ፈልግ

በቻይና ውስጥ ምዕመናን በጸሎት ላይ ሆነው በቻይና ውስጥ ምዕመናን በጸሎት ላይ ሆነው  

ርዕሳነ ሊቃነ ጳጳሳት በቻይና ለምትገኝ ቤተክርስቲያን ልዩ ፍቅር ያላቸው መሆኑ ተገለጸ

የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን አዲስ በታተመው እና “ከቻይና ጋር የሚያገናኝ ድልድይ” በሚል አርዕስት ለተጻፈው መጽሐፍ መግቢያ እንዲሆን ባቀረቡት ጽሑፋቸው፣ ርዕሳነ ሊቃነ ጳጳሳት በቻይና ለምትገኝ ቤተክርስቲያን ልዩ ፍቅር ያላቸው መሆኑ ገለጹ። የቅድስት መንበር ሐዋርያዊ ልኡካን እ. አ. አ ከ1919-1939 ዓ. ም ድረስ ከሕዝባዊት ቻይና ጋር የነበራቸው ግንኙነት ሁለቱ ወገኖች ይበልጥ እንዲቀራረቡ እና በቻይና የሚገኝ ካቶሊካዊ ማሕበረሰብም ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጋር ያለው ግንኙነት ወደ መልካም ደረጃ የደረሰበት መሆኑን እና ለዚህም በወቅቱ የቅድስት መንበር ተወካይ የነበሩት ብጹዕ ካርዲናል ቼልሶ ኮስታንቲኒ ባደረጉት ከፍተኛ ጥረት መሆኑን ካርዲናል ፔትሮ ፕሮሊን አስታውሰዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን በጽሑፋቸው ርዕሳነ ሊቃነ ጳጳሳት በሙሉ በቻይና ለምትገኝ ቤተክርስቲያን እና ለመላው የቻይና ሕዝብ ልዩ ፍቅር ያላቸው መሆኑ አስታውቀዋል። የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮስ 12ኛ እ. አ. አ በ1952 ዓ. ም ለቻይና ሕዝብ በጻፉት መልዕክታቸው፣ የቻይና ሕዝብ በታሪኩ አስቸጋሪ ወቅት የተባለለትን ወቅት ባሳለፈባቸው ዓመታት ከጎኑ በመሆን ፍቅራቸውን የገለጹ መሆኑን ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን አስረድተዋል። ወቅቱ በርካታ ብጹዓን ጳጳሳት፣ ካህናት እና ምዕመናን በወንጌል  አገልግሎት የተሰማሩበት ቢሆንም አገልግሎታቸው እንቅፋት የበዛበት፣ ከወንጌል አገልግሎት እንዲርቁ የተደረጉበት ወቅት መሆኑን ካርዲናል ፓሮሊን አስታውሰዋል። በወቅቱ የነበሩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮስ 12ኛ ከቻይና ሕዝብ ጎን መቆማቸውን የገለጹት ካርዲናል ፓሮሊን ቅዱስነታቸው ለቻይና ሕዝብ የላኩትን መልዕክት ሲያስታውሱ “ልባችን እንደገና ወደ እናንተ በመመለስ በተለይም ይህንን ደብዳቤ ለመላው የቻይና ሕዝብ ስንልክ፣ ችግሮቻችሁን እና ጭንቀቶቻችሁን በሚገባ አውቀን በአባትነት መንፈስ ለማፅናናት እና ለመምከር እንመኛለን” ማለታቸውንም አስታወሰዋል። ይህን የመሰለ ሃሳብ ከቅዱስ ጴጥሮስ ተተኪ ከሆኑት ርዕሳነ ሊቃነ ጳጳሳት ልብ ውስጥ መፍለቁ እውነተኛ የአባትነት ስሜት እና አጋርነት የተገለጸበት በመሆኑ ከቻይና ሕዝባዊት ሪፓብሊክ ጋር ለሚደረግ ውሳኔ ወንድማዊነትን እና ቸርነትን የሚያጎለብት መሆኑን የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን ገልጸዋል።

ቅድስት መንበር ይህ የፍቅር ስሜት ቅዱስ ወንጌልን መሠረት ያደረገ መሆኑን በመገንዘብ ፣ ከቻይና ጋር ያላትን ግንኙነት የሚያሳድጉ አዳዲስ ሃሳቦችን በማፍለቅ እ. አ. አ በ1919 ዓ. ም ይፋ የሆነውን የሐዋርያዊ መልዕክት እቅዶችን በማስታወስ የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክቶስ 15ኛ ተግባራዊ ማድረጋቸውን አስታውሰዋል። ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን አክለውም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክቶስ 15ኛ በመላው ዓለም በተለይም በሚወዷት በቻይና ምድር የወንጌል አገልግሎትን ለማሳደግ ከፍተኛ ጥረት ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክቶስ 15ኛ ቀጥለው ሐዋርያዊ የቤተክርስቲያን መሪነትን የተረከቡት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮስ 11ኛ አስቀድሞ የተዘረጉ እቅዶችን ወደ ፊት በማራመድ የቻይናን ሕዝብ የበለጠ ለመርዳት እና ፍቅርንም ለመግለጽ የሚያስችሉ መንገዶችን መፈለጋቸው ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን አስታውሰዋል። ዕቅዶችን ተግባራዊ ለማድረግ በሁለቱ ወገኖች ማለትም በቅድስት መንበር እና በቻይና ሕዝባዊት ሪፓብሊክ መካከል መልካም ግንኙነትን መፍጠር አስፈላጊ መሆኑን በመገንዘብ ቅድስት መንበር ወደ ቻይና ሐዋርያዊ ልኡካንን መላኳን ገልጸዋል። ይህ ሐዋርያዊ ልኡክ በቻይና ውስጥ የሚፈጽመውን ሐዋርያዊ ተልዕኮ ይሳካለት ዘንድ አስቀድሞ ይፋ በተደረገው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሐዋርያዊ መልዕክት መመራት እጅግ አስፈላጊ እንደነበር ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን አስረድተዋል። ቅድስት መንበር በቻይና ያላትን ተጠርነት ለማጠናከር ብጹዕ አቡነ ቼልሶ ኮስታንቲኒ መሰየማቸውን ካርዲኦናል ፔትሮ ፓሮሊን አስታውሰው፣ አስቀድመው የተቀመጡ ውጥኖችን ተግባራዊ ለማድረግ እና ፍሬያማ ሐዋርያዊ ተልዕኮን ለመፈጸም ጠንካራ እና ደፋር አገልጋይ ማስፈለጉን ገልጸዋል። ቅድስት መንበር ከቻይና ሕዝባዊት ሪፓብሊክ እና ከሌሎች የውጭ አገር መንግሥታት ጋር ያላትን ግንኙነት ለማሳደግ ጥረቶችን የምታደኣርግ መሆኑን የገለጹት ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን፣ ከዚህ በፊትም የነበሩ ርዕሳነ ሊቃነ ጳጳሳት ከጳጳሳዊ ምክር ቤቶች ጋር በመተባበር በጊዜው የተነሱለትን ዓላማን ማሳካት መቻላቸውን አስረድተዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ለእያንዳንዱ አገር መንግሥታት እና ተወካዮቻቸው ልዩ ፍቅር እንዳላቸው አስረድተው፣ በተለይም ጠንካራ እና ብርቱ ሠራተኛ ለሆነው ታላቁ የቻይና ሕዝብ ልዩ ፍቅር ያላቸው መሆኑን አስረድተው፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ምንም እንኳን መንፈሳዊ አባት በመሆናቸው ተጠሪነታቸው ለክርስቲያን ማኅበረሰብ ቢሆኑም ፍቅራቸው እና ወዳጅነታቸው ድንበር ሳይገድበው በየትኛውም የዓለማችን ክፍል ለሚገኝ የሰው ልጅ መሆኑን ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን አስረተዋል። የቅድስት መንበር ሐዋርያዊ መልዕክተኞችም ይህንኑን መንፈስ በተግባር ሲገልጹ መቆየታቸውን የገለጹት የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን፣ ወደ ቻይና የተላኩት የቅድስት መንበር ሐዋርያዊ ልኡካን በሁለቱ ወገኖች መካከል ያለውን ግንኙነት ተመሳሳይ መንፈስን በመከተል ሲያጠናክሩ መቆየታቸውን አስረድተዋል።

ምንም እንኳን ዘመናችንም በርካታ እንቅፋቶች ቢኖሩም በሁለቱ ወገኖች ማለትም በቻይና ሕዝባዊት ሪፓብሊክ እና በቅድስት መንበር መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር ዘላቂ እና ገንቢ የጋራ ውይይቶች ሊኖሩ እንደሚገባ ገልጸው፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመልዕክታቸው በቻይና ውስጥ የምትገኝ ቤተክርስቲያን የሚያጋጥማትን መጠነ ሰፊ ችግሮችን ተቋቁማ ለመዝለቅ የሚያስችላትን እውነተኛ የእርቅ መንገድን መከተል እንደሚገባ ማሳሰባቸውን ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን አስረድተዋል።                 

15 May 2021, 16:15