ፈልግ

የቫቲካን ሬዲዮ ዋና ጽሕፈት ቤቱን ለማግኘት ያደረጋቸው ጉዞዎች ሲታወሱ

የቫቲካን ሬዲዮ ዛሬ የደረሰበትን የዕድገት ደርጃ ስንመለከት፣ ለዚህ እንዲበቃ ከፍተኛ አስተዋጾ ያበረከቱትን የቀድሞ ር. ሊ. ጳ ቅዱስ ጳውሎስ ስድስተኛን ማስታወስ ግድ ይለናል። ሬዲዮ ጣቢያዎች እየተበራከቱ በመጡመት ወቅት፣ ባለ ስድስት ወለል የዝግጅት ክፍሎች እንዲኖሩት ካደረጉበት ጊዜ እነሆ 50 ዓመታት ተቆጥረዋል። የቫቲካን ሬዲዮ የአገልግሎት ዓመታትን የሚያስታውስ ታሪክ ከዚህ ቀጥሎ የምንመለከት ይሆናል። የሬዲዮ ሞገድ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገኘበትን ወቅት የቴክኒክ ዘመን ብለን መጥራት እንችላለን። የሬዲዮ ሞገድን እንዳገኘ የሚነገርለት ጣሊያናዊ አዋቂ ጉሊዬልሞ ማርኮንኒ የሬዲዮ ማሰራጫ ጣቢያን በቫቲካን ውስጥ ከሚገኘው ቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ጀርባ ካቋቋመ በኋላ እ.አ.አ ጥር 12/1931 ዓ. ም. የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትን ድምጽ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ መላው ዓለም እንዲደስ ማድረጉ ይታወሳል። ይህም በቫቲካን ሬዲዮ ጣቢያ ታሪክ ትልቅ እድገት የታየበት በመሆኑ ላለፉት 90 ዓመታት ሲታወስ ቆይቷል። በተለይም የስርጭት ጣቢያው ከተመሰረተበት ዓመት እስከ ሰማንያዎቹ ያሉት ዓመታት ሦስት ዋና ዋና የእድገት ደረጃዎች የተመዘገቡባቸው ዓመታት እንደሆኑ ማሰብ እንችላለን።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ሁለቱ ተጨማሪ የዕድገት ደረጃዎች

ሁለተኛውን የቫቲካን ሬዲዮ የዕድገት ደረጃን፣ ዜናዎች በሬዲዮ አማካይነት የተሰራጩበት ዘመን፣ ወይም “የሬዲዮ ዜናዎች ዘመን” ብለን መጥራት እንችላለን። የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ድምጽ የሆነው የቫቲካን ሬዲዮ ከሬዲዮ ጣቢያነት ባሻገር የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትን መልዕክቶች በከፍተኛ ድምጽ ከማስተጋባት በተጨማሪ የማኅበራዊ መገናኛ መሣሪያ በመሆን እ. አ. አ. ወደ 1957 ዓ. ም. መጨረሻ አካባቢ ወደ መረጃ ልውውጥ ዘመን መድረሱን እናስተውላለን። እ. አ. አ. ጥር 1/1957 ዓ. ም. በሰባት የተለያዩ ቋንቋዎች የተዘጋጀ መጽሔት ለመጀመሪያ ጊዜ ሊታተም በቃ። ከአሥር ዓመታት በኋላ ወደ ሦስተኛው የዕድገት ደረጃ ላይ ለመድረስ የተቻለ ሲሆን የቫቲካን ሬዲዮ ጣቢያ ወደዚህ ደረጃ እንዲደርስ ፈር የቀደዱት፣ የጋዜጠኝነት ዝንባሌ የነበራቸው የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ጳውሎስ ስድስተኛ ነበሩ።

ሃሳብ የሚገለጽበት ዘመን

እ. አ. አ. 1966 ዓ. ም. የበጋ ወራት መጀመሪያ ላይ ር. ሊ. ጳ. ቅዱስ ጳውሎስ ስድስተኛ የቫቲካን ሬዲዮ ማሰራጫ ወደሚገኝበት ወደ ቅድስት ማርያም ማዕከልን መጎብኘታቸው ይታወሳል። በወቅቱ የቫቲካን ሬዲዩ ጣቢያ እንዲያድግ በማለት፣ በሰሜን አሜሪካ የኒውዮርክ ከተማ ጳጳስ የነበሩት ካርዲናል ፍራንሲስ ዮሴፍ ስፔልማን ሁለት የአጭር ሞገዶች ማሰራቻ መሣሪያዎችን መለገሳቸው ይታወሳል። የቀድሞ ር. ሊ. ጳ ቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ አባት በጣሊያን ውስጥ በብሬሻ ክፍለ ሀገር ውስጥ “ኢል ቺታዲኖ” የተባለ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ጋዜጣ ለረጅም ዓመታት በመሪነት የሰርሩ በመሆናቸው ቅዱስነታቸው የመረጃን አስፈላጊነት በሚገባ ያውቁ ነበር። ር. ሊ. ጳ. ቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ ከሦስት ዓመታት በኋላ “ኢንተር ሚሪፊካ” ወይም “ከአስደናቂ ነገሮች መካከል” የተባለ የብዙሃን መገናኛ ብዙሃን አዋጅ አወጁ። ቅዱስነታቸው ይህን አጋጣሚ በመጠቀም እነዚያን በስጦታ ያገኟቸውን ሁለት የአጭር ሞገዶጭ ማሰራጫ መሳሪያዎች አገልግሎት እንዲጀምሩ አድርገዋል። ቅዱስነታቸው በዕለቱ ባስተላለፉት መልዕክት “የቫቲካን ሬዲዮ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትን መልዕክት በሰፊው የሚያስተጋባ መሣሪያ ብቻ ሳይሆን ሃሳብ ለመግለጽ ችሎታ ያለው መሣሪያ መሆን አለበት” ማለታቸው ይታወሳል።

የቫቲካን ሬዲዮ የቴክኖሎጂ ውጤት ብቻ አይደለም

የቀድሞ ር. ሊ. ጳ. ቅዱስ ጳውሎስ ስድስተኛ እ. አ. አ. ሰኔ 30/1966 ዓ. ም. ያስተላለፉት የመጀመሪያ መልዕክት ለቫቲካን ሬድዮ ጣቢያ ምስረታ ትልቅ ዋጋ የሚሰጠው ነበር። ለሬዲዮ ጣቢያው አዲስ ለውጥን ለማምጣት በማሰብ ባስተላለፉት መልዕክታቸው፣ የሬዲዮ ጣቢያው ማትኮር ያለባቸውን የዝግጅት ዓይነቶችን በመጥቀስ፣ ሬዲዮ ጣቢያው የተቋቋመበትን ዋና ዓላማ፣ አገልግሎቱን እና ውጤታማ አገልግሎቱን በተግባር የሚገልጽ መሆን እንዳለበት አስታውቀዋል። ቅዱስነታቸው በዚህ መልዕክታቸው እነዚህን ከላይ የተጠቀሱትን ዓላማዎች በተግባር የሚገልጽ ካልሆነ እና አጠቃቀሙን በሚገባ የማናውቅ ከሆነ፣ እጅግ ዘመናዊ መሣሪያ ብቻ ሆኖ ይቀራል በማለት መናገራቸው ይታወሳል። ቅዱስነታቸው ይህን መልዕክት ባስተላለፉበት ወቅት ሬዲዮ ጣቢያውን ለማሳደግ ሃሳብ እንዳላቸው፣ ሰፊ የዝግጅት አስተባባሪ ጽሕፈት ቤትን ለማቋቋም፣ የተለያዩ ቋንቋዎችን በማስተባበር አብረው ለመስራት የሚያስችላቸውን ሁኔታ ለማመቻቸት ሃስብ እንደነበራቸው ያሳይ ነበር።

በቫቲካን ሬዲዮ የታዩ ከፍተኛ ለውጦች

እ. አ. አ. ከ1967 ዓ. ም. መጨረሻ ጀምሮ የቫቲካን ሬዲዮ በ32 የተለያዩ ቋንቋዎች ዝግጅቶቹን ማስተላለፍ ጀመረ። ይሁን እንጂ የሬዲዮ ዝግጅቶቹ አየር ላይ የሚውሉባቸው አካባቢዎች የተለያዩ ነበሩ። ዋና ጽሕፈት ቤቱ እና የዝግጅት ክፍሉ ከ1959 ዓ. ም. ጀምሮ ወደ ነበረበት፣ ከሰኔ ወር 1967 ዓ. ም. በጊዜያዊነት በኮንቺሊያሲዮኔ ጎዳና ወደሚገኝ ወደ ቶርሎኒያ ሕንጻ እንዲዛወር ተደረገ። ይህ ቦታ ር. ሊ. ጳ ቅዱስ ጳውሎስ ስድስተኛ አስቀድመው ለሬዲዮ ጣቢያው ዋና ጽሕፈት ቤት እንዲሆን ያቀዱት ቦታ ነበር። ሕንጻውም በአርኪቴክት አቶ ፒያቼንቲኒ እና አቶ ስፓካረሊ ንድፍ መሠረት እ. አ. አ. ከ1948-1950 ዓ. ም. ድረስ ተገንብቶ በቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮስ 12ኛ ስም የሚጠራ መሆኑ ታውቋል። ሕንጻው አስቀድሞ የተለያዩ የቫቲካን ውስጥ ሰራተኞች እና የጣሊያን ካቶሊካዊ እንቅስቃሴዎች አባላት የሚኖሩበት ሲሆን እ. አ. አ. ከ1970 ዓ. ም. ጀምሮ ነዋሪዎቹ ወደ ሌላ አካባቢዎች እንዲዛወሩ ከተደረገ በኋላ ሦስተኛ እና አራተኛ ፎቆች ለሬዲዮ ዝግጅቶች ምቹ የሆኑ የድምጽ መቅረጫ ክፍሎች እንዲዘጋጁ ተደርገዋል።

የቫቲካን ሬዲዮ ዋና ጽሕፈት ቤት በር. ሊ. ጳ ፒዮስ 11ኛ ሕንጻ ውስጥ ስለመሆኑ

ወደ ቫቲካን ሬዲዮ ዋና ጽሕፈት ቤት መግቢያ ዋና በር እንደዛሬው ሳይሆን ወደ ኮቺሊያሲዮኔ ጎዳና የዞረ ሲሆን ዋና ዋና የሬዲዮ ፕሮግራሞች የሚዘጋጁባቸው ክፍሎች እና መስመሮች በቫቲካን አትክልት ውስጥ ከተገነባው ከቀድሞ ር. ሊ. ጳጳሳት ሌዮኔ 13ኛ ሕንጻ ጋር በመገናኘት፣ በውስጡ በሚገኘው በመጀመሪያ ፎቅ ላይ በ15 የምስራቅ አውሮፓ ቋንቋዎ ፕሮግራሞች የሚዘጋጁበት እና ቤተመጽሐፍት የሚገኙበት፣ ሦስተኛው ፎቅ በፈረንሳይኛ፣ በስፔይን፣ በፖርቱጋል፣ በጀርመን እና በስካንደኔቪያን ቋንቋዎች ፕሮግራሞች የሚዘጋጁበት፣ የፕሮጋራም ማስተባበሪያ እና ዋና ጽሕፈት ቤት የሚገኝበት ሲሆን አራተኛው ፎቅ፣ ዜናዎች በጣሊያን፣ በአረብኛ፣ በቻይንኛ፣ በሁለቱ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች፥ በአማርኛ እና በትግርኛ እንዲሁም በጃፓንኛ ቋንቋ የሚተላለፉባቸው ክፍሎች የተዘጋጁ ሲሆን አምስተኛው ፎቅ የስርጭቶች መቆጣጠሪያ እና የቴክኒክ ክፍሎች ያሉበት እንደነበር ይታወሳል።

አዲስ ጅማሬ

ቀጥለው የነበሩ ሁለቱ ዓመታት የሙዚቃ እና የድምጽ መዛግብት እና የር. ሊ. ጳጳሳት ሐዋርያዊ መልዕክቶች የሚቀመጡባቸው ክፍሎች ተዘጋጅተው የቀረቡበት ሲሆን፣ እ. አ. አ. 1974 ዓ. ም. በፒያ አደባባይ የሚገኘው የር. ሊ. ጳጳሳት ፒዮስ 11ኛ ሕንጻ ዋና መግቢያ የተሰራበት ነበር። እ. አ. አ. የካቲት 5/1980 ዓ. ም. በአርባ  ቋንቋዎች የተለያዩ ፕሮግራሞች የሚተላለፍበትን ሬዲዮ ጣቢያን አንድ ሰዓት ተኩል ያህል ጊዜን በመስጠት ለመጀመሪያው ጊዜ የጎበኙት የቀድሞ ር. ሊ. ጳ ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ነበሩ። የቀድሞ ር. ሊ. ጳ ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ የቫቲካን ሬዲዮን ከጎበኙ ከአሥር ዓመታት በኋላ አዳዲስ ቢሮዎችን በውስጡ በማዘጋጀት አሁን የሚገኝበትን ዋና ጽሕፈት ቤቱን ይዞ ይገኛል።   

13 February 2021, 13:14