ፈልግ

በአውስትራሊያ፣ ሲድኒ ከተማ በአውስትራሊያ፣ ሲድኒ ከተማ  

በምድራችን ላይ የደረሰውን ቀውስ ለማሳሰብ መብራት እንዲጠፋ መደረጉ ተነገረ

የመሬት እንክብካቤን የሚከታተል ዓለም አቀፍ ድርጅት በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ምድራችን በከፍተኛ ስጋት ውስጥ የምትገኝ መሆኗን አስታውቋል። ድርጅቱ ምድራችን የደረሰውን አደጋ ለማሳሰብ የዓለማችን ሕዝቦች ለአንድ ሰዓት ያህል መብራት እንዲያጠፉ ማዘዙ ታውቋል። በዚህ ሥነ-ሥርዓት ላይ ቅድስት መንበርም የተካፈለች ሲሆን ከ 300 በላይ የጣሊያን ማዘጋጃ ቤቶች መሳተፋቸው ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

እ. አ. አ. ከ1961 ጀምሮ ሥራውን በማካሄድ ላይ የሚገኘው ዓለም አቀፍ የተፈጥሮ ፈንድ ይህን ሥነ-ሥርዓት በየዓመቱ በመፈጸም የሚያከብር መሆኑ ታውቋል። በቫቲካን በሚገኝ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይም ጥቂት መብራቶች ብቻ ቀርተው ሌሎች እንዲጠፉ መደረጉ ተስተውሏል።

ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ማሳያ

“Earth Hour” በመባል የሚታወቀው ዓለም እንቅስቃሴ፣ የዓለማችንን የአየር ንብረት ለውጥ ለማጉላት በመላው ዓለም የሚገኙ ሕዝቦችን፣ ተቋማት እና ኩባንያዎች በማስተባበር ለዓለም ዘላቂ የወደፊት ተስፋን ለመስጠት እና ተፅእኖውን በመጨመር የአየር ንብረት ለውጥ ተግዳሮትን ለማሸነፍ በአንድ የጋራ ዓላማ እንዲቆሙ የሚያስተባር ድርጅት መሆኑ ይታወቃል። የመጀመሪያ ተነሳሽነቱን በአውስትራሊያ፣ ሲድኒ ከተማ እ. አ. አ. በ2007 የመጀመረ ሲሆን ቀጥሎም ወደ ሁሉም የዓለማችን ክፍሎች ተሰራጭቶ የትላልቅ ከተሞች አደባባዮች እና ጎዳናዎች በጨለማ እንዲዋጡ በማድረግ ዝግጅቱን ሲያስተባብር መቆየቱ ታውቋል።

ዓለም አቀፍ ድርጅቱ ዘንድሮ ባዘጋጀው ሥነ-ሥርዓቱ ለጤንነታችን፣ ለምግብችን ፣ ለውሃችን ፣ ለንጹህ አየራችን መሠረት ለሆነው የተፈጥሮ ሃብታችን ትክክለኛ ዋጋ እንዲሰጠው፣ ሁሉም ሰው ድምጹን ከፍ አድርጎ ተፈጥሮን መጠበቅ አስፈላጊ መሆኑን መናገር ያስፈልጋል በማለት በጣልያን ውስጥ የመሬት እንክብካቤን የሚከታተል ዓለም አቀፍ ድርጅት ፕሬዝዳንት ወ/ሮ ዶናቴላ ቢያንኪ አሳስበዋል። ወ/ሮ ዶናቴላ ቢያንኪ አክለውም የብዝሃ-ህይወትን መከላከል ማለት የሰው ልጅ የወደ ፊት ሕይወትን እና የምድራችንን ጥራት መጠበቅ እንደሆነ አስረድተዋል።

31 March 2021, 08:29