ፈልግ

በባግዳድ የሺአ እስልምና እምነት ተከታዮች  በባግዳድ የሺአ እስልምና እምነት ተከታዮች  

የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ሪፖርት፣ በሐይማኖቶች መካከል ልዩነት የሚፈጥር ነው ተባለ

ቅድስት መንበር፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት፣ የሐይማኖት እና የእምነት ነጻነትን አስመልክቶ ያቀረበው አዲስ ሪፖርት በሐይማኖቶች መካከል ከፍተኛ ልዩነትን እና መከፋፈልን የሚፈጥር ነው በማለት የተሰማትን ቅሬታ ገለጸች።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ባለፈው ሳምንት በጀኔቭ ላይ “የጸረ እስልምና እምነት ጥላቻ” በማለት ያወጣው ሪፖርት፣ በዓለማች ውስጥ የሚገኙ የበርካታ እምነቶች አቋም ያላገናዘበ፣ ለጥላቻ፣ ለልዩነት እና ለስደት የሚዳርግ ነው በማለት ቅድስት መንበር ቅሬታዋን ገልጻለች።

እንደ ቅድስት መንበር ገለጻ መሠረት፣ በአንድ ሐይማኖት ላይ ብቻ ትኩርት ማድረግ ልዩነትን ከመፍጠሩ ባሻገር በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ መካከል መከፋፈልን በማስከተል፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት የሚያካሂደውን የሰው ልጅ መብት እና እንክብካቤ ጥረት ለአደጋ የሚያጋልጥ ነው ተብሏል።  ይህ የተገለጸው በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ የሆኑት ሊቀ ጳጳስ ኢቫን ዩርኮቪክ፣ የካቲት 25 /2013 ዓ. ም. በጀኔቭ ለ46ኛ ጊዜ በተካሄደው የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጉባኤ ላይ ባቀረቡት ሪፖርት መሆኑ ታውቋል።       

የሃይማኖት ነፃነት መሸርሸር

የቫቲካን እንደራሴ የሆኑት ሊቀ ጳጳስ ኢቫን ዩርኮቪክ በተባበሩት መንግሥታት ለሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ባቀረቡት ሪፖርት፣ አድልዎ፣ ማገለል፣ የአመጽ ድርጊቶች፣ በግለሰብ ሆነ በማህበረሰብ በኩል እምነትን በመግለጽ መብት ላይ ገደቦችን ማስቀመጥ ብዙውን ጊዜ ከሙስሊም ማኅበረሰብ በኩል የሚንጸባረቅ ተግባር መሆኑን ገለጸዋል። ሊቀ ጳጳስ ኢቫን በማከልም በዓለም አቀፉ ሰብአዊ መብቶች ድንጋጌ ውስጥ የተቀመጠውን የሃይማኖት ነፃነት ሁለንተናዊነት ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ ማንኛውም ዓይነት የሐይምኖት ጥላቻ፣ ማግለል እና ስደት በጽኑ መወገዝ እንዳለበት አሳስበዋል።

የሰዎችን ሕይወት “ከኮቪድ -19 ወረርሽኝ ለመጠበቅ ጥረት እየተደረገ ባለበት ሁኔታ የሃይማኖት ነፃነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሸረሸረ በመምጣቱ፣ ሕዝባዊ ባለስልጣናት የሐይማኖት እና የእምነት ነጻነትን ለማስከበር እና ከጥቃት ለመጠበቅ ጥረት ማድረግ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ሊቀ ጳጳስ ኢቫን ዩርኮቪክ ገልጸዋል።

የማኅበራዊ ምርምር ዘዴ ማነስ

እንደ ሊቀ ጳጳስ ኢቫን ዩርኮቪክ አስተያየት፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውስጥ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት በአንድ የሐይማኖት ወገን ብቻ ትኩረት በማድረግ ያቀረበው ሪፖርት፣ በማኅበራዊ ምርምር ዘዴ ላይ ከፍተኛ ለውጥን ሊያስከትል እንደሚችል ገልጸዋል። የእነዚህን ወገኖች አፍራሽ የማግለል ተግባርን አቅልሎ መመልከት እውነተኛ አደጋን ሊያስከትል እንደሚችል አስረድተዋል። የሃይማኖታዊ መመዘኛዎችን መሠረት ያደርገ እና አንድ ወገንን ለይቶ የሚያወጣ ማንኛውም የሕግ አሠራር አድልዎን ሊያስከትል የሚችል ውጤት እንደሚያመጣ ተናገረዋል።

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት፣ መሠረታዊ እና ጠቅላላ ሰብዓዊ መብቶችን፣ የሐይማኖት ወይም የእምነት ነጻነቶችን ማስጠበቅ ሲገባው በአንድ የሐይማኖት ወገን ላይ ብቻ በማትኮር ሌሎችን ወደ ጎን ማድረጉ ልዩነትን ከመፍጠሩ ባሻገር በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ መካከል መከፋፈልን በማስከተል፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት የሚያካሂደውን የሰው ልጅ መብት እንክብካቤ ጥረት ለአደጋ የሚያጋልጥ መሆኑን፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ የሆኑት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ኢቫን ዩርኮቪክ፣ የካቲት 25 /2013 ዓ. ም. በጀኔቭ ለ46ኛ ጊዜ በተካሄደው የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጉባኤ ላይ አስታውቀዋል። 

10 March 2021, 14:31