ፈልግ

የእስራኤል እና የሐማስ ግጭት የእስራኤል እና የሐማስ ግጭት 

ካርዲናል ፓሮሊን፣ እስራኤል እና ሐማስ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲያደረጉ አሳሰቡ

የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን፣ በእስራኤል እና በሐማስ መካከል የተቀሰቀሰው ግጭት በር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ እና በቅድስት መንበር ላይ ያስከተለውን ስጋት ገልጸው ባስተላለፉት መልዕክት፣ ግጭቱ ከፍተኛ የሰው ሕይወት እልቂት እና የንብረት መውደም የታየበት መሆኑን ገልጸው ሁለቱም ወገኖች ወደ መረጋጋት የሚያደርሳቸውን የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ እንዲደሩ ጠይቀው፣ የአውሮፓ ምክር ቤት ፕሬዚደንት የሆኑት ወ/ሮ ኡርሱላ ቮን ዴር ሊን ሁለቱን ወገኖች እንዲያነጋግሩ መልዕክት የሚልኩ መሆኑን ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በቅድስት አገር በእስራኤል እና ሐማስ መካከል የተቀሰቀሰው አመጽ የተሞላበት ግጭት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን እና ቅድስት መንበር እጅጉን እንዳሳሰባቸው ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን ገለጸዋል። የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን ይህን ያስታወቁት ሎዜርቫቶሬ ሮማኖ የተሰኘ የቅድስት መንበር ጋዜጣ የቀድሞ ዳይሬክተር የሆኑት የአቶ ማርዮ አኜስ መጽሐፍ ምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ መሆኑ ታውቋል። ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን በማሳሰቢያቸው እንደ ገለጹት የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በማቅረብ ላይ የሚገኘውን የተኩስ አቁም ጥሪ ሁለቱም ወገኖች ተቀብለውት በአካባቢው መረጋጋትን እንዲያመጡ ጠይቀዋል።

ግጭትን ለማስወገድ ማንኛውንም ዋጋ መክፈል ያስፈልጋል

የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን እስራኤል እና ሐማስ አስቸኳይ የተኩስ አቁም እንዲያደርጉ ባቀረቡት ጥሪ እንዳስታወቁት በሁለቱ ወገኖች መካከል የተቀሰቀሰው ግጭት ለበርካታ የሰው ሕይወት መጥፋት እና ለንብረት መውደም ምክንያት መሆኑን ገልጸው፣ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ እሑድ ግንቦት 8/2013 ዓ. ም. በቫቲካን በሚገኘው ቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለጸሎት ለተሰበሰቡት ምዕመናን ባስተላለፉት መልዕክት በግጭቱ ወቅት በርካታ ሕጻናት ለሞት የሚዳረጉ መሆናቸውን ለዓለም ማኅበረሰብ ማሳወቃቸውን አስታውሰው፣ የቅድስት መንበር ትልቁ ጥረት ሁለቱ ወገኖች የተኩስ አቁም ስምምነትን እንዲያደርጉ የምትችለውን ጥረት ማድረግ እንደሆነ ገልጸዋል።

መፍትሄው የሁለት መንግሥታት ምስረታ ነው

ቅድስት መንበር ሁለቱን ወገኖች ለማስታረቅ የምትጋበዝ ከሆነ ጣልቃ መግባት አይሁን እንጂ፣ ምንልባትም አንዳንድ ቴክኒካዊ ነገሮች ላይ ሳይሆን የእርቅ ሃሳቦችን በማቅረብ ላይ የሚያግዳት ነገር አለመኖሩን ገልጸው ከሁሉም አስቀድሞ ሁለቱ ወገኖች የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲያደርጉ እና ወደ እርቅ እንዲደርሱ ማገዝ ይቻላል ብለው ወደዚህ ደረጃ መድረስ የሚቻለው እስራኤል እና ፍልስጤም ሁለት አገሮ እና ሁለት መንግሥታት የሚለውን የመፍትሄ ሃሳብ በጸጋ እንዲቀበሉ ማድረግ ነው ብለዋል።                

  ከወ/ሮ ኡርሱላ ቮን ዴር ሊን ጋር የተደረገ ግንኙነት

የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን መጭው ቅዳሜ ግንቦት 14/2013 ዓ. ም. ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከአውሮፓው ምክር ቤት ፕሬዚደንት ከወ/ሮ ኡርሱላ ቮን ዴር ሊን ጋር የሚገናኙ መሆኑን ገልጸው፣ በዚህ አጋጣሚ እርሳቸውም እንደሚያገኟቸው እና ዕለቱ በሁለቱ ወገኖች ማለትም በእስራኤል እና በሐማስ መካከል ስለ ተከሰተው ግጭት የሚነጋገሩበት አዲስ አጋጣሚ እንደሚሆን አስረድተው፣ ሁለቱ ወገኖች ተቀራርበው በመካከል የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደርጉ ጥረት የሚደረግበት መሆኑን አስታውቀዋል። 

19 May 2021, 16:48