ፈልግ

ካርዲናል ካንታላሜሳ እ.አ.አ. የ 2021 ዓ.ም የዐብይ ፆም የመጀመሪያ ስብከትን አቀረቡ! ካርዲናል ካንታላሜሳ እ.አ.አ. የ 2021 ዓ.ም የዐብይ ፆም የመጀመሪያ ስብከትን አቀረቡ! 

ካርዲናል ካንታላሜሳ እ.አ.አ. የ 2021 ዓ.ም የዐብይ ፆም የመጀመሪያ ስብከትን አቀረቡ!

የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ አሁን የምንገኝበት ወቅት የዐብይ ጾም ወቅት እንደ ሆነ ይታወቃል። በዚህ በዐብይ ጾም ወቅት ተገቢ የሆነ መንፈሳዊ ዝግጅት ለማድረግ ይቻል ዘንድ የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት እና በቫቲካን የእርሳቸው የቅርብ የሥራ ተባባሪ የሆኑት ብጹዕን ጳጳሳት እና ቄሳውስት በአጠቃላይ የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ቤት ሰባኪ የሆኑት ካርዲናል ራኔሮ ካንታላሜሳ ይህንን የዐብይ ጾም ወቅት ምክንያት በማደረግ ዘወትር አርብ እለት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በተገኙበት መንፈሳዊ አስተንትኖ እንደ ሚያደርጉ የሚታወቅ ሲሆን በእዚህም መሰረት እርሳቸው ለእዚህ ለጎርጎሮሳዊያኑ 2021 ዓ.ም የዐብይ ጾም ወቅት የመረጡት መሪ ሐሳብ “ሰዎች እኔን ማን ይሉኛል?” የሚለው ከማቴዎች ወንጌል በተወሰደው ጥቅስ ላይ መሰረቱን ያደረገ እንደ ሆነ የተገለጸ ሲሆን በየካቲት 19/2013 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በጳውሎስ 6ኛ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ውስጥ ባደረጉት አስተንትኖ ኢየሱስ ሁላችንም ወደ ንስሐ መንገድ እንድንመለስ ይጠራናል ማለታቸው ተገልጿል።  

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ እና በቫቲካን የእርሳቸው የቅርብ የሥራ ተባባሪ የሆኑት ብጹዕን ጳጳሳት እና ቄሳውስት በአጠቃላይ የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ቤት ሰባኪ የሆኑት ካርዲናል ካንታላሜሳ በእለቱ ባደረጉት አስተንትኖ “ንስሐ ግቡ፣ በወንጌል አምኑ!” በሚለው አንቀፅ ላይ በማተኮር የዐብይ ጾምን ወቅት አጠቃላይ እይታ አቅርበዋል ፡፡

ሶስቱ ወደ ንስሐ መመለሻ ጊዜዎች

ንስሐ መግባት ወይም መለወጥ ካርዲናል ካንታላሜሳ እንዳሉት በሕይወታችን ውስጥ ካሉ የተለያዩ ጊዜያት ጋር በሚመሳሰል መልኩ በአዲስ ኪዳን ውስጥ “በሦስት የተለያዩ ጊዜያት እና አውዶች” ውስጥ ተጠቅሷል ማለታቸው ተገልጿል።

የመጀመሪያው የተመሰረተው ኢየሱስ በአገልግሎቱ መጀመሪያ ላይ “ንስሐ ግቡ በወንጌልም እመኑ” በሚሉት ቃላት ላይ እንደ ሆነ የገለጹት ካርዲናል ካንታላሜሳ ይህ በዋነኝነት የሞራል ስሜት ጋር የተገናኘ ሳይሆን ነገር ግን ወይም ይልቁንም በመጀመሪያ እምነትን፣ ማመንን፣ ከእግዚአብሄር ጋር ያለንን ግንኙነት እንዴት መመልከት እና መለወጥ እንደ ሚገባን የሚያሳይ ነው ብለዋል።

ሁለተኛው አዲስ ኪዳን ወደ ንስሐ ወይም ወደ ኢየሱስ እንድንመለስ ከሚያቀርብልን ጥሪ የሚመነጨው ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን “ተመልሳችሁ እንደ ሕጻናት ልጆች ሁኑ” ብሎ ካቀረበላቸው ጥሪ እንደ ሆነ የገለጹት ካርዲናል ካንታላሜሳ እዚህ ጋር “ኢየሱስ እውነተኛ የሆነ መንፈሳዊ ለውጥ እንድናመጣ” ደቀ መዛሙርቱን እና እኛንም ወደ እዚህ መንገድ እንድንመለስ በመጥራት “ራሳችንን ማዕከል ካደረገ አስተሳሰብ በመውጣት ክርስቶስን ማዕከል ወዳደረገ ሕይወት መዘዋወር” ማለት እንደ ሆነ ገልጸዋል።  እንደ ካርዲናል ካንታላሜሳ አገላለጽ እንደ ሕጻናት ልጆች መሆን ማለት ኢየሱስን ለመጀመሪያ ጊዜ በእውነት ወደ አገኘነው ጊዜ መመለስ ማለት ነው ብለዋል።

በመጨረሻም በራእይ መጽሐፍ ውስጥ ኢየሱስ “ቀዝቃዛ ወይም ትኵስ እንዳልሆንህ ሥራህን ዐውቃለሁ፤ ቀዝቃዛ ወይም ትኵስ ብትሆን በወደድሁ ነበር። እንግዲህ ለብ ያልህ ብቻ እንጂ ትኵስ ወይም ቀዝቃዛ ስላልሆንህ ከአፌ አውጥቼ ልተፋህ ነው” (ራእይ 3፡15) በማለት ኢየሱስ ስለማይሞቃቸው ወይም ስለማይበርዳቸው ሰዎች መናገሩን በማውሳት “በቅንነት ወደ ንስሐ እንዲመለሱ” ጥሪ ማድረጉን የገለጹ ሲሆን ካርዲናል ካንታላሜሳ “እዚህ ላይ ያለው ትኩረት መካከለኛ እና ለብ ያለ ከመሆን ወደ ልበ ቅንነት መለወጥ ነው” ያሉ ሲሆን ይህ የራሳችን ሥራ አይደለም በማለት አበክረው የተናገሩ ሲሆን ይልቁንም የመንፈስ ቅዱስ ሥራ ነው ብለዋል።

ለብ ያለ ከመሆን ወደ ቅንነት መሻገር

ካርዲናል ካንታላሜሳ አስተንትኖዋቸውን ሲቀጥሉ ደቀ መዛሙርቱ በመጀመሪያው የበዓለ አምሣ ዕለት በመንፈስ ቅዱስ ሲሞሉ የነበረውን ልምዳቸውን አስታውሰዋል። የቤተክርስቲያኗ አባቶች ይህንን ተሞክሮ “በስካር እንደ መደንዘዝ” ከሚለው ምስል ጋር አያይዘውት እንደ ነበረ የገለጹ ሲሆን ደቀመዛሙርቱ ሰዎቹ እንዳሰቡት በወይን ጠጅ አልሰከሩም ይልቁንም መንፈስ ቅዱስን ተቀብለው በመንፈሳዊነት ሰክረው ነበር ብለዋል።

“ይህንን በስካር መደንዘዝ የሚለውን ምስል ወስደን በታሪክ እና በቤተክርስቲያኗ ውስጥ አሁን ባለው ሁኔታ እንዴት ልንመለከተው እንችላለን?” በማለት ጥያቄ ያነሱት ካርዲናል ካንታላሜሳ በእየለቱ ከምንካፈለው የቅዱስ ቁርባን እና የቅዱሳት መጻሕፍት መንገዶች ባሻገር መሄድ እንደ ሚገባ የገለጹ ሲሆን ካርዲናሉ ቅዱስ አምብሮዚዮስን በመጥቀስ ሦስተኛ “ያልተለመደ” መንገድ መከተል እንደ ሚገብ አየገለጹ ሲሆን “በበዓለ ሃምሳ ዕለት የሐዋርያትን ተሞክሮ በድጋሚ መኖርን” ያጠቃልላል ብለዋል።

ይህ ከሚከሰትበት አንዱ መንገድ “በመንፈስ መጠመቅ” ተብሎ በሚጠራው ውስጥ ነው ፣ ይህም “ስለ ጥምቀት እና ክርስቲያን መሆናችንን የምናረጋግጥበት ብቻ ሳይሆን ስለ መላው የክርስትና ሕይወት መገንዘብ በጣም አስፈላጊ ፍሬ የሆነውን መታደስን ያካትታል”፣ ከኢየሱስ ጋር ‘የግል ግንኙነት’ መፍጠርን እንደ ሚያካትት ገልጸዋል።

ካርዲናል ካንታላሜሳ “ለብ ካለ ልብ ወደ እውነተኛ ልውጥ ወደ ልበ ሙሉነት የመሻገር አስፈላጊነትን” በመግለጽ ይህንን አስተንትኖ የሚታደሙ ሁሉ ይህንን ጸጋ እግዚአብሔር ያጎናጽፈን ዘንድ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በአማላጅነቷ እንድትረዳን መጸለይ እንደ ሚገባ ከተናገሩ በኋላ የእለቱን አስተንቶ አጠናቀዋል።

26 February 2021, 10:56