የክርስትና እና የቡዳ እምነት ተከታዮች ለሰብዓዊ አገልግሎት መተባበራቸው ተገለጸ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
“የቡዳ እምነት ተከታዮች እና የክርስትና እምነት ተከታዮች የአንድነት ባሕልን በጋራ እናሳድግ” በሚል ርዕሥ ዓመታዊ የቡዳ ልደት በዓላቸውን ለሚያከብሩት የእምነቱ ተከታዮች መልካም ምኞታቸውን የገለጹት በጳጳሳዊ ምክር ቤት የሐይማኖት ተቋማት የጋራ ውይይት ጠቅላይ አስተባባሪ ብጹዕ ካርዲናል ሚገል አንገል ኣዩሶ እና የምክር ቤቱ ዋና ጸሐፊ ብጹዕ አቡነ ኮዲቱዋኩ ኢንዱኒል መሆናቸው ታውቋል።
ሰብዓዊ አገልግሎትን ለማቅረብ የቀረበ የጋራ ጥሪ
የመልካም ምኞት መግለጫ መልዕክቱ በመግቢያው፣ ዓመታዊ የልደት በዓሉ ለእምነቱ መሥራች ለሆነው ለጋውታማ ቡዳ የተገለጠውን የደስታ፣ የሰላም እና የተስፋ መልዕክትን በመላው ዓለም በሚገኙ የእምነቱ ተከታዮች ልብ የሚያሳድር መሆኑን ገልጾ፣ በዚህ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ወቅትም በዓለማችን የሚገኙ የሁሉም ሐይማኖቶች ተከታዮች በመተጋገዝ ሰብዓዊ አገልግሎቶችን ለማቅረብ መተባበር እንደሚያስፈልግ አስታውቋል። የጳጳሳዊ ምክር ቤቱ መልዕክት በተጨማሪም ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ከዚህ በፊት መልዕክታቸው “የመላው ዓለም ማኅበረሰብ የደረሰበትን አደጋ እና ችግር በጋራ ለማሸነፍ አንድነቱን ማጠንከር ይኖርበታል” ማለታቸውን አስታውሷል። በጋራ እሴቶቻችን ላይ በመመስረት ትብብርን ማሳደግ እንደሚገባ የገለጸው መልዕክቱ “ሐይማኖቶቻችን የሚያተምሩንን የአንድነት እና የመረዳዳት ባሕልን ከልብ እንድንረዳ ተጠርተናል” ብሏል። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ እ. አ. አ ዘንድሮ 2021 ዓ. ም ባስተላለፉት ዓለም አቀፍ የሰላም ቀን መልዕክታቸው “በመጽሐፍ ቅዱስ ወስጥ እንደተገለጸው በሰዎች አንድነት እና ለሕይወት በሚሰጠው እውነተኛ እንክባካቤ መካከል ግንኙነት መኖሩ በዘመናችን በገሃድ እየታየ መሆኑን ገልጸው፣ ይህ ግንኙነት ፍሬያማ የሚሆነው ወንድማማችነትን፣ ፍትህን እና መተማመንን በመካከላችን ስናሳድግ ነው” ማለታቸው ይታወሳል።
አንድነትን በተመለከተ የቡዳ አስተምህሮ
የጳጳሳዊ ምክር ቤት፣ የሐይማኖት ተቋማት የጋራ ውይይት አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት መልዕክት፣ የቡዳ አስተምህሮ አንድነትን የተመለከቱ አራት በጎነቶች መኖራቸውን ገልጾ፣ እነዚህ ስለ አንድነት እና ስለ እንክብካቤ የሚናገሩ ቋሚ መልዕክቶች መሆናቸውን፣ የቡዳ አምነት ተከታዮችም ከሌሎች ጋር ያላቸውን ፍቅር ከጊዜ ወደ ጊዜ ማሳደግ እንዳለባቸው የሚያስተምር መሆኑን የሐይማኖት ተቋማት የጋራ ውይይት አስተባባሪ ጽሕፈት ቤቱ መልዕክት አስረድቷል። መልዕክቱ የቡዳ እምነት አስተምህሮን በመጥቀስ “እናት ለልጇ ስትል የሕይወት መስዋዕትነት ጭምር እንደምትከፍል፣ ለሌሎች የምንገልጸው ደግነት እና ፍቅር ማንኛውንም ጥረት በማድረግ ከጊዜ ወደ ጊዜ ማደግ ይኖርበታል” የሚል መሆኑ አስታውሷል። የሐይማኖት ተቋማት የጋራ ውይይት አስተባባሪ ጽሕፈት ቤቱ መልዕክት በማከልም ሐኪም የሕሙማንን ሕይወት ከሞት ለማትረፍ ጊዜን ሳያባክን እንደሚጥር ገልጾ፣ በማከልም “መልካምን ከመሥራት የዘገዩ በክፉ ነገር ደስ ይላቸዋል፤ ምክንያቱም መልካም ሥራቸውን በፍጥነት የማይፈጽሙ ከሆነ የክፉ ሥራ ተባባሪዎች ይሆናሉ” የሚል የቡዳ እምነት አስተምህሮ መኖሩን አስታውሷል። በጳጳሳዊ ምክር ቤት፣ የሐይማኖት ተቋማት የጋራ ውይይት አስተባባሪ ጽሕፈት ቤቱ መልዕቱን ሲያጠቃልል፣ ዛሬ የምንገኝበት ከባድ ወቅት የእርስ በእርስ መረዳዳትን፣ በክርስትና እና በቡዳ እምነቶች መካከል ያለውን ወዳጅነትን በማጠንከር፣ ለሰው ልጅ የሚገባውን አገልግሎት ለማቅረብ፣ ሁለቱም ሐይማኖቶች የሚያተምሩትን የአንድነት እና የመረዳዳት አስተምህሮን ተግባራዊ ለማድረግ፣ የጋራ ውይይት ባሕልን ማሳደግ እንደሚያስፈልግ አሳስቧል።