ፈልግ

የቤተሰብ እንክብካቤ የቤተሰብ እንክብካቤ  

ቅድስት መንበር፣ የአውሮጳ አገራት ለሠራተኞች እኩል የሥራ ዋስትናን እንዲያረጋግጡላቸው አሳሰበች

በቅድስት መንበር የአውሮፓ ደህንነት እና ትብብር ቋሚ ተወካይ ብጹዕ አቡነ ጃኑስ ኡርባንቺክ፣ ቅድስት መንበር በቤተሰብ መካከል ሴቶች የሚያበረክቱት ተግባር ለኤኮኖሚያዊ እድገት አስፈላጊ መሆኑ እውቅና ሊሰጠው ይገባል በማለት አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

መንግሥታት የሴቶችን እና የወንዶችን እኩልነት ለማሳደግ ከሚያደርገው ጥረት በተጨማሪ በኤኮኖሚ እድገት ውስጥ ለቤተሰብ የሚሰጠውን ትኩረት በማሳደግ፣ ቤተሰብ የሕብረተሰብ መሠረት እና የነገው ኢኮኖሚያዊ ሕይወት ግንባታ ቀዳሚ ተዋናይ በመሆኑ ማበረታታት እንደሚያስፈልግ፣ ቅድስት መንበር የአውሮፓ የደህንነት እና የትብብር ድርጅትን አሳስባለች።

በአውሮፓ የደህንነት እና የትብብር ድርጅት ውስጥ የቅድስት መንበር ቋሚ ተወካይ የሆኑት ብጹዕ አቡነ ጃኑስ ኡርባንቺክ፣ ድርጅቱ ማክሰኞ የካቲት 9/2013 ዓ. ም. በአውታረ መረብ አማካይነት ባካሄደው 29ኛ የኤኮኖሚ እና የአካባቢ ጥበቃ ጉባኤ መዝጊያ ላይ ቀርበው ባሰሙት ንግግር፣ ሥራ እና ቤተሰብ ሰብዓዊ ክብርን እና ኤኮኖሚኣይዊ እድገትን በማምጣት፣ እንዲሁም ማኅበረሰብን በመለወጥ ረገድ የማይነጣጠሉ መሆናቸውን አስረድተዋል። ብጹዕ አቡነ ጃኑስ ኡርባንቺክ አክለውም ቤተሰብ ከፍተኛ ዋጋ የሚሰጠው የማኅበረሰብ ክፍል በመሆኑ ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ የሥራ ዕድል ለቤተሰብ እንዲመቻች አሳስበዋል።

የኢኮኖሚ እድገትን ማበረታታት

በአውሮፓ የደህንነት እና የትብብር ድርጅት ውስጥ የቅድስት መንበር ቋሚ ተወካይ ብጹዕ አቡነ ጃኑስ ኡርባንቺክ፣ ሴቶች ያለ ክፍያ የሚያበረክቱት ሥራ ከፍተኛ ሚና እንዳለው እውቅና ባይሰጠውም፣ ለሁሉም አገራት ኤኮኖሚያዊ እድገት ብቻ ሳይሆን እያንዳንዱን ማኅበረሰብ እና አገር በዘላቂነት ማስተዳደር መሠረታዊ ድጋፍ የሚሰጥ መሆኑን አስረድተዋል። ይህም ለሕጻናት እና ለአዛውንትን ያለ ክፍያ የሚያበረክቱት እንክብካቤ መሆኑን አስታውሰው፣ ይህ ባይሆን ኖሮ በርካታ መንግሥታት ለማኅበራዊ አገልግሎት ከፍተኛ ወጪን ሊያወጡ እንደሚችሉ አስረድተዋል። 

ብጹዕ አቡነ ጃኑስ ኡርባንቺክ በንግግራቸው ወቅት፣ ቅድስት መንበር የሴቶችን እድገት የምታበረታታ መሆኗን ገልጸው፣ እያንዳንዱ ሰው፣ ወንዶች እና ሴቶች ኢኮኖሚያዊ ተነሳሽነት የማግኘት መብት ያላቸው መሆኑን እና ችሎታቸውንም በሕጋዊ መንገድ መጠቀም መቻል አለባቸው በማለት አሳስበዋል። ብጹዕ አቡነ ጃኑስ ኡርባንቺክ በማከልም የአውሮፓ የደህንነት እና የትብብር ድርጅት ለዜጎቹ እኩል እና ፍትሃዊ የሥራ ዕድሎችን በማመቻቸት ወደ ሞያዊ ብቃት እንዲያተኩር አሳስበዋል።   

22 February 2021, 13:11