ፈልግ

ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን በካሜሩን ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን በካሜሩን ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው 

አቡነ አንድሪው፤ እምነት፣ ከሚደርስባቸው ማስፈራሪያ የሚበልጥ መሆኑን አስረዱ

የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን የሰሜን ምዕራብ አፍሪካ አገር በሆነችው ካሜሩን ከጥር 20 - 26/2013 ዓ. ም ድረስ ሐዋርያዊ ጉብኝት ማድረጋቸው ተገልጿል። በጉብኝታቸው ወቅት ከር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የተላከውን የአንድነት እና የወዳጅነት መግለጫ መልዕክትም ለካሜሩን ሕዝብ አድርሰዋል። በካሜሩን ባሜንዳ ካቴድራል በተደረገላቸው ደማቅ የአቀባበል ሥነ- ሥርዓት ላይ ንግግር ያደረጉት የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ አንድሪው እምነት፣ ከሚደርስባቸው ማስፈራሪያ እና ዛቻ የሚበልጥ መሆኑን አስረድተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን፣ በካሜሩን አለመረጋጋት ከታየበት፣ እ.አ.አ ከ2016 ዓ. ም. ወዲህ በሰሜን ምዕራብ እና ደቡብ ምዕራብ የሚገኙ የካሜሩን ሕዝቦችን የጎነኙ የመጀመሪያው የቅድስት መንበር ሐዋርያዊ ልኡክ መሆናቸውን የባሜንዳ ሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ አንድሪው ገልጸዋል። ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ አንድሪው ንኬያ ፏኛ በማከልም በሀገረ ስብከታቸው የሚኖሩ ምዕመናን የተለያዩ ማስፈራሪያዎች እና ዛቻዎች በየጊዜው ቢደርስባቸውም በአንድነት ስሜት ለሰላም አብረው ለመጸለይ የመጡ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ ተገንጣይ ቡድኖች መተላለፊያ መንገዶችን መዘጋታቸው የተለያዩ ትርጓሜዎች የተሰጡት ሲሆን፣ የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን ከሌሎች ልኡካን ጋር ጸጥ ረጭ ባለው ከተማ መካከል አቋርጠው እንዲያልፉ መፈቀዱ ለቤተክርስቲያኒቱ የተቃውሞ መልእክትን ለማስተላለፍ የተደረገ ከመሆኑ ይልቅ የከተማው ነዋሪዎች የሚገኙበትን ሁኔታ በግልጽ ለማሳየት የተደረገ ነው ተብሏል። ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ አንድሪው ንኬያ እሑድ ጥር 23/2013 ዓ. ም. የተፈጸመውን የመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት ለተካፈሉት በሺዎች ለሚቆጠሩ ምዕመናን የማበረታቻ መልዕክታቸውን ርስተላልፈዋል።

የእርቅ አምባሳደር

ለቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ለብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን ደማቅ አቀባበል ለማድረግ እና የተሰማቸውን ደስታ ለመግለጽ፣ ቅዳሜ ጥር 22/2013 ዓ. ም. ከተለያዩ የካሜሩን ግዛቶች ረጅም መንገድ ተጉዘው ወደ ማንኮን ቅዱስ ዮሴፍ ካቴድራል ድረስ በርካታ ወጣቶችን መምጣታቸው ተመልክቷል። ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ አንድሪው ንኬያም በዕለቱ ባሰሙት መልዕክታቸው፥ “በዚህ ቀውስ ወቅት እንደ ሰላም መልእክተኛ እና እንደ እርቅ አምባሳደር አድርገን ስለምንመለከታችሁ ደስተኞች ነን፤ የፍትህ አራማጅ መሆናችሁን እንመለከታለን፤ በእናንተ በኩል ቅዱስ አባታችን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በመካከላችን መገኘታቸውን እንመለከታለን፤ የቅዱስነታቸውን ድምጽ ባንሰማ የእርሳቸው መኖር መጽናኛችን ነው፤ የእርሳቸው ቡራኬ ሰላምን ያሰጠናል፣ ሐዋርያዊ መልዕክታቸውም ገና ትኩስ ለሆነው ቁስላችን የፈውስ መድኃኒት ይሆንልናል፤ አሁን የሰላም ጊዜ ነውና!” ብለዋል።

በሁከት መካከል የተደረገ ጎብኝ ነው

የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን ሐዋርያዊ ጉብኝት፣ በሰሜን ምዕራብ እና ደቡብ ምዕራብ የሚገኙ የካሜሩን ሕዝቦች፣ እነርሱ ባልፈጠሩት ከፍተኛ ችግር ውስጥ በወደቁበት ጊዜ መሆኑ ሲታወቅ፣ ሐዋርያዊ ጉብኝቱን ያስተባበሩት በካሜሩን የሚገኙ የቅድስት መንበር እንደራሴ፣ ሊቀ ጳጳስ ጁሊዮ ሙራት እና ረዳታቸው ክቡር አባ ማርዮ ቢፊ መሆናቸው ታውቋል። በእነዚህ አካባቢዎች የሚኖሩ በርካታ ሰዎች ከመኖሪያ አካባቢያቸው ተፈናቅለው በጎረቤት አገሮች በጥገኝነት የሚኖሩ መሆናቸው ታውቋል። በሥፍራው የንግድ ተቋማት መዘጋታቸው፣ ለአራት አመታት ያህል ሕጻናት እና ወጣቶች ወደ ትምህርት ቤት የማይሄዱ መሆናቸው ታውቋል። ሕጻናት የፖለቲካ መጠቀሚያ በመሆን ለአመጽ እንደሚመለመሉ፣ በሁለቱ አካባቢዎች ሐዋርያዊ አገልግሎታቸውን በማበርከት ላይ የሚገኙ በርካታ ካህናት፣ ገዳማዊያን እና ገዳናዊያት፣ ጳጳሳት እና ምዕመናን በአመጹ መካከል እንደሚገረፉ ብሎም እንደሚገደሉ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ አንድሪው ገልጸው፣ ቢሆንም በፍርሃት እና ጭንቀት ውስጥ ለሚገኝ ምዕመናን ተስፋን በመሰነቅ ቤተክህነቱ የቅዱስ ወንጌልን መልካም መልዕክት ማድረስ መቀጠላቸውን አስታውቀዋል።      

የእምነት ጥንካሬ

በባሜንዳ ከተማ፣ የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ የብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን መገኘት ለሰላም፣ ለፍትህ እና ለዕርቅ የሚሆኑ ሃሳቦችን ለማበርከት የሚጋብዝ ነው ተብሏል። ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ አንድሪውም በመልዕክታቸው፣ የብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን ወደ ባሜንዳ መምጣት “አፈርን እንደሚያረጥብ ዝናብ እንደሚሆኑ እርግጠኞች ነን” ብለው፣ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ወደ አመጽ ተመልሰን ሳንገባ በመካከላችን ፍቅርን ማሳየት እንድንጀምር ያደርጋል ብለዋል። ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ አንድሪው ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን ያቀረቡትን የሰላምታ ንግግራቸውን ሲያጠቃልሉ “የባሜንዳ ሕዝብ ብዙ ነገር ቢጎለውም ነገር ግን በእግዚአብሔር ላይ ያለውን እምነት አላጣም” ብለው “ማረጋገጫውም በዚህ አስፈሪ ወቅት በቁጥር እጅግ በርካታ የባሜንዳ ሕዝብ በሥፍራው መገኘቱ ነው” ካሉ በኋላ “እምነታችን ዘወትር ከሚደርስብን ማስፈራሪያ እና ዛቻ ይበልጥብናል” በማለት አስረድተዋል። በማከልም በእዚህ ሥፍራ መገኘታችን ዲያቢሎስ ሐሰተኛ መሆኑን ያረጋግጣል ብለው፣ በእግዚአብሔር ባላቸው እምነት በመታገዝ፣ ለተደረገላቸው ሐዋርያዊ ጉብኝት ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን ካመሰገኑ በኋላ ለሰላም እና ለዕርቅ የጋራ ጸሎችንን እናቅርብ ብለዋል።       

የመጀመሪያዎቹ የሰላም ፍሪዎች

በካሜሩን ሰላም እና እርቅ እንደሚወርድ ከነዋሪው ሕዝብ የሚታዩ የተስፋ ምልክቶች መኖራቸው ሲነገር፣ ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን ባካሄዱባቸው ቀናት በሙሉ ከምዕመናኑ አንደበት የሚወጡ የዝማሬ ቃላት የመጀመሪያዎቹ የሰላም ፍሬዎች መዘራታቸውን ይገልጻሉ ተብሏል። የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን በሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ወቅት በአመጽ መካከል በርካታ ሰዎች ደማቸውን ባፈሰሱባቸው ቦታዎች ተገኝተው የነዋሪውን ስቃይ በመመልከት፣ የሰላም እና የእርቅ መልዕክታቸውን በማስተላለፍ፣ እያንዳንዱ ሰው በሰላም እና በዕርቅ ውይይት ሂደት ላይ እንቅፋት የሚሆኑ ነገሮችን እንዲያስወግዱ አደራ ብለዋል።

03 February 2021, 13:25