ፈልግ

ገዳማዊያን እና ገዳማዊያት ‘የእግዚአብሔር ውበት መገለጫ ምስክሮች’ ናቸው! ገዳማዊያን እና ገዳማዊያት ‘የእግዚአብሔር ውበት መገለጫ ምስክሮች’ ናቸው! 

ገዳማዊያን እና ገዳማዊያት ‘የእግዚአብሔር ውበት መገለጫ ምስክሮች’ ናቸው!

“Vita consecrata” በአማርኛው “የተቀደሰ ሕይወት” በሚል አርእስት የዛሬ 25 ዓመት ገደማ ለንባብ የበቃው ሐዋርያዊ ማሳሰቢያ ይፋ የሆነበት 25ኛ አመት መታሰቢያ በተዘከረበት ወቅት ካርዲናል ጆአዎ ብራዝ ዴ አቪዝ ባስተላለፉት መልእክት እንደ ገለጹት የተቀደሰ ሕይወት የሚኖሩ ሰዎች በደስታ አገልግሎታቸው የክርስቶስን ውበት እንዲመሰክሩ ማሳሰባቸው ተገለጸ።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

በቅድስት መንበር ሥር የሚተዳደረውና የተቀደሰ ሕይወት እና በሐዋርያዊ ሕይወት ውስጥ በመሳተፍ አገልግሎት የሚሰጡ ማኅበራትን በበላይነት የሚቆጣጠረው ጽሕፈት ቤት ሐሙስ መጋቢት 16/2013 ዓ.ም ይፋ ባደርገው መልእክቱ እንደ ገለጸው በእለቱ መልአኩ ገብርኤል ማርያምን አብስሯት ወንድ ልጅ እንደ ምትወልድ በነገራት ጊዜ ማርያም “እነሆኝ እንደ ቃልህ ይሁንልኝ” ብላ አዎንታዊ ምላሽ የሰጠችበት እለት ተከብሮ ማለፉን ምክንያት በማደረግ ይፋ ባደርገው መልእክት ሕይወታቸውን ለአምላክ በልዩ መንገድ ለሰጡ ወንዶችና ሴቶች ሁሉ አስፈላጊ የሕይወት ምዕራፍ ከእግዚአብሔር ጋር በመሆን ይራመዱ ዘንድ ጥሪ አቅርበዋል።

ብፁዕ ካርዲናል ጆአዎ ብራዝ ዴ አቪዝ በመልእክታቸው አክለው እንደ ገለጹት እ.አ.አ በመጋቢት 25/1996 ዓ.ም በወቅቱ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት የነበሩት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ “ቪታ ኮንሴክራታ” በሚል አርእስት ሐዋርያዊ ማሳሰቢያ ይፋ ማደረጋቸውን ገልጸው የእዚህ ሐዋርያዊ ማሳሰቢያ 25ኛ አመት መታሰቢያ በሚከበርበት በአሁኑ ወቅት መንፈሳዊ ጥሪን መንከባከብ እንደ ሚገባ የገለጹ ሲሆን ለአምላክ አገልግሎት ጥሪ ምላሽ የሰጡትን ገዳማዊያን እና ገዳማዊያትን እጅግ ከፍ አድርገው አመስግነዋል።

ዓለም በኮቪድ -19 ወረርሽኝ ምክንያት በጤና ፣ በኢኮኖሚ እና በማህበራዊ ተፅእኖዎች ውስጥ ገብታ እነዚህን ተግዳሮቶች እየተጋፈጠች ባለችበት በእዚህ ወቅት ካርዲናል ደ አቪዝ እንደ ገለጹት ገዳማዊያን እና ገዳማዊያት “በሁሉም ዘንድ የተስፋ ስሜት ተመልሶ ያንሰራራ ዘንድ በግላቸው ሰዎችን እንዲያነቁ” ጋብዘዋቸዋል።

የቤተክርስቲያን ልብ

ብፁዕ ካርዲናል ጆአዎ ብራዝ ዴ አቪዝ በተጨማሪ እንደ ገለጹት “የተቀደሰ ሕይወት የሚኖሩስ ሰዎች ሁሉ ለተልእኮዋ ወሳኝ አካል እና የቤተክርስቲያኗ እምብርት እንደሆኑ” ያረጋገጡ ሲሆን “ቪታ ኮንሴክራታ” የተሰኘው ሐዋርያዊ ማሳሰቢያ ከፍተኛ ጥርጣሬ እና “አገልግሎትን የመወጣት ድክመት” በሚታይበት ወቅት ይህንን መንፈስ ለመለወጥ ታስቦ ይፋ የሆነ ሐዋርያዊ ማሳሰቢያ እንደ ነበረ የገለጹ ሲሆን ሰነዱ ገዳማዊያን እና ገዳማዊያት “የክርስቶስ ፊት መገለጫ ምልክት” በማለት አስገራሚ ጽኑ ፍቺ እንደሰጠ ተናግረዋል።

ብፁዕ ካርዲናል ጆአዎ ብራዝ ዴ አቪዝ አክለው እንደ ገለጹት ገዳማዊያን እና ገዳማዊያት “የአብ ክብር እና የፊት ገጽታ በሚያንጸባርቀው የመንፈስ ግርማ” ይገልጣሉ በማለት የተናገሩ ሲሆን ስለሆነም “በእዚህ በሚያንፀባርቅ ውበት ላይ በማሰላሰል እና አስጨናቂ በሆነ ድህነት በማገልገል” እነዚህን በማጣመር መለኮታዊውን እና ሰብዓዊውን ፍጡር በዕለት ተዕለት አገልግሎታቸው ማዋሃድ አለባቸው ብለዋል።

በግንኙነት ውስጥ መኖር

ብፁዕ ካርዲናል ጆአዎ ብራዝ ዴ አቪዝ በገዳማዊያን እና ገዳማዊያት ሰዎች ሕይወት ውስጥ ስለ “ግንኙነት” ማዕከላዊነት በማንፀባረቅ መልእክታቸውን የቀጠሉ ሲሆን በቅድስት በሥላሴ ኅብረት ውስጥ እና በመካከላቸው የተፈጠረው ግንኙነት “የጋራ ቅድስናን ለመፈለግ ይመራቸዋል” ብለዋል። ገዳማዊያን እና ገዳማዊያት ፍጹም የሆኑ ሰዎች አይደሉም፣ ነገር ግን  በየቀኑ ካላቸው የሚያካፍሉ እና አንዳቸው ለሌላው ምህረትን እና ማስተዋልን የሚያቀርቡ ምስኪን ኃጢአተኞች ” ናቸው ብለዋል።

“ዛሬ የገዳም ሕይወት ከቀድሞዎቹ ጊዜያት ይልቅ‘ ምስኪን ’መሆኑን ይረዳል፣ ነገር ግን በሕይወት - በጸጋ - ከቤተ ክርስቲያን እና ከዓለም ጋር ፣ ከሚያምኑ እና ከማያምኑ ፣ ከሚሰቃዩ እና ብቻቸውን ከሚኖሩ ሰዎች ጋር አብሮ ለመጓዝ ይፈልጋል” ብለዋል።

የወልድ ስሜቶች

ብፁዕ ካርዲናል ጆአዎ ብራዝ ዴ አቪዝ የዛሬ 25 ዓመት ገደማ ይፋ የሆነውንና “ቪታ ኮንሴክራታ” የተሰኘው ሐዋርያዊ ማሳሰቢያ የተቀደሰ ሕይወት የሚኖሩ ወንዶችና ሴቶች የሕነጻ ትምሕርት አሰጣጥ ሂደት ላይ “አዲስ ንጥረ ነገር” እንዳስተዋሉ ገልጸዋል። ሃይማኖታዊ የሕነጻ ትምህርቶች ግለሰቡ “እንደ ታዛዥ ልጅ ፣ የሚሰቃይ አገልጋይ፣ ንፁህ በግ ዓይነት በሚመስል መልኩ ተመሳሳይ ስሜት እንዲሰማው” ለመርዳት እንደሆነ ገልጸዋል።

ስለዚህ ገዳማዊያን እና ገዳማዊያት ከኢየሱስ ጋር እንዲህ ያለውን ጥልቅ ግንኙነት እንዲያዳብሩ የተጠሩ በመሆናቸው የተነሳ “በመለኮታዊ ልብ ሰውን ይወዳሉ” ያሉ ሲሆን “እኛ ክርስቲያኖች እጅግ አፍቃሪ ስሜት ባለው አምላክ እናምናለን፣ እርሱ የተጨቆኑትን ልቅሶ ሰምቶ የመበለቲቱን ልመና ያዳምጣል ፣ እሱ ከእነርሱ እና ለእነርሱ ከሰው ልጆች ጋር አብሮ ይሰቃያል” ያሉ ሲሆን “የተቀደሰ ሕይወት ፣ በብዙ ማራኪ ነገሮች የተሞላ እና  የዚህ ስሜታዊነት መገለጫ ነው ብለን ማመን እንፈልጋለን ” በማለት አክለው ገልጸዋል።

የውበት መንገድ

ብፁዕ ካርዲናል ጆአዎ ብራዝ ዴ አቪዝ መልእክታቸውን ሲቀጥሉ እንደ ተናገሩት ውበት ከእግዚአብሔር ባሕሪዎች ውስጥ አንዱ ነው ፣ ስለሆነም ለእርሱ የተቀደሰ አስፈላጊ አካል ነው ያሉ ሲሆን “በሚረብሽ የጭካኔ ድርጊት ውስጥ መስመጥ በሚችልበት ዓለም ውስጥ ወደ እውነት ለመድረስ ወይም ተዓማኒ እና ማራኪ ለማድረግ ብቸኛው መንገድ ላይ ለመድረስ “በውበት መንገድ” በኩል መመላለስ ያስፈልጋል ብለዋል።

ብፁዕ ካርዲናል ጆአዎ ብራዝ ዴ አቪዝ “ቪታ ኮንሴክራታ” የተሰኘው ሐዋርያዊ ማሳሰቢያ 25ኛ አመት የብር ኢዩቤልዩ በተከበረበት ወቅት ያስተላለፉትን መልእክት ያጠናቀቁት ድንግል ማርያም ሕይወታቸውን ለእግዚአብሔር የተቀደሰ እንዲሆን ያቀረቡ ሰዎችን እንድትረዳ በመማጸን እንደ ነበረ ተገልጿል።

25 March 2021, 16:40