ፈልግ

ቫቲካን ለ300 ሰዎች የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ ክትባት መስጠት ጀመረች ቫቲካን ለ300 ሰዎች የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ ክትባት መስጠት ጀመረች  

ቫቲካን የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ ክትባትን ለድሃ ቤተሰቦች ማከፋፈሏን አስታወቀች

ቫቲካን ካለፈው ጥር ወር 2013 ዓ. ም ጀምሮ በሮም እና ቫቲካን አካባቢዎች ለሚገኙ 1,800 ድሃ ቤተሰቦች የኮቪዲ-19 መከላከያ ክትባትን መሰጠቷ ታውቋል። በሌላ ወገንም ቅድስት መንበር በማደግ ላይ ያሉ አገሮች የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል እንዲያግዛቸው ለአፍሪካ እና እስያ አገራትን በእንደራሴዎቿ በኩል ድጋፍ ስታደርግ የቆየች ሲሆን ለሶርያም የ350, 000 ዩሮ ዕርዳታ ማድረጓ ታውቋል። በቫቲካን የር. ሊ. ጳ በጎ አድራጎት ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ ብጹዕ ካርዲናል ኮንራድ ክራዬቭስኪ፣ ቫቲካን የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ ዕርዳታዎችዋን ችግር ላይ ለሚገኙት ሕዝቦች እንድታቀርብ በመቻሏ ለእግዚአብሔርን አመስግነው፣ ተመሳሳይ ዕርዳታን ለአገሮች በቅርቡ ማቅረብ እንደምትጀምር አስታውቀዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ቫቲካን ቅዳሜ ግንቦት 21/2013 ዓ. ም ሁለተኛ ዙር የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ ክትባትን በቫቲካን ውስጥ በሚገኝ የቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ወስጥ ለተገኙት 300 ሰዎች መስጠት መጀመሯን አስታውቃለች። ይህ ሁለተኛ ዙር የክትባት መርሃ ግብር የሚካሄደው ከዚህ በፊት አንደኛ ዙር ክትባትን በቫቲካን ተገኝተው ለተቀበሉት አቅመ ደካማ ቤተሰቦች መሆኑን በቫቲካን የር. ሊ. ጳ በጎ አድራጎት ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት አስታውቋል። ቫቲካን እስካሁን የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ ክትባትን የሰጠቻቸው ተረጅዎች ቁጥር ወደ 1,800 መድረሱን የበጎ አድራጎት ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ገልጾ ይህም የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ዕቅድ መሆኑን ገልጿል። የበጎ አድራጎት ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ኮንራድ ክራዬቭስኪ፣ የመከላከያ ክትባቱ የተሰጣቸው ቤተሰቦች የጎዳና ተዳዳሪዎች፣ በሮም ከተማ ውስጥ በተለያዩ መጠለያዎች የሚገኙ ተረጂዎች እና በጣሊያን ውስጥ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ ክትባትን የማግኘት መብት የሌላቸው ሰዎች መሆኑን ገልጸው፣ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ላደረጉት በጎ ተግባር ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል። አቅመ ደካማ ለሆኑ ድሃ ቤተሰቦች ሲሰጥ የቆየውን የመጨረሻ ዙር የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ ክትባት ከተጠናቀቀ በኋላ የክትባት መድኃኒቱ ወደ ገበያ በሚቀርብበት ጊዜ የስርጭት አገልግሎት በአዲስ መልክ የሚጀምር መሆኑን በቫቲካን የር. ሊ. ጳ በጎ አድራጎት ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ ብጹዕ ካርዲናል ኮንራድ አስታውቀዋል።

ቫቲካን ለሶርያ የ350, 000 ዩሮ ዕርዳታ አድርጋለች

ብጹዕ ካርዲናል ኮንራድ በማከልም ማዳጋስካር፣ ቬነዙዌላ፣ ኤኳዶር እና ሕንድ ከቫቲካን የገንዘብ ዕርዳታን ካገኙት አገሮች መካከል መሆናቸውን ገልጸው፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ መድኃኒትን ለጊዜ በግዢ መልክ ማግኘት የማይቻል ቢሆንም በአፍሪካ ውስጥ የሚገኙ የቅድስት መንበር እንደራሴ ጽሕፈት ቤቶች መድኃኒቱን ገዝተው ማቅረብ የሚችሉ መሆኑን አስረድተው፣ በሶርያ ውስጥ ለሚገኙ ችግረኞች የወረርሽኙ መከላከያ መድኃኒቱ በግዢ እንዲቀርብላቸው በማለት የር. ሊ. ጳ በጎ አድራጎት ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት 350, 000 ዩሮ ዕርዳታ ማድረጉን ብጹዕ ካርዲናል ኮንራድ አስረድተዋል። የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በዓለማችን ውስጥ መሰራጨት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ለሃብታም አገሮች ባቀረቡት መልዕክት፣ የመከላከያ ክትባቱ በአገሮች እና ሕዝቦች መካከል ልዩነትን ሳያሳይ ለሁሉም ተደራሽ እንዲሆን በማለት ማሳሰባቸውን ብጹዕ ካርዲናል ኮንራድ አስታውሰዋል።     

31 May 2021, 15:38