ፈልግ

ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር ሆነው ባሕር ዳርቻ ሲናፈሱ ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር ሆነው ባሕር ዳርቻ ሲናፈሱ  

ካርዲናል ታርክሰን፣ ያልተለመዱ በሽታዎችን ለማከም የሚያግዙ እውቀቶችን መጋራት ያስፈልጋል አሉ

በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ፒተር ኮዱዎ ታርክሰን፣ በሁሉም የዕድገት ደረጃ ላይ የሚገኙት የጤና ተቋማት፣ የጤና ሥርዓቶቻቸውን እንዲያሳድጉ ጠይቀው፣ ሕሙማንን እና የሕሙማን ቤተሰቦችን እንድታግዛቸው በማለት ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጸሎታቸውን አቅርበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ብጹዕ ካርዲናል ታርክሰን፣ የካቲት 21/2013 ዓ. ም. የተከበረውን 14ኛ ዙር ያልተለመዱ በሽታዎች ዓለም አቀፍ ቀንን ምክንያት በማድረግ ባስተላለፉት መልዕክት፣ በጤና አጠባበቅ ሃላፊነት የተጣለባቸው የፖለቲካ መሪዎች፣ ብሔራዊ እና ዓለም አቀፍ ተቋማት በመካከላቸው ያለውን ግንኙነት በማጠናከር፣ ያልተለመዱ በሽታዎችን ለማከም የሚያግዙ እውቀቶችን በመጋራት እና የጤና ሥርዓታቸው ዘላቂ እንዲሆን በማድረግ፣ ዕርዳታን የሚፈልጉ አቅመ ደካሞች ተዘንግተው ወደ ጎን ሳይባሉ፣ የሕዝቦቻቸውን የጤና ዋስትናን እንዲያረጋግጡላቸው ጠይቀዋል።

ይበልጥ ለአደጋው የተጋለጡትን መርዳት

ብጹዕ ካርዲናል ታርክሰን፣ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በላኩት መልዕክታቸው፣ ባልተለመዱ በሽታዎች የተጠቁ የማኅበረሰብ ክፍሎች ለአደጋ የተጋለጡ መሆናቸውን አስታውሰዋል። በማኅበረሰቡ መካከል ያልተለመዱ በርካታ የበሽታ ዓይነቶች መድኃኒት ያልተገኘላቸው መሆኑን አስታውሰው፣ ሕክምናቸውም ረጅም ጊዜን የሚወስድ፣ ሥር የሰደደ፣ የአካል ጉዳትን የሚያስከትል፣ ውድ የሆኑ ሕክምናን የሚጠይቁ የሕፃናት በሽታዎች መሆናቸውን በመልዕክታቸው ገልጸዋል።

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ አደጋ

በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ፒተር ኮዱዎ ታርክሰን በማከልም፣ በማኅበረሰቡ መካከል ባልተለመዱ የበሽታ ዓይነቶች የሚሰቃዩ ሰዎች በኮቪድ-19 ወረርሽኝ በሚጠቁበት ጊዜ ሕመማቸው እንደሚብስባቸው ገልጸው፣ ቤተሰቦቻቸው እና የሕክምና አገልግሎትን የሚያበረክቱ የጤና ባለሞያዎችም ለከፍተኛ ችግር የሚጋለጡ መሆናቸውን አስረድተዋል። በቂ ሕክምናን ለመስጠት ያለው አቅም ውስንነት፣ ሕክማናውን ዘግይቶ መጀመር እና ከጀመሩ በኋላ ማቋረጥ እንዲሁም ሕክምናውን ለመከታተልም ፈቃደኛ አለመሆን፣ የመድኃኒት እጥረት፣ ተገቢውን ምርመራ ማድረግ አለመቻል፣ በሥነ-ልቦና እና አካላዊ ጤንነታቸው ላይ ሥር የሰደዱ ከባድ መዘዞችን የሚያስከትል መሆኑን አስረድተዋል።

ለሁሉም እኩል እንክብካቤ ማድረግ

የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስን መልዕክት ያስታወሱት ብጹዕ ካርዲናል ታርክሰን፣ የእያንዳንዱን ሰው ሰብዓዊ ክብር የጠበቀ የሕክምና አገልግሎት ማሳደግ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸው፣ ይህ ሊረጋገጥ የሚችለው የሕክምና ዕርዳታን ለሚፈልጉት በሙሉ እኩል አገልግሎትን በማቅረብ መሆኑን አስረድተዋል። ብጹዕ ካርዲናል ታርክሰን አክለውም፣ ትክክለኛ ሰብዓዊ ማኅበረሰብን መገንባት የሚቻለው በማኅበረሰብ መካከል የሚታየውን ብቸኝነት እና መገለል በማስወገድ መሆኑን ገልጸዋል።

በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ፒተር ኮዱዎ ታርክሰን መልዕክታቸውን በደመደሙበት ወቅት እንደተናገሩት፣ በያዝነው የአብይ ጾም ወራት ምዕመናን የቸርነት ሥራዎችን እንዲያበረክቱ፣ በሚያጽናኑ ንግግሮች እግዚአብሔር ልጆቹን እንደሚወድ መመስከር ያስፈልጋል ብለው፣ ባልተለመዱ በሽታዎች የተጠቁትን፣ ቤተሰቦቻቸውን እና የእንክብካቤ አገልግሎትን ለሚያበርክቱት በሙሉ፣ የበሽተኞች ፈውስ የሆነች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ረዳታቸው እንድትሆን በማለት ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዘንድ ጸሎታቸውን አቅርበዋል።

02 March 2021, 13:17