ፈልግ

በዓለም አቀፍ ሴቶች ቀን በዓል ላይ ከታዩት መካከል በዓለም አቀፍ ሴቶች ቀን በዓል ላይ ከታዩት መካከል 

ቅድስት መንበር፣ በማኅበራዊ ሚዲያ ዘርፍ የጾታ እኩልነት እንዲከበር አሳሰበች

ሴቶች በማኅበራዊ ሚዲያ ዘርፍ የሚቻወቱት ከፍተኛ ሚና እንዳለ “የማኅበራዊ ሚዲያ ነጻነት እና የጾታ እኩልነት” በሚል ርዕስ በኦስትሪያ ቬና ከተማ በተዘጋጀ ስብሰባ ላይ የተገኙት ብጹዕ አቡነ ጄነሽ አርባንቺክ ለተካፋዮቹ ባሰሙት ንግግር ገለጹ።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በዓለማች ውስጥ ዘላቂ ሰላምን እና ጸጥታን ማሳደግ የሚቻለው፣ በማኅበራዊ ሚዲያ ዘርፍ የወንዶች እና ሴቶች እኩል ተጠቃሚነት ሲረጋገጥ መሆኑን ቅድስት መንበር የምታምን መሆኑን፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና የልዩ ተቋማት ኅብረት ቋሚ ተጠሪ የሆኑት ብጹዕ አቡነ ጄነሽ አርባንቺክ ተናግረዋል። ብጹዕ አቡነ ጄነሽ አርባንቺክ ይህን የተናገሩት ማክሰኞ የካቲት 30/2013 ዓ. ም. “የማኅበራዊ ሚዲያ ነጻነት እና የጾታ እኩልነት” በሚል ርዕስ፣ በአውሮፓ ውስጥ የደህንነት እና ትብብር ድርጅት በኦስትሪያ ቬና ከተማ ባዘጋጀው ስብሰባ ላይ ተገኝተው ማሰሙት ንግግር መሆኑ ታውቋል። ስብሰባው የተካሄደው “ማርች 8” ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን ተከብሮ ካለፈ ከአንድ ቀን በኋላ መሆኑ ታውቋል።

ሚዲያ ለጋራ ጥቅም እንዲቆም

በማኅበራዊ ሚዲያ በኩል የሚቀርቡ መረጃዎች ለጋራ ጥቅም የቆሙ መሆን እንደሚገባ የቅድስት መንበር እምነት መሆኑን የገለጹት ብጹዕ አቡነ ጄነሽ አርባንቺክ፣ ምክንያቱን ሲገልጹ፣ ማኅበረሰብ በእውነት፣ በነጻነት፣ በፍትህ እና በአንድነት ላይ የተመሰረቱ መረጃዎችን የማግኘት መብት ስላለው ነው ብለዋል። ስለሆነም ማኅበራዊ ሚዲያ ሰላምን እና ጸጥታን ለማስከበር፣ በጋራ ግንዛቤ ላይ ተመስርቶ ሰብዓዊ ክብርን ለማስጠበቅ እና ለማሳደግ ለጫወተው አዎንታዊ ሚና ዋጋን በመስጠት ድጋፍ ሊደረግለት ያስፈልጋል ብለዋል።      

ማኅበራዊ ሚዲያዎች እና ጋዜጠኞች ትክክለኛ ፣ ተጨባጭ እና ሚዛናዊ መረጃዎችን ለሕዝብ በማድረስ የጋራ ጥቅምን ማስከበር አለባቸው ብጹዕ አቡነ ጄነሽ አርባንቺክ አሳስበዋል። ይህም ሕግ አውጭዎች እና ዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ በእውነት ላይ ተመስርተው ሃላፊነት ያለበትን ውሳኔ ለማድረግ ያግዛቸዋል ብለዋል። አቡነ ጄነሽ አርባንቺክ በማከልም የጋዜጠኞች ሚና አመጽ እና ጦርነት ባሉባቸው አካባቢዎች እጅግ ጠቃሚ መሆኑን ገልጸዋል። መንግሥት መረጃን መስጠት በማይችልባቸው ግጭቶች፣ ጋዜጠኞች ትክክለኛ እና አድልዎ የሌለበት ዘገባን በማቅረብ ለዓለም ግንዛቤን ማስጨበጥ ይችላሉ ብለዋው። ይህም የሰው ሕይወት በከፍተኛ ስቃይ ውስጥ በሚገኝበት ጊዜ በግልጽ ሊታይ ይችላል ብለዋል።

ሴት ጋዜጠኞች

ሴት ዘጋቢዎችን በማስመልከት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ “ሴቶች ነገሮችን በተለየ ስሜት በመመልከት የተሻለ ይገነዘባሉ” ማለታቸውን ያስታወሱት አቡነ ጄነሽ አርባንቺክ፣ ቅድስት መንበር በአውሮፓ ውስጥ የደህንነት እና ትብብር ድርጅት የጾታ እኩልነትን ለማረጋገጥ ለሚያደርገው ጥረት ድጋፍን መስጠት የምትቀጥል መሆኑን ገልጸው፣ ይህም ሴቶች በመገናኛ ብዙኃን ዘርፍ እኩል ዕድል እንዲኖራችው ማድረግ እና ሴት ጋዜጠኞችን ከማንኛውም ዓይነት ጥቃት ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት እንደሚያካትት ገልጸዋል።

የሴቶች ራዕይ እና ስሜታዊነት

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና የልዩ ተቋማት ኅብረት የቅድስት መንበር ቋሚ ተጠሪ የሆኑት ብጹዕ አቡነ ጄነሽ አርባንቺክ፣ የሴቶች እና የወንዶች እኩልነትን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት ለማሳደግ የሚወሰድ ቀዳም እርምጃ፣ ሴቶች በሁሉም ባህላዊ ፣ ማህበራዊ ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ሕይወት ውስጥ ለሚያደርጉት ተሳትፎ አስፈላጊነት እውቅና መስጠት ነው ብለው፣ የሴቶች ራዕይ እና ስሜት ብዙን ጊዜ ለተጨባጭ እውነታ መታየት ቁልፍ ሊሆን ይችላል ብለዋል። በመሆኑም በመገናኛ ብዙሃን ዘርፍ ለሴቶች እና ለወንዶች እኩል ክብርን በመስጠት ተሳትፎአቸውንም ማጎልበት ዘላቂ ሰላምን እና ጸጥታን ለማስፈን እጅግ አስፈላጊ እና ወሳኝ እርምጃ መሆኑን ብጹዕ አቡነ ጄነሽ አርባንቺክ አስረድተዋል።   

11 March 2021, 15:10