ፈልግ

በሞዛምቢክ፣ በሴቶች ላይ የሚደርስ ጥቃትን ለመከላከል ታልሞ የተደረገ ስብሰባ በሞዛምቢክ፣ በሴቶች ላይ የሚደርስ ጥቃትን ለመከላከል ታልሞ የተደረገ ስብሰባ 

ያለ ሴቶች ድምጽ እና ልምድ ልማትን ማምጣት የማይቻል መሆኑ ተገለጸ

በቅድስት መንበር የመንግሥታት ግንኙነት ጽሕፈት ቤት ምክትል ዋና ጸሐፊ የሆኑት ወ/ሮ ፍራንችስካ ዲ ጆቫኒ፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በሴቶች ሚና ላይ በተወያየው 65ኛ የምክር ቤት ስብሰባ ላይ ባደረጉት ንግርር፣ ያለ ሴቶች ድምጽ እና ልምድ ልማትን ማምጣት የማይቻል መሆኑን ገልጸዋል። አክለውም በሴቶች ላይ የሚፈጸመውን ዓመፅ ለመግታት እና እኩል ክብርን ለመስጠት የበለጠ መሥራት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት 65ኛ የምክር ቤት ስብሰባ፣ በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን መዋጋት፣ የሴቶችን ማኅበራዊ ተሳትፎ ማሳደግ እና ለሴቶች የትምህርት ዕድልን መስጠት የሚሉት ርዕሠ ጉዳዮች፣ ሴቶች በማኅበራዊ ሕይወት ውስጥ የሚጫወቱትን ሚና የበለጠ ለማሳደግ የሚያግዙ መሆኑን ቅድስት መንበር እንደምታምን በቅድስት መንበር የመንግሥታት ግንኙነት ጽሕፈት ቤት ምክትል ዋና ጸሐፊ የሆኑት ወ/ሮ ፍራንችስካ ዲ ጆቫኒ ገልጸዋል።

በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት የቤት ውስጥ ጥቃቶች ጨምረዋል

በሴቶች ላይ ያለ ማያቋርጥ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣውን ጥቃት ለማስወገድ ከምን ጊዜም በበለጠ ጠንክሮ መሥራት እንደሚገባ 65 ኛው የተባበሩት መንግሥታት ጉባኤ አሳስቧል። የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመግታት ተብሎ በወጣው ደንብ መሠረት ቤተሰብ ብዙ ጊዜያቸውን በቤታቸው በሚያሳልፉበት ባሁኑ ወቅት በሴቶች ላይ የሚፈጸም የቤት ውስጥ ጥቃት በማደጉ ምክንያት የዕርዳታ ጥያቄዎች መበራከታቸው ታውቋል። በተጨማሪ በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ሴቶች በሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀል ሰለባ በመሆን ጥቃት እንደሚደርስባቸው፣ እንደሚደፈሩ፣ የጉልበት ብዝበዛ እንደሚደርስባቸው፣ አልፎ ተርፎም ፅንስን ለማስወረድ እንደሚገደዱ እና ሰብዓዊ ክብራቸውን የሚቀንሱ ተግባራትን እንዲፈጽሙ መደረጋቸው ታውቋል። በሴቶች ላይ የሚደርስ ችግር ለማስወገድ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በሺህዎች የሚቆጠሩ ማኅበራዊ ተቋማትን መስርታ ሴቶችን በማኅበራዊ ሕይወት መልሶ ለማቋቋም፣ ማኅበራዊ ስነ-ልቦናቸውን ለማሳደግ የሕክምና፣ የገንዘብ እና የሕግ ድጋፍ እየሰጠች መሆኗን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ገልጾ፣ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት ሴቶች ከማኅበረሰብ ተገልለው ለችግር እንዳይጋለጡ ተጨማሪ ድጋፍ እና ጥበቃን የሚሰጡ ማኅበራዊ ማዕከላት መቋቋም ያስፈልጋል በማለት አሳስቧል።

ሴቶችን በውሳኔ ሰጭነት ማሳተፍ

ቅድስት መንበር የሴቶችን ማኅበራዊ ተሳትፎ አስፈላጊነት እና አንገብጋቢነት ተገንዝባ ባቀረበችው አስተያየት፣ ሴቶች በማኅበራዊ ሕይወት ውስጥ ለጋራ ጥቅም የሚያበረክቱትን አስተዋጽኦ ማሳደግ እንዲቻል፣ ውሳኔዎችን መስጠት በሚችሉበት አስፈላጊ ቦታ ላይ መቀመጥ እንዳለባቸው ገልጻለች። በብዙ ህብረተሰቦች ዘንድ የሴቶች እኩልነት የሚረጋግጥበት ጊዜ አሁንም ገና ሩቅ መሆኑ ሲነገር፣ በሌላ ወገን ሴቶችን በማኅበራውዊ ሕይወት ውስጥ ማካተት እና ማስተዋወቅ ማለት ሴቶችን በሁሉም ባህሪያዊ ገፅታቸው መቀበል እና ማክበር እንደሆነ፣ ልጅ የመውለድ ልዩ ችሎታዋን እና ለደካሞች ድምጽ ሆና የመቆም ምኞቷን ማረጋገጥ መሆኑን ቅድስት መንበር በአስተያየቷ አክላ ገልጻለች። ከዚህ አንፃር ህብረተሰቡ እናቶች ትምህርታቸውን እንዳይቀጥሉ የሚያደርግ ወይም ከወንድ የሥራ ባልደረቦቻቸው ጋር ሲነፃፀሩ በወሊድ ምክንያት በሥራ ገበታቸው የሚደርስባቸውን ቅጣት መታገል እንደሚያስፈልግ ቅድስት መንበር አሳስባለች።

የትምህርት ተደራሽነት እጅግ አስፈላጊ ነው

በመጨረሻም በሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት ውስጥ የሴቶች ድምጽ እና የሕይወት ልምዶች አስፈላጊ መሆናቸውን በሴቶች ሚና ላይ ውይይቱን ያካሄደው 65ኛ የተባበሩት መንግሥታት ምክር ቤት፣ ለወጣት ልጃገረዶች እና ለሴቶች የትምህርት እድልን ማመቻቸት እንሚያስፈልግ አሳስቧል። የተማሩ ሴቶች የበለጠ ዕድል እንዳላቸው የገለጹት ወ/ሮ ፍራንችስካ ዲ ጆቫኒ፣ ይህ ደግሞ በምላሹ ለወደፊት ትውልድ እንደሚጠቅም እና የተማሩ እናቶች በተሻለ ሁኔታ ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት መላክ በመቻላቸው ድህነትን እና የመገለል አዝማሚያን ማስቀረት እንደሚቻል፣ በቅድስት መንበር የመንግሥታት ግንኙነት ጽሕፈት ቤት ምክትል ዋና ጸሐፊ የሆኑት ወ/ሮ ፍራንችስካ ዲ ጆቫኒ፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በሴቶች ሚና ላይ በተወያየው 65ኛው የምክር ቤት ስብሰባ ላይ ባሰሙት ንግግር ገልጸዋል።

25 March 2021, 15:49