ቫቲካን፣ ሰራተኞቹ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ ክትባት እንዲወስዱ የማያስገድድ መሆኑን አስታወቀ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
የቫቲካን መንግሥት በግዛቱ ውስጥ በተለያዩ መሥሪያ ቤቶች ውስጥ የሚገኙ ሰራተኞች የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ ክትባትን መውሰድ በተመለከተ ሐሙስ የካቲት 11/2013 ዓ. ም. መግለጫ ማውጣቱ የሚታወስ ነው። መግለጫው በቫቲካን ግዛት ውስጥ የሚታየውን የኮቪድ-19 ወረርሽኝን መሠረት በማድረግ የጳጳሳዊ ኮሚሽን ፕሬዝዳንት የካቲት 1/2013 ዓ. ም. በቁጥር 398 ያወጣውን ድንጋጌ መሠረት ያደረገ መሆኑ ታውቋል። ድንጋጌው፣ በቫቲካን ግዛት ውስጥ የሚገኙ ሰራተኞች ፣ ዜጎች እና ነዋሪዎች ጤና እና ደህንነት ለመጠበቅ እና ዋስትና ለመስጠት ባለው ቀዳሚ ፍላጎት፣ አስቸኳይ ቁጥጥር በማድረግ ፈጣን ምላሽ ለመስጠት መሆኑን አስታውቋል። በተጨማሪም በግዛቱ ውስጥ የሚገኙ ሠራተኞች ጤናን ለመንከባከብ፣ የሥራ ቦታዎችን ደህንነት ለመጠበቅ እና ሊከሰት ለሚችለው የጤና መቃወስ ተመጣጣኝ ምላሽ በመስጠት አደጋውን ከውዲሁ ለመከላከል መሆኑ ታውቋል።
ካለመከተብ የሚከሰቱ አደጋዎችን ከግምት ውስጥ ማስገባት ያስፈልጋል
የቫቲካን መንግሥት የጤና ጥበቃ ባለስልጣን እንዳስታወቀው፣ አንዳንድ የአገልግሎት መስጫ ዘርፎች ወይም መስሪያ ቤቶች ከሕዝብ ጋር የቀረበ ግንኙነት ያላቸው በመሆኑ፣ የተስተናጋጁን እና የሰራተኛውን ጤና ለመጠበቅ ሲባል የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ ክትባትን መውሰድ አስፈላጊ መሆኑን ገልጿል። የክትባት መርሃ ግብሩን በፈቃደኝነት ማከናወን የማይፈልጉ የግዛቱ ሰራተኞችም ሆነ ነዋሪዎች በራስ ሆነ በሌሎች ሰዎች ሊያስከትል የሚችለውን አደጋ ከግምት ውስጥ ማስገባት እንዳለበት አሳስቧል። የጤና ባለስልጣኑ በማከልም፣ የህብረተሰቡን ጤና መጠበቅ ፥ የጤና ችግር ከሌለባቸው በስተቀር በጤና ላይ የሚደርሰውን አደጋ የሚቀንሱ መመሪያዎችን ተግባራዊ ማድረግ እና ሊላ አማራጭ የሥራ ዕድሎችን ለማግኘት የሚያስችሉ እርምጃዎችን መውሰድ የሚያጠቃልል መሆኑን አስረድቷል።
ዓላማው የማህበረሰብን ጤና ለመጠበቅ ነው
የቫቲካን አስተዳደር መግለጫ፣ የጤና ጉዳዮችን የሚመለከቱ ቀደም ሲል የነበሩትን ደንቦች በማስታወስ፣ የሰውን ልጅ ክብር እና መሰረታዊ መብቶቻቸውን በማክበር፣ ከቅጥር እና ከጠቅላላው የሥራ ስምሪት አንጻር በጤና ምርመራዎች ውስጥ ያሉት ደንቦች መከበራቸውን ማረጋገጥ እና ሰራተኞች በተወሰኑ ከባድ በሽታዎች ወይም በልዩ የስነ-ልቦና ሁኔታ ውስጥ የሚገኙትን ለመርዳት እ.አ.አ. ህዳር 18/2011 ዓ. ም. የወጣውን ደንብ በማክበር መሆኑን አስታውቋል። የዚህ ደንብ ዓላማ የማህበረሰቡን ጤና ለመጠበቅ የታሰበ እንጂ በማንም ላይ ቅጣት ለመጣል የታሰበ አለመሆኑን አስታውቆ፣ በማከልም የጋራ ጤናን እና የእያንዳንዱ ሰው የመምረጥ ነፃነትን በማስጠበቅ መካከል ሚዛናዊነት እና ተመጣጣኝ ምላሽ ለመስጠት የታቀደ መሆኑን አስታውቋል።