ፈልግ

በደቡብ ኮሪያ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ ክትባት አሰጣጥ መርሃ ግብር በደቡብ ኮሪያ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ ክትባት አሰጣጥ መርሃ ግብር  

ቫቲካን ለጎዳና ላይ ተዳዳሪዎች የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ ክትባት ለመስጠት ተዘጋጅታለች

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በጎ አድራጎት ጽሕፈት ቤት በድህነት ምክንያት ከማኅበረሰቡ ለተገለሉት ሰዎች የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ ክትባት እንደምትሰጥ ያስታወቀች ሲሆን፣ መርሃ ግብሩ የሚካሄደው በመጋቢት 20/2013 ዓ. ም በሚጀምረው የአውሮፓዊያኑ የሕማማት ሳምንት መሆኑ ታውቋል። በቫቲካን ውስጥ የተዘጋጀው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ ክትባት የሚወስዱ ሰዎች ቁጥር 1,200 መሆናቸውን ቫቲካን አስታውቃለች።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በሁሉም የዓለማችን ክፍሎች የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ባለበት ባሁኑ ወቅት፣ በሰዎች መካከል ልዩነት ሳይደረግ ለሁሉም ሰው በእኩል የመከላከያ ክትባቱ እንዲደርስ በማለት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በተደጋጋሚ ለሚያቀርቡት ጥሪ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በጎ አድራጎት ጽሕፈት ቤት መልስ የሚሰጥ መሆኑን አስታውቋል። በጎ አድራጎት ጽሕፈት ቤቱ እንዳስታወቀው በሕማማት ሳምንት ውስጥ ለጎዳና ላይ ተዳዳሪዎች የሚሰጥ “Pfizer-BioNTech” የተባለ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ ክትባት፣ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስን ጨምሮ ሁሉም የቅድስት መንበር ሠራተኞች የወሰዱት የክትባት ዓይነት መሆኑ ታውቋል። ቅድስት መንበር በግዥ ወደ አገር ውስጥ ያስገባችውን የኮቪድ-19 መከላከያ መድኃኒት ስርጭት በበላይነት የሚያስተባብረው በቫቲካን የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መቆጣጠሪያ ምክር ቤት መሆኑ ታውቋል።

የኮቪድ ክትባትን ለማዳረስ የሚደረግ ልገሳ

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በጎ አድራጎት ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት በድህነት ምክንያት ለችግር ለተጋለጡ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ካለን በማካፈል ሕክምናን እንዲያገኙ ዕድል መስጠት እንደሚያስፈልግ አሳስቦ፣ ዕርዳታቸውን በአውታረ መረብ አማካይነት ማቅረብ ለሚፈልጉት “www.elemosineria.va” የሚል የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በጎ አድራጎት ጽሕፈት ቤት ድረ ገጽ መዘርጋቱን አስታውቋል።

ክትባቶቹ ለሁሉም እኩል ተደራሽነት ይኑራቸው

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ ክትባት ለሁሉም እኩል ተደራሽነት እንዲኖረው በማለት ተደጋጋሚ ጥሪ ማቅረባቸውን ያስታወሰው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በጎ አድራጎት ጽሕፈት ቤት፣ ይህ ተግባር ለጎረቤቶቻችን ሕይወት ያለንን ሃላፊነት በተግባር እንድንገልጽ የሚያግዝ ነው ብሏል። የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ ክትባት በሁሉም አካባቢ እኩል ተደራሽነት እንዲኖር በማለት የቀረቡት ጥያቄዎች በብዙ አገሮች ዘንድ ተሰሚነትን ሳያገኙ በመቅረታቸው፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ሰዎች በሙሉ እኩል መብት እንዳላቸው በማስታወስ፣ ሁሉም ሰው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ ክትባት የማግኘት አስፈላጊነትን በድጋሚ አስገንዝበዋል። ቅዱስነታቸው እ.አ.አ 2020 ዓ. ም. የተከበረውን የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የልደት መታሰቢያ በዓልን ምክንያት በማድረግ ለመንግሥታት መሪዎች፣ ለንግድ ተቋማት እና ለዓለም አቀፍ ድርጅቶች ባስተላለፉት መልዕክታቸው፣ በመላው ዓለም የገባውን ቀውስ ለመመከት የሚያስችል መፍትሄን ለማግኘት ሁሉም መተባበር እንደሚያስፈልግ ጠይቀው፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ክትባት ለሁሉም እንዲደርስ፣ ከሁሉም አስቀድሞ ከማኅበረሰቡ ለተገለሉ አቅመ ደካማ ማኅበረሰብ ማቅረብ እንደሚገባ ገልጸው “ድንበር የማያግደውን ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት ሳንገድብ "ሁላችንም በአንድ ጀልባ ላይ መሳፈራችንን መዘንጋት የለብንም” በማለት ማሳሰባቸው ይታወሳል።

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ለድሆች ያላቸው ቅርበት

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ ክትባት በተጀመረበት የጎርጎሮሳዊያኑ 2021 ዓመተ ምሕረት መጀመሪያ ላይ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ አሥራ አምስት ድሃ ሰዎች ክትባቱ እንዲወስዱ ማድረጋቸው ይታወሳል። ከእነዚህ መካከል አብዛኛዎቹ በቫቲካን በሚገኝ ቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ዙሪያ ግድግዳ ሥር ተጠግተው የሚገኙ የጎዳና ላይ ተዳዳሪዎች እንደነበሩ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በጎ አድራጎት ጽሕፈት ቤት አስታውቋል። 

27 March 2021, 18:19