብለዋል።

ለጋራ ጥቅም መሥራት

ብጹዕ ካርዲናል አንቶኒዮ ታግለ የቸርነት አገልግሎትን በማስመልከት ባስተላለፉት መልዕክት ሦስት ርዕሠ ጉዳዮችን አንስተው ያስረዱት ሲሆን የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች ሰዎች ራሳቸውን ከሁሉ በላይ አድርገው የሚቆጥሩበት እና የግልግ ፍላጎታቸውን የሚያስፈጽሙበት መንገድ መሆን እንደሌለበት አስረድተው፣ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች የግል ሳይሆኑ ለጋራ ጥቅም የሚውሉ ፍሬዎችን ለማምጣት የምንጓዝባቸው መንገዶች መሆናቸውን አስረድተዋል። ስለሆነም የቸርነት አገልግሎት የግል ዝናን ለማትረፍ ወይም በሰዎች መካከል ተወዳጅነትን ለማግኘት የሚረዳ የግብዝነት መሣሪያ ሳይሆን ለፍቅር ስንል የተቸገሩትን የምንረዳበት መንገድ መሆን አለብት ብለው፣ ሌሎችን የምንረዳው ስለምናፈቅራቸው ነው በማለት አስረድተዋል።

የቸርነት አገልግሎት በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት

የካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ዓለም አቀፍ በጎ አድራጊ ድርጅት ፕሬዚደንት ብጹዕ ካርዲና አንቶኒዮ ታግለ በኮቪድ ወረርሽኝ ወቅት ሕዝብን ግንዛቤ ለማስጨበጥ በላኩት መልዕክት፣ በውስጣችን ያለው ፍቅር በስቃይ ውስጥ ለሚገኙት ትዕግስትን፣ አስተዋይነትን፣ ሰው አክባሪነትን እና ትህትናን እንድናሳይ ያደርገናል ብለዋል። የሰዎችን ስቃይ በቅርብ ሆኖ መመልከት ወንድማዊ ፍቅርን እንድናሳይላቸው ያደርገናል ያሉት ብጹዕ ካርዲናል አንቶኒዮ ታግለ፣ ብዙ የካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በጎ አድራጊ ድርጅት ሠራተኞች በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት ወንድማዊ ፍቅርን ለመግለጽ የበኩላቸውን ጥረት ማድረጋቸውን አስታውሰው፣ የጣሊያን ካቶሊካዊ ዕርዳታ ሰጭ ድርጅቶችም በችግር ውስጥ ለሚገኙት ያላቸውን አንድነትን በመግለጽ ፍቅርን በተግባር እንዲያሳዩ አደራ ብለዋል። የጣሊያን ካቶሊካዊ ዕርዳታ ድርጅት ምስረታ 50ኛ ዓመት መታሰቢያን ምክንያት በማድረግ በተዘጋጀው የጸሎት ሥነ ሥርዓት ላይ የድርጅቱ ሊቀመንበር የሆኑት ብጹዕ አቡነ ካርሎ ሮቤርቶ እና የድርጅቱ ዳይሬክተር ክቡር አባ ፍራንችስኮ ሶዱ የተገኙ ሲሆን፣ በጸሎቱ ሥነ-ሥርዓት ላይ ጳጳሳዊ አስተምህሮች ለአስተንትኖ መቅረባቸው ታውቋል።  

ከር. ሊ. ጳ ጋር የተደረገ ግንኙነት

የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ጳውሎስ ስድስተኛ እ. አ. አ 1971 ዓ. ም ሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ ባስጀመረው የተሃድሶ መርሃ ግብር መሠረት፣ በጣሊያን ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ የሚመሩ 220 የዕርዳታ ድርጅቶች በሀገረ ስብከቶች ውስጥ መመስረታቸው ይታወሳል። የዕርዳታ ድርጅቱ የተመሰረተበት 50ኛ ዓመት ለማክበር ዝግጅት ሲጀመር በሁለት ርዕሠ ጉዳዮች ላይ ማትኮሩ ሲታወስ የመጀመሪያ እ. አ. አ ከ2019 - 2020 ዓ. ም ድረስ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ባስከተለው ቀውስ ምክንያት ያጋጠሙትን ችግሮች ለመቋቋም ጥረት ማድረግ ሲሆን ሁለተኛው እ. አ. አ ከ2020 - 2021 ዓ. ም. ድረስ የዕርዳታ ድርጅቱ በቀጣይ ዓመታት ተግባራዊ ለማድረግ ባቀዳቸው ተግባራት ላይ ተወያይቶ የመፍትሄ ሃሳቦችን ያሰባሰበበት ዓመት መሆኑ ታውቋል። የጣሊያን ካቶሊካዊ ዕርዳታ ድርጅት የተቋቋመበት 50ኛ ዓመት መታሰቢያ የጸሎት ሥነ-ሥርዓት የተጠቃለለው የድርጅቱ አባላት ቅዳሜ ሰኔ 19/2013 ዓ. ም. ከር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ጋር በቫቲካን ውስጥ በተገናኙበት ሥነ-ሥርዓት መሆኑ ታውቋል።        

28 June 2021, 16:14