ፈልግ

በፓኪስታን አንድ እናት በእርሻ ሥራ ላይ በፓኪስታን አንድ እናት በእርሻ ሥራ ላይ 

ቅድስት መንበር፣ ለሴቶች እድገት የቆመች መሆኗን አስታወቀች

በአውሮፓ የደህንነት እና የትብብር ድርጅት ቋሚ ተወካይ የሆኑት ብጹዕ አቡነ ጃኑስ ኡርባንቺክ፣ ሴቶች በኤኮኖሚ ራሳቸውን እንዲችሉ ለማድረግ የሚደረግ ከፍተኛ ጥረት ለዓለም ደህንነት፣ መረጋጋት እና ዘላቂ እድገት እጅግ አስፈላጊ መሆኑን አስታውቀዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በቅድስት መንበር የአውሮፓ ደህንነት እና ትብብር ድርጅት ቋሚ ተወካይ የሆኑት ብጹዕ አቡነ ጃኑስ ኡርባንቺክ የአውሮፓ የደህንነት እና የትብብር ድርጅት እ.አ.አ በ2021 ዓ. ም. በሚያካሂደው ጉባኤው፣ ሴቶችን በሁሉም የኑሮ እና የሥራ መስክ ራሳቸውን እንዲችሉ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል በማለት አሳስበዋል። ብጹዕ አቡነ ጃኑስ ኡርባንቺክ፣ ሰኞ የካቲት 8/2013 ዓ. ም. በአውታረ መረብ አማካይነት በተካሄደው 29ኛው የኤኮኖሚ እና የአካባቢ ጥበቃ መድረክ ላይ ቀርበው ባሰሙት ንግግር፣ የእያንዳንዱን ሰው እውነተኛ እኩልነት መጠበቅ እና ማስተዋወቅ እንዲሁም የሴቶችንና የወንዶንች ተጓዳኝነት ቅድስት መንበር ቅድሚያ የምትሰጥባቸው ርዕሠ ጉዳዮች መሆናቸውን ገልጸዋል።

ለሴቶች የሰላምን እና ማህበራዊ ደህንነትን ጥረት ዋጋን መስጠት

በቅድስት መንበር የአውሮፓ ደህንነት እና ትብብር ድርጅት ቋሚ ተወካይ የሆኑት ብጹዕ አቡነ ጃኑስ ኡርባንቺክ ለመድረኩ ተካፋዮች ባሰሙት ንግግር፣ በሴቶች ሰብዓዊ ክብር እና በተሰማሩበት የሥራ ዘርፍ ወደ ፊት እንዳይራመዱ የሚያደርጉ በርካታ መድሎዎች እንደሚደረግባቸው አስረድተዋል። ብዙ ሴቶች የነበራቸው መብት በተሳሳተ መንገድ ሲገለጽ መመልከታቸውን እና በህብረተሰቡ መካከል ዝቅተኛ ደረጃን በመያዝ ወደ አገልጋይነት የተለወጡ መሆናቸውንም አክለው አመልክተዋል።

የቀድሞ ር. ሊ. ጳ ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ እ. አ. አ. በ1995 ዓ. ም. የሴቶችን ጉዳይ በማስመልከት በጻፉት መልዕክታቸው፣ በሁሉም መስክ የሴቶች እኩልነት እንዲረጋገጥ፣ ለእኩል ሥራ እኩል ክፍያ እንዲሰጣቸው፣ ለሰራተኛ እናቶች ጥበቃ እንዲደረግላቸው፣ ፍትሃዊ የሞያ እድገት እንዲኖራቸው ማድረግ፣  በቤተሰብ መብቶች እና ዲሞክራሲያዊ መንግስት ውስጥ የዜጎች መብት እና ግዴታ ለሚስቶች የእኩልነት ዕውቅና እንዲሰጥ ማለታቸውን ብጹዕ አቡነ ጃኑስ ኡርባንቺክ አስታውሰዋል። ከዚህም በተጨማሪ በህብረተሰቡ ውስጥ የሴቶችን ተሳትፎ ማሳደጉ ሰላምና ፀጥታ እንዲጨምር አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ እና የኅብረተሰብ መሠረታዊ የሆነው የቤተሰብ ክፍል እንዲያድግ ያደርጋል ብለዋል።

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ

ብጹዕ አቡነ ጃኑስ ኡርባንቺክ ንግግራቸውን በመቀጠል በዓለማችን እየተስፋፋ ያለው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ያስከተለው ቀውስ በሥራው ዓለም ውስጥ የሴቶችን ተሳትፎ እጅግ የጎዳው መሆኑን ገልጸው። ዝቅተኛ ደሞዝ የሚከፈላቸው ሴቶች በኮሮና ወረርሽኝ ወቅት ከሥራ የመባረር ዕድላቸው ከፍተኛ መሆኑን አስረድተው፣ በሥራ ዘርፍ በቁጥር በልጠው በሚገኙበት ቦታ ለሴቶች የሚደረግ የገንዘብ ድጋፍ ዝቅተኛ መሆኑን እና እናቶች ልጆቻቸውን እቤት ውስጥ እንዲማሩ ማድረግ ቢከፈላቸውም ባይከፈላቸውም የሥራ ጫናን ያሳደገባቸው መሆኑን ብጹዕ አቡነ ጃኑስ ኡርባንቺክ በማከል አስረድተዋል።

በሴቶች ጥረት የወንዶች እገዛ ይታከል

በሴቶች ዙሪያ የሚታዩ በርካታ ችግሮችን ያስታወሱት በቅድስት መንበር የአውሮፓ ደህንነት እና ትብብር ድርጅት ቋሚ ተወካይ የሆኑት ብጹዕ አቡነ ጃኑስ ኡርባንቺክ፣ በወንዶች እና ሴቶች መካከል መተጋገግ እንዲኖር አሳስበው፣ ሴቶችን በሁሉም የኑሮ እና የሥራ መስክ ራሳቸውን እንዲችሉ ማድረግ ሴቶችን ብቻ ሳይሆን ለዓለም ደህንነት፣ መረጋጋት እና ዘላቂ እድገት እጅግ አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል።    

20 February 2021, 12:19